ትራምፕ «ከሦስተኛ ዓለም ለሚመጡ ዜጎች ጥገኝነት ተቋርጧል» አሉ
ዓርብ፣ ኅዳር 19 2018
ትራምፕ «ከሦስተኛ ዓለም ለሚመጡ ዜጎች ጥገኝነት ተቋርጧል» አሉ
ዩናይትድ ስቴትስ ከሦስተኛ ዓለም ሀገራት ስደተኞችን መቀበል ማቆምዋን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታወቁ። ይህ የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተያየት የተሰማዉ አንድ አፍጋናዊ ሁለት የአሜሪካ ብሔራዊ ዘቦች ላይ ተኩስ ከፍቶ ካቆሰላቸዉ በኋላ ነዉ። ከኤርትራ፣ ከሶማልያ፣ ሊቢያና የመንን ጨምሮ ከ 19 ሃገራት የመጡ ስደተኞች የአሜሪካ የመኖርያ ፈቃዳቸዉ በጥልቅ ይመረመራል ተብሏል።
የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ከሦስተኛው ዓለም ሀገራት የሚደረገውን ስደት ሁሉ በዘላቂነት እንደሚያቆሙ” አስታውቀዋል። የትራምፕ ይህ አስተያየት የተሰማዉ ከትናንት በስትያ ረቡዕ አንድ አፍጋናዊ, ዋሽንግተን ነጩ ቤተ-መንግሥት አቅራቢያ ሁለት የብሔራዊ ዘብ አባላት ላይ ተኩስ ከፍቶ ከፍተኛ ጉዳት ካሰረሰ በኋላ ነዉ። ከቁስለኞቹ አንዱ መሞቱ ተዘግቧል። ትናንት ሃሙስ ፕሬዚዳንት ትራምፕ “የሦስተኛ ዓለም አገሮች” ካሉዋቸው አገሮች የሚሰደዱ ሰዎችን ዩናይትድ ስቴትስ እንደማትቀበል ገልፀዋል። ትራምፕ አፋጋናዊዉ በዋሽንግተን ጥቃት እንዳደረሰ አገራችንን የማይወድን አንፈልግም ብለዋል።
«በባይደን አስተዳደር ከአፍጋኒስታን ወደ አገራችን የገቡትን የውጭ ዜጎች ሁሉ እንደገና መመርመር አለብን። ማንኛውም የውጭ ዜጋ ከየትኛውም ሀገር እዚህ ያልሆነ ወይም አገራችንን የማያገለግል ማንኛውንም አይነት እርምጃ መውሰድ አለብን። አገራችንን መውደድ ካልቻሉ እኛ አንፈልጋቸውም።» «የአሜሪካ ስርዓት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ እንዲያገግም ለማስቻል ከሁሉም የሦስተኛ ዓለም ሀገራት የሚደረግ ስደትን በዘላቂነት አቆማለሁ» ሲሉ ትራምፕ ትናንት ለሊቱን «ትሩዝ ሶሻል ሚዲያ» በተባለዉ የግል ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴያቸዉ ላይ መረጃን አጋርተዋል። በኢኮኖሚ ታዳጊ ሀገራት ሲሉ ጊዜ ያለፈበት እና አፀያፊ ቃል መጠቀማቸዉን ዶቼ ቬለን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ከዚህ በተጨማሪ "ለዩናይትድ ስቴትስ የተጣራ ሀብት ያልሆነን ማንኛውንም ሰው እንደሚያስወግዱ ትራምፕአክለዉ ገልፀዋል። «ዜጋ ላልሆኑ ሰዎች የሚሰጠውን የፌደራል ጥቅማጥቅሞች እና ድጎማዎች ሁሉ እንደሚያቋርጡ እና የሀገር ውስጥ ሰላም እና መረጋጋትን የሚጎዱ የዉጭ ዜጎችን የዜግነት ፈቃዳቸዉን እንደሚነጥቁ አስታዉቀዋል። አንድ የውጭ ዜጋ ህዝባዊ ተጠያቂነት፣ ደህንነት ስጋት አልያም ከምዕራባዊያን ስልጣኔ ጋር የማይጣጣም አይነት ከሆነ» አባርራለሁም ሲሉ ጽፈዋል። ይህ የአፍቃኒስታን ታሊባን ወደ ስልጣን ከመመለሱ በፊት በአፍጋኒስታን ከአሜሪካ ጋር ይሰሩ ለነበሩ እና በልዩ የቪዛ ፕሮግራም አሜሪካ ዉስጥ የሚኖሩ አፍጋኖችንም እንደሚያካትት ትራምፕ ባጋሩት መረጃ ገልፀዋል። ዋሽንግተን ዲሲና ሜሪላንድ አካባቢ ጠበቃና የሕግ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ፍጹም አቻሜለህ ዓለሙ እንዳሉት አፍጋኑ የፈፀመዉ አይነት ጥቃት ለትራምፕ አስተዳደር በእሳት ላይ ቤንዚን እንደመጨመር ያህል ነዉ።
በዩናይትድ ስቴትስ የምስጋና ቀን በሚከበርበት በትናንትናዉ እለትየትራምፕ አስተዳደር ከ19 ሀገራት የመጡ ስደተኞችን የመኖሪያ ፍቃድ እንዲመረመር በጥልቅ ትዕዛዝ ያስተላለፈዉ፤ አፋጋናዊዉ ግለሰብ ነጩ ቤተ-መንግሥት አቅራብያ ሁለቱን ዘቦች በፅኑ ካቆሰለ በኋላ ነው። ግለሰቡ እንደ ጎርጎረሳዉያኑ በ2021 በአፍጋኒስታን ውስጥ ከአሜሪካ ወታደራዊ እና የስለላ አገልግሎቶች ጋር ከሰራ በኋላ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መምጣቱ ተዘግቧል። የአሜሪካ ዜግነት እና ኢሚግሬሽን አገልግሎት (USCIS) ዳይሬክተር ጆሴፍ ኤድሎ በኤክስ ማኅበራዊ መገናኛቸዉ ላይ ይፋ እንዳደረጉት «ለሁሉም አሳሳቢ ሀገራት ለተባሉ ሁሉ የመኖርያ ፈቃዳቸዉ «ግሪን ካርድ» በጥልቀት እና በጥብቅ እንዲመረመር ትዕዛዝ አስተላልፌያለሁ።» ሲሉ ጽፈዋል።
ባለፈዉ ረቡዕ አፍጋናዊዉ ዋሽንግተን ዉስጥ ጥቃት ካደረሰ በኋላ የትራምፕ አስተዳደር የአፍጋኖች የጥገኝነት ማመልከቻዎችን ሁሉ ዉድቅ ማድረጉንን እና መዝጋቱን አስታዉቋል። ባለፈዉ ሰኔ ወር በወጣው አዋጅ መሰረት ምርመራ እንዲደረግባቸዉ ትዕዛዝ የተላለፈባቸዉ 19 ሀገራት ዜጎች በመጀመርያ ደረጃ የማጣራት ሂደት እንዲደረግ እና የጉድለት አለባቸው ተብለው በሚገመቱ ሃገራት ዜጎች ላይ የመግቢያ ገደቦች ተጥሏል። ከነዚህ ሃገራት መካከል አፍጋኒስታን፣ ሶማሊያ፣ ሊቢያ ፤ የመን፣ ቻድ እና ኤርትራ ይገኙበታል። ትችት አቅራቢዎች የተላለፈዉ ትዕዛዝ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህጋዊ ቋሚ ነዋሪዎችን የመቅጣት ብሎም ዜግነትንም የመንጠቅ አደጋ አለዉ ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። በዉጭ ዜጎች ላይ ይደረጋል የተባለዉ የመኖርያ ፈቃድ ግምገማ የዜግነት መብትን ይሻር አልያም ዜጎችን ያስጠርዝ ግልጽ የተነገረ ነገር የለም።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ