1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትምህርት ያልተጀመረበት ጎሮዶላ ወረዳ

ማክሰኞ፣ ጥር 7 2016

ኦሮሚያ ክልል ከመዋቅር ጋ በተገናኘ ተቃውሞ ጎሮዶላ ወረዳ የተለያዩ የማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥራ መስተጓጎሉ ትምህርትም አለመጀመሩ ተገለጸ ። እስካሁን ትምህርት አለመጀመሩ የተነገረው ባለፈው ዓመት ኦሮሚያ ክልል በዘረጋው አዲስ የዞን መዋቅር በምስራቅ ቦረና ስር በተዋቀረው ጎሮዶላ ወረዳ ነው ።

የኦሮሚያ ክልል አዲስ የዞን መዋቅር
ባለፈው ዓመት ሚያዚያ 2015 ይፋ የሆነው የኦሮሚያ ክልል አዲስ የዞን መዋቅር ከጉጂ፣ ቦረና እና ባሌ ዞኖች የተወሰኑ ወረዳዎችን ምስራቅ ቦረና በሚል አዲስ 21ኛ ዞን ማዋቀሩን ተከትሎ በአከባቢው በተለይም በጉጂ ዞን ሰፊ ተቃውሞ በማስነሳት የሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል፡፡ ምስል Private

ሥራና አገልግሎት የተስተጓጎለው ዞናዊ መዋቅሩን በመቃወም ነውም ተብሏል

This browser does not support the audio element.

ኦሮሚያ ክልል ከመዋቅር ጋ በተገናኘ ተቃውሞ ጎሮዶላ ወረዳ የተለያዩ የማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥራ መስተጓጎሉ ትምህርትም አለመጀመሩ ተገለጸ ። እስካሁን ትምህርት አለመጀመሩ የተነገረው ባለፈው ዓመት ኦሮሚያ ክልል በዘረጋው አዲስ የዞን መዋቅር በምስራቅ ቦረና ስር በተዋቀረው ጎሮዶላ ወረዳ ነው ። በዚህም ስጋት እንደገባቸው የተናገሩት ተማሪዎች እና የተማሪዎች ወላጆች ነገሩ እንዳሳሰባቸው አስረድተዋል ። በወረዳው ትምህርትን ጨምሮ የተለያዩ የማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥራ የተስተጓጎለው ዞናዊ መዋቅሩን በመቃወም ነውም ተብሏል

የተማሪዎች ስጋት

ጫልቱ ባናታ ሶርሳ ትባላለች፡፡ ነዋሪነቷ ቀደም ሲል በጉጂ ዞን ስር ይተዳደር በነበረውና አሁን በምስራቅ ቦረና ዞን ስር በተዋቀረው ጎሮዶላ ወረዳ ነው፡፡ ጫልቱ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን አሁን ድረስ ግን የዘንድሮው 2016 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ትምህርቷን አልጀመረችም፡፡ ተማሪዋ ለዶይቼ ቬለ በስልክ በሰጠችው አስተያየት በዚህ ወረዳ ተማሪዎች በተለይም እንደሷ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን የሚወስዱ ተማሪዎች የትምህርት ጅማሮን ብጠባበቁም እስካሁን የተጀመረ ትምህርት የለም፡፡

"የጎሮዶላ ወረዳ በጉጂ ስር ነበር የሚተዳደረው፡፡ አሁን መልሰው ምስራቅ ቦረና ዞን ስር እንዲተዳደር ሆነ፡፡ ከዚህ የተነሳ ዘለግ ያለ ተቃውሞ ተነሳ፡፡ መንግስት ለህዝቡ ተቃውሞ ምላሽ እሰጣለሁ ጠብቁ ቢልም እስካሁን የሰጠን ምላሽ የለም፡፡ ከዚሁ የተነሳ ተማሪዎችም ጥያቄው መልስ እስኪያገኝ ድረስ አንማርም እያሉ ነው፡፡ አንድም ተማሪ ወደ ትምህርት ቤት እየሄደ አይደለም፡፡ እኔ አሁን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ ነኝ፡፡ ግን አሁን በዚህ ወረዳ ስለ ትምህርት እንኳ የሚያነሳ የለም፡፡ መንግስት ከላይ መዋቅር መጥቶ ምንድነው ችግራችሁ፣ ትምህርትስ ለምን አልጀመራችሁም አላለንም፡፡ እስካሁን ድረስ ትምህርት በወረዳችን አልተጀመረም፤ ወደ ትምህርት ቤት ያመራ ተማሪም የለም" በማለትም አስተያየቷን አጋርታናለች፡፡

ሌላም የ11ኛ ክፍል ተማሪ አስተያየቱን አከለ፡፡ "እኛ ጋ ትምህርት አልተጀመረም፡፡ አንድ ሁለት ትምህርት ቤቶች ትምህርት የመጀመር ጥረት አድርገው የ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ኑና ፎርም ሙሉ ብለው ነበር፡፡ በዚያም የተወሰኑትን ተማሪዎች ወደ ትምህር ቤት እንዳያመሩ ትከለክላላችሁ በማለት የታሰሩ አሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ከስምንተኛ ወር ጀምሮ በኦሮሚያ የተዘረጋው አዲስ ዞናዊ መዋቅር ግን ለዚህ ሁሉ ችግር መነሻ ምክንያት ነው፡፡ በአከባቢያችን ያ መዋቅር ተቃውሞ ስለገጠመው መረጋጋት የለም፡፡ ከዚህ የተነሳ ዘንድሮ ትምህርት እንደጎሮ ዶላ ወረዳ ምንም የለም" ብለዋል፡፡

ኦሮሚያ ክልል ከመዋቅር ጋ በተገናኘ ተቃውሞ ጎሮዶላ ወረዳ የተለያዩ የማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥራ መስተጓጎሉ ትምህርትም አለመጀመሩ ተገልጿል። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Private

ከሱ ጋር ቤተሰቡ ሰባት ተማሪዎችን እንደሚያስተምሩ የሚገልጸው ይህ አስተያየት ሰጪ የአርብቶ አደር ልጅ መሆኑንም ገልጸው በቁጥር ውስን የሆኑ የተሻለ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ወደ ሌሎች መረጋጋት ወደሚስተዋልባቸው ከተሞች ልጆቻቸውን ልከው ቢያስተምሩም እሱ ግን ከአቅም ውስንነት የተነሳ ይህን እድል ማግኘት እዳልቻለ አስረድቷል፡፡

"አቅም ያላቸው ሰዎች ልጆቻቸውን አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ አዶላ አሊያም ሻኪሶ እየወሰዱ ቤት ተከራይተውላቸው ቀለብ ሰፍረው ያስተምራሉ፡፡ እኛ ግን አቅም የሌለን እዚህ ትምህርት የለም፤ ሌላ ቦታም ሄደን ለመማር አቅሙ የለንም፡፡ ግን ከወረዳችን አጠቃላይ ተማሪዎች መሰል እድል ያላቸው በእጅጉ ትንሽ ቁጥር ያላቸው ናቸው፡፡ በብዛት የአርብቶ አደር ልጆች እንደመሆናቸውን ቤተሰቦቻችን እያገዝን ካልሆነ ርቀን መማር አንችልም፡፡ የኔን ብነግርህ እኛ ለቤተሰቦቻችን ሰባት ልጆች ነን፡፡ እኔ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነኝ፡፡ ተላላቆችና ተናናሾች አሉኝ፡፡ ወደ ሌላ ቦታ ሄደን ለመማር በፍጹም አቅሙ የለንም፡፡ እባካችሁ ድምጽ በመሆን አግዙን፡፡ ከባድ ጉዳት ውስጥ ነን" በማለት ሃሳቡንም አጋርቶናል፡፡

የወላጆች ጥያቄ

በዚህ ተቃውሞ ባየለበት ወረዳ የትምህርት አለመጀመር  ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን የተማሪዎች ወላጆችንም በእጅጉ አሳስቧል፡፡ አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ የተማሪዎች ወላጅም ይህን ብለውናል፡፡ "ህዝቡ ባለው ቅሬታ ተማሪዎች አንማርም እያሉ ነው፡፡ ማኅበረሰቡም በተሰማው ቅሬታ ልጆቹን ወደ ትምህርት እየላከ አይደለም፡፡ እስካሁን ትምህርት አልተጀመረም፡፡ ቢከፈትም ጥያቄ አለንና አንማርም እያሉ ነው ተማሪዎቻችን፡፡ በዚህ ውድ ኑሮ ሌላ ቦታ ወስደን ለማስተማር ብናስብም አቅማችን አይፈቅድም" ብለዋል፡፡

የአስተዳደር መዋቅሩ ያስተጓጎለው ማኅበራዊ አገልግሎት

ኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ባለፈው ዓመት ከመዋቅር ጋ በተገናኘ ተቃውሞ ተከስቶ ሕይወት መጥፋቱ ይታወሳል። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Private

ተማሪዎቹና የተማሪዎቹ ወላጆች ያነሱትን ስጋት ብሎም አስተያየት ይዘን ለወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ብንደውልም የወረዳው ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ገልጸው ሃሳባቸውን ሳያጋሩን ቀርተዋል፡፡ የዚህ ወረዳ ተማሪዎች እጣፈንታ ምን ሊሆን ይችላል በሚል ለኦሮሚያ ክልል ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊዎች ደውለንም አንድ ከፍተኛ አመራር ችግሩ ከአስተዳደር ጋር የተያያዘ በመሆኑ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ገልጸውልናል፡፡

ባለፈው ዓመት ሚያዚያ 2015 ይፋ የሆነው የኦሮሚያ ክልል አዲስ የዞን መዋቅር ከጉጂ፣ ቦረና እና ባሌ ዞኖች የተወሰኑ ወረዳዎችን ምስራቅ ቦረና በሚል አዲስ 21ኛ ዞን ማዋቀሩን ተከትሎ በአከባቢው በተለይም በጉጂ ዞን ሰፊ ተቃውሞ በማስነሳት የሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል፡፡ ይህ የዞን መዋቅር የአከባቢውን ልማት እና ጸጥታ ማዕከል አድርጎ አስፈላጊነቱ በመታመኑ በአዲስ መልክ ማዋቀር ማስፈለጉንም ተቃውሞውን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት በተለያዩ ጊዜያት ማብራሪያ መስጠታቸውም አይዘነጋም፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW