1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትራምፕ ዳግም ቢመረጡ ለአፍሪቃ ምን ማለት ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 14 2017

ዶናልድ ትራምፕ ሥለተፈጥሮ ጥበቃ ብዙ አይጨነቁም።ሥደተኞች ግን ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ጠንካራ ርምጃ ወስደዋል።ዩናይትድ ስቴትስን ከሜክሲኮ ጋር የሚያዋስነዉን ድንበር በግንብ ማሳጠር ጀምረዉም ነበር።በዘንድሮዉም የምርጫ ዘመቻ በሕግ ወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ የገቡ ሥደተኞች ወደየሐገራቸዉ ለመላክ እየዛቱ ነዉ።

የሪፐብሊካኑ ዕጩ ዶናልድ ትራም ዳግም ሥልጣን ከያዙ ለአብዛኛዉ አፍሪቃዉያን ብዙ አይጠቅሙም ይባላል።
በዘንድሮዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የሚፎካከሩት (ከግራ ቀደ ቀኝ) የሪፐብሊካኑ ፓርቲ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕና የዴሞክራቶቹ ዕጩ ካማላ ሐሪስምስል Alex Brandon/AP/picture alliance und Mat Otero/AP/dpa/picture alliance

ትራምፕ ዳግም ቢመረጡ ለአፍሪቃ ምን ማለት ይሆን?

This browser does not support the audio element.

 

የዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ የወደፊት ፕሬዝደንቱንና ከፊል የምክር ቤት ተወካዮቹን ለመምረጥ እየተዘጋጀ ነዉ።በመጪዉ ጥቅምት 26 ለሚደረገዉ ምርጫ በተለይ ለፕሬዝደንትነት በሚወዳደሩት በቀድሞዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና በምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሐሪስ መካከል ጠንካራ ፉክክር እየተደረገ ነዉ።የምርጫዉ ዉጤት፣ ዩናይትድ ስቴትስ እንደ አብዛኛዉ ዓለም ሁሉ ከአፍሪቃ ጋር በሚኖራት ግንኙነት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳርፍ በሰፊዉ ይታመናል።ዶቸ ቬለ የእንግሊዝኛዉ ክፍል ከወራት በፊት ያነጋገራቸዉ የጋናና የደቡብ አፍሪቃ ተወላጆች ግን በተለይ ትራምፕ ቢመረጡ ለአፍሪቃ ጥሩም፣ መጥፎም ነዉ ባይ ናቸዉ።
                         
ትራምፕ በአፍሪቃዉያን ዕይታ

ለጋናዊቱ ተማሪ ለአቢጌል ግሪፍት ዶናልድ ትራምፕ ሕግ የሚጥሱ፣ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርን የሚቃረኑ «ነዉጠኛ» ብጤ ናቸዉ።«ሁለቴ ተከሰዋል» ትላለች አቢጌል።
«ዶላንድ ትራም በተደጋጋሚ ተጠርጥረዋል።በምክር ቤት ሁለቴ ተከስሰዋል።በ2020 በተደረገዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ሲሸነፉ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዳይደረግ ለማወክ ሞክረዋል።ዳግም ቢመረጡ ለአሜሪካ ጥሩ ዜና አይመስለኝም።እንደ አፍሪቃዊ ለምርጫ መወዳደራቸዉ ያስፈራኛል።ካሸነፉ እሰጋለሁ።»

ሳሙኤል ኦፎሶ ግን አቢጌልን ይቃረናል።ኦፎሶ እንደሚለዉ ባይደን መጥፎ አይደሉም።ግን ትራምፕ ቢመረጡ ደስተኛ ነዉ።
                               
«ዶናልድ ትራምፕ ዳግም የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ቢሆኑ ደስ ይለኛል።ባይደን ጥሩ አይደሉም ማለቴ አይደለም።ግን ትራምፕ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የአፍሪቃ የመሠረተ ልማት አዉታር እንዲሻሻል፣ የአፍሪቃና የዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲካዊ ግንኙነት እንዲዳብር አድርገዋል።በጤና ጥበቃና በሌላዉም መስክ አፍሪቃን ረድተዋል።ጆ ባይደን ግን አፍሪቃ ዉስጥ ሲያደርጉ ያየሁት የLGBTQን ጉዳይ ተቀባይነት እንዲኖረዉ ግፊት ማድረጋቸዉ ብቻ ነዉ።»

የባደን አስተዳደር በምሕጻሩ LGBTQ ተብለዉ የሚጠሩት ግብረ ሰዶማዉያን፣ ፍናፍንቶች፣ ፆታ የቀየሩና መሰል ሰዎች አፍሪቃ ዉስጥ መብታቸዉ እንዲከበር ግፊት አድርጓል።ዩናይትድ ስቴትስ ከአፍሪቃ ሐገራት ጋር ያላት የኤኮኖሚ ትብብርና ተራድኦ መርሕም የነዚሕን ወገኖች መብት ከማስከበር ጋር እንዲያያዝ ባይደን ጥረዋል።አፎንሶ «ለአፍሪቃ ጥሩ አይደለም» ባይ ነዉ።
                             
«የአፍሪቃ ሐገራትን ለመርዳት ቢሞክሩ እንኳን ዋና አላማቸዉ በምትረዳዋ ሐገር LGBTQ እንዳሻቸዉ እንዲሆኑ ማስድረግ ነዉ።ይሕ ለአፍሪቃ ጥሩ አይመስለኝም።»
 

ዶናልድ ትራምፕ በሰሜን ካሮሊና ለተሰበሰበዉ ደጋፊያቸዉ የምርጫ ዘመቻ ቅስቀሳ ሲያደርጉምስል Evan Vucci/AP/dpa/picture alliance

የትራምፕ መመለስ አሳሳቢነት

ኢፄ ሲካንኩ በአክራ ዩኒቨርስቲ የመገናኛ ዘዴዎች፣ የሥነ ጥበብና የግንኙነት መምሕርና የፖለቲካ ተንታኝ ናቸዉ።የትራምፕ ዳግም ሥልጣን መያዝ አፍሪቃን «ሊያሳስብ ይገባል»ይላሉ- ሲካኑ።
                          
«ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ፕሬዝደንት ከሆኑ አፍሪቃን ሊያሰጋ ይገባል»
ትራምፕ ለአፍሪቃ ሥጋት የሚሆኑባቸዉ ዋናዉ ምክንያት ከሚከተሉት አክራሪ ርዕዮተ ዓለም የሚመነጨዉ መርሐቸዉ ነዉ።
                           
«የዶናልድ ትራምፕ አስተሳሰብና ርምጃ የሚመራዉ ከሚከተሉት ርዕዮተ ዓለማዊ መሠረት ነዉ።እሳቸዉ ለሁሉም ነገር መነሻ፣ ዓላማና ግብ የሚያደርጉት ግለኝነትንና በግለኝነት ያላቸዉን እምነት  ነዉ።ወደ ዉስጥ ብቻ የሚያዩ ሰዉ ናቸዉ።የጋራና ሁሉን የሚያካትት ሥራና አሰራር የሚቀበሉ አይደሉም።»
 

ወደ ዉስጥ ብቻ መመልከት

ሲካንኩ እንደሚያምኑት ትራምፕ ዳግም ፕሬዝደንት ከሆኑ ዩናይትድ ስቴትስ ለራስዋ ከሚጠቅማት በስተቀር ከዓለም አቀፍ ጉዳዮች ራስዋን ታገልላለች።ርዕሰ መንበሩን ፕሪቶሪያ-ደቡብ አፍሪቃ ያደረገዉ የፀጥታ ጥናት ተቋም ባልደረባ ፕሪያል ሲንጌሕ ደግሞ ትራም «መጡ የድሮ መርሐቸዉ መጣ» ማለት ነዉ ይላሉ።ለአፍሪቃ አይጠቅምም።
የመልከዓ ምድራዊ ፖለቲካዊ ወዳጅነት
ሌላዉ ደቡብ አፍሪቃዊ የፖለቲካ ተንታኝ ዳንኤል ሲልከ በበኩላቸዉ ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪቃ በምጣኔ ሐብቱም፣ በፖለቲካዉም አስፈላጊ ሐገር ናት ባይ ናቸዉ።
                                          
«ዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ሥፍራ አላት።ከፍተኛ ተፅዕኖ ታደርጋለች።የአጎዋ ስምምነት የአፍሪቃ ሸቀጦች ሰሜን አሜሪካ ዉስጥ እንዲሸጡ በማድረግ ለአፍሪቃ ንግድ ብዙ ይጠቅማል።ከፀጥታ አኳያ ደግሞ ከአሸባሪዎችና ከተለያዩ ደፈጣ ተዋጊዎች ጋር ለሚዋጉ ለበርካታ የአፍሪቃ ሐገራት ድጋፍ ታደርጋለች።»

የጋና ዋና ከተማ የአክራ አዉራ መንገድ በከፊል።ጋና ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ካላቸዉ የአፍሪቃ ሐገራት አንዷ ናትምስል Thomas Imo/photothek/picture alliance

 

ዶናልድ ትራምፕ ሥለተፈጥሮ ጥበቃ ብዙ አይጨነቁም።ሥደተኞች ግን ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ጠንካራ ርምጃ ወስደዋል።ዩናይትድ ስቴትስን ከሜክሲኮ ጋር የሚያዋስነዉን ድንበር በግንብ ማሳጠር ጀምረዉም ነበር።በዘንድሮዉም የምርጫ ዘመቻ በሕግ ወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ የገቡ ሥደተኞች ወደየሐገራቸዉ ለመላክ እየዛቱ ነዉ።
አሜሪካዊዉ የፖለቲካ ተንታኝ ቻርልስ ማርቲን እንደሚሉት በተፈጥሮ ሐብትም ሆነ በስደተኞች መርሕ ከአፍሪቃ ጋር ለመስረት የሞከረዉ የባይደን አስተዳደር ነዉ።ትራምፕ ዳግም ከተመረጡ ግን በሁሉቱም መስክ ለአፍሪቃ ብዙም አይጠቅሙም።

ማርቲና ሽቪኮቭስኪ 

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ
                              


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW