“ትምህርት ቤቶችን የግጭት ሰለባ የምናደርግበትን መንገድ ማቆም አለብን” ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 8 2017
የኑሮ ውድነት የበረታባቸው የኢትዮጵያ አስተማሪዎችን ለመርዳት ይቋቋማል የተባለው “የመምህራን የኅብረት ሥራ ባንክ” በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ሊጀምር እንደሚችል የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ ፍንጭ ሰጡ። መንግሥት ለአስተማሪዎች ለቤት መሥሪያ የሚሆን መሬት ቢያቀርብ የሚቋቋመው ባንክ በአነስተኛ ወለድ ብድር የሚሰጥ ይሆናል።
ፕሮፌሰር ብርሀኑ ባንኩ በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ሊጀምር እደሚችል ተስፋቸውን የገለጹት ትላንት ማክሰኞ የትምህርት ሚኒስቴርን የ2017 የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ነው።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ የኢትዮጵያ መምህራን የሚከፈላቸው ደመወዝ ልጆቻቸውን ለመመገብ፣ ለማስተማር እና ልብስ ለመቀየር እንኳ የሚበቃ እንዳልሆነ ተችተዋል።
ለመምህራን የሚከፈለው ዝቅተኛ ደመወዝ በሥራ ተነሳሽነታቸው ላይ ጭምር የከፋ ተጽዕኖ እንደሚኖረው የጠቀሱት ደሳለኝ ትምህርት ሚኒስቴር ማሻሻያ እንዲደረግ ግፊት ማድረግ እንደሚኖርበት አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ ለመምህራን የምትከፍለው ደመወዝ “በምንም መስፈርት በቂ” እንዳልሆነ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ አምነዋል። ነገር ግን መሥሪያ ቤታቸው በተናጠል የደመወዝ ማሻሻያ ማድረግ እንደማይችል ለምክር ቤቱ ያስረዱት የትምህርት ሚኒስትሩ መንግሥት ለአስተማሪዎች የደመወዝ ጭማሪ አድርጎ ችግሩን የመፍታት ዕድሉ “የረዥም ጊዜ ሕልም” እንደሆነ ተናግረዋል።
“በተለይ በክልሎች በኩል በመንግሥት መሬት ቢያገኙ መምህራን ቤት ለመሥራት የሚያስችል ፋይናንሲንግ እንዲያገኙ ምን እናድርግ?” በሚል ሐሳብ “የመምህራን ባንክ” ለማቋቋም መታሰቡን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።
“እኛ ተስፋ የምናደርገው በሚቀጥለው ዓመት መምህራን የራሳቸው የኅብረት ሥራ ባንክ እንዲኖራቸው አድርገን ቢያንስ subsidized የሆነ ወለድ ኖሯቸው ቤት በሚሠሩበት ጊዜ [ብድር እንዲያገኙ] ለማድረግ እየሞከርን ነው” ሲሉ ፕሮፌሰር ብርሀኑ አብራርተዋል።
በትላንትናው የምክር ቤቱ ውሎ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል በግጭት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ተማሪዎች ቁጥር እና ችግሩን እንዴት ይፈታል የሚለው ይገኝበታል።
ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ልጆች በሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ከትምህርት ቤት ውጪ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) በታኅሳስ 2017 ይፋ አድርጎ ነበር።
ግጭት፣ ብጥብጥ፣ የተፈጥሮ አደጋዎች እና መፈናቀል የኢትዮጵያን ልጆች ከትምህርት ያራቁ ዋንኛ ምክንያቶች ናቸው። በሪፖርቱ መሠረት በአማራ ክልል 4.4 ሚሊዮን፣ በኦሮሚያ ክልል 3.2 ሚሊዮን፤ በትግራይ ክልል 1.2 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ልጆች ትምህርት ቤት አይሔዱም።
ከትምህርት ቤት ውጪ የሆኑ ተማሪዎችን ቁጥር በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት “እስከ 10 ሚሊዮን ያደርሰዋል” ያሉት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ “ቢያንስ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ ምን እየተሠራ” እንደሆነ ጠይቀዋል።
ፕሮፌሰር ብርሀኑ ግን በተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት የተጠቀሰውን ቁጥር “በፍጹም አላምንም” ሲሉ ተናግረዋል። ቢሆንም “7.2 ሚሊዮን ልጆቻችን ትምህርት ቤት አለመግባታቸው በጣም በጣም ሊያሳስበን የሚገባ ጉዳይ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። የኢትዮጵያን ልጆች ከትምህርት ገበታ ያራቀው “ትልቁ” ምክንያት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚካሔዱ ግጭቶች መሆናቸውንም አምነዋል።
ፕሮፌሰር ብርሀኑ ማብራሪያ ሲሰጡ “እነዚህን ግጭቶች መፍታት እንኳ ባንችል፤ በግጭቱ ውስጥ የሚሳተፉ በሁሉም ወገን ያሉ ሰዎች ትምህርት ቤቶችን መተው እንዴት ያቅታቸዋል?” ሲሉ ጠይቀዋል።
በግጭቱ የሚሳተፉ ኃይሎች “እንዴት ነው መምህራንን የሚገድሉት? እንዴት ነው ተማሪዎች ትምህርት ቤት እንዳይገቡ የሚከለክሉት?” ያሉት ብርሀኑ “እንደ ሕብረተሰብ አይነኬ” ከሚባሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ትምህርት ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል።
“በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት የፖለቲካ ግጭት ውስጥ ልንገባ እንችላለን” ያሉት ፕሮፌሰር ብርሀኑ “ነገር ግን የነገውን ትውልድ የሚገድል፤ ያውም ራሳችን ቆመንለታል የምንለውን ማኅበረሰብ የሚገድል ሲሆን በጣም በጣም ያሳዝናል፤ ያሳፍራል” ሲሉ አውግዘዋል።
“ትምህርት ቤቶችን የግጭት ሰለባ የምናደርግበትን መንገድ ማቆም አለብን” ያሉት ብርሀኑ “እኔ ወደ አንዱ እየወገንኩ አይደለም። ሁሉንም ነው አቁሙ ማለት ያለብን” ሲሉ ተደምጠዋል።
አርታዒ ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር