1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ትራምፕ፤ የአባይ ግድብና የግብፅና ኢትዮጵያ

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ሐሙስ፣ ጥር 14 2018

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ያሳሰባቸው ይመስላል። እሳቸው እንደሚሉት በግድቡ ምክንያት ግብፅ የውኃ እጥረት ይገጥማታል ነው። ለዚህ ደግሞ ሰላማዊ መፍትሄ ማምጣት እንደሚችሉ በድጋሚ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ደጋግመው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ (ፎቶ ከማኅደር)ምስል፦ Luis Tato/AFP

ትራምፕ፤ የአባይ ግድብና የግብፅና ኢትዮጵያ

This browser does not support the audio element.

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ያሳሰባቸው ይመስላል። እሳቸው እንደሚሉት በግድቡ ምክንያት ግብፅ የውኃ እጥረት ይገጥማታል ነው። ለዚህ ደግሞ ሰላማዊ መፍትሄ ማምጣት እንደሚችሉ በድጋሚ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ደጋግመው ተናግረዋል። በዓለም የኤኮኖሚ ጉባኤ ለመሳተፍ ዳቮስ ስዊዘርላንድ በተገኙበት አጋጣሚ ከግብፁ ፕሬዝደንት ጎን ተቀምጠው ይህንኑ መቆርቆራቸውን በይፋ አሳይተዋል። ይሳካላቸው ይሆን?

የዩናይትድ ስቱትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የገነባችው ታላቁ የኅዳሴ ግድብ ጉዳይ እንቅልፍ የነሳቸው መስሏል። በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ከዓመታት በፊት ጉዳዩን አንስተው ትራምፕ ኢትዮጵያ የግድብ ግንባታውን ካላቆመች ግብፅ በአውሮፕላን ቦምብ ልታፈራርሰው ትችላለች ማለታቸው በወቅቱ በኢትዮጵያውያን በኩል ቁጣ መቀስቀሱ ይታወሳል። ውዝግቡ መፍትሄ እንዲያገኝም ጉዳዩ ወደ አፍሪቃ ሕብረት መድረክ ተመርቶ ሱዳን እና ግብፅ፤ ከኢትዮጵያ ጋር የገቡበትን ንትርክ ለማርገብ ጥረት አድርጓል።

ኢትዮጵያ ሕዝቧን በማስተባበር በአባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው ግድብ ለኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭነትና ለሀገራዊ ልማት ወሳኝ ፕሮጀክቴ ነው ትላለች። ግብፅ የውኃ ደኅንነቴን ያሳጣኛል በማለት ግድቡን የሕልውናዋ ስጋት አድርጋ ትመለከታለች። እንደ የአባይ የታችኛው ተፋሰስ ሀገር የውኃ ስጋት እንዳለባት የምትገልጸው ሱዳንም ኢትዮጵያ አባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው ታላቅ ግድብ የሚመለከታት ሌላዋ ተደራዳሪ ሀገር ናት። የአፍሪቃ ሕብረት የማሸማገል ጥረት እነዚህ ሃገራት ወደሚያግባባ መፍትሄ መምራት ላይ ያተኮረ ነው። ምንም እንኳን የሕብረቱ ሽምግልና ውጥረቱ እንዳይባባስ ቢረዳም አሳሪ ከሚባል ስምምነት ላይ ግን አልተደረሰም።

ለዚህም ይመስላል ኢትዮጵያ ትኩረቷን ግድቡን ውኃ በመሙላትና ኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ላይ ስታደርግ፤ ግብፅ ደግሞ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በውስጥም ሆነ በውጪ ከሚወዛገቡ ኃይላት ጋር ግንኙነት የመመስረትና የመቀራረብ ሙከራዎችን የምታደርገው።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና የግብፁ ፕሬዝደንት አብደል ፈታህ አልሲሲ(ፎቶ ከማኅደር)ምስል፦ Pat Benic/IMAGO

ትራምፕም ታዲያ በድጋሚ ወደ ዋይት ኀውስ ሥልጣን መመለሳቸውን ተጠቅመው ታዲያ ኢትዮጵያ እና ግብፅ በአባይ ግድብ ምክንያት ጦርነት ከመክፈታቸው አስቀድሜ እኔ አደራድራቸዋለሁ እያሉ ነው።  በእርግጥ ትራምፕ እንደሚሉት በአባይ ግድብ ምክንያት ግብፅ ወደ ጦርነት ታመራ ይሆን? ባልደረባዬ አንጋፋው ጋዜጠኛ ነጋሽ መሀመድ እንደሚለው ግን ግብፅ የፊት ለፊት ጦርነት ላትመርጥ ትችላለች።

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በአንድ ዓመት የሥልጣን ቆይታቸው በየጊዜው ከሚያስተላልፏቸው አወዛጋቢ ውሳኔዎችና እርምጃዎች ጎን ለጎን የሰላም መልእክተኛ ለመሆን ጥረት እያደረጉ ነው። በእስራኤል ፍልስጤም ጉዳይ የግብፁን ፕሬዝደንት በአደባባይ ያመሰገኑት ትራምፕ ካይሮ ከአዲስ አበባ ጋር በአባይ ግድብ ምክንያትለገባችበት ውዝግብ መፍትሄ እንደሚያስገኙ መናገር ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ይሳካላቸው ይሆን? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ ጋዜጠኛ ነጋሽ የሚለው ትራምፕ በአልሲሲ በኩል ሊያሳኩት የሚፈልጉት ነገር ይኖራል ነው።

ምንም እንኳን ዶናልድ ትራምፕ ሰሞኑን ደጋግመው በአባይ ግድብ ጉዳይ ግብፅና ኢትዮጵያን አሸማግላለሁ ቢሉም ኢትዮጵያ ግን ዝምታን መርጣለች።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW