1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የምርጫ ማኒፌስቶውን ዛሬ ይፋ አደረገ

ሥዩም ጌቱ
ቅዳሜ፣ መጋቢት 19 2018

በዚሁ የማኒፌስቶ ምረቃ ስነስርዓቱ መድረክ ላይ ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ጌጡ በትብብሩ ማኒፌስቶ ኢትዮጵያ የምትተዳደርበት የፌዴራላዊ ስርዓት ጥያቄ ውስጥ ባይገባም “ቋንቋ እና ዘርን መሰረት ያደረገ” ያሉትን አስተዳደራዊ ስርዓት ግን ተቃውመዋል፡፡

የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት መለያ አርማ
የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት መለያ አርማምስል፦ Coalition for Ethiopian Unity

የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የምርጫ ማኒፌስቶ

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ (አግን)፣ እናት ፓርቲ እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)ን ወደ አንድ መድረክ ያመጣው ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት፤ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ለ2018ቱ የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ማኒፌስቶአቸውን በይፋ አስተዋውቀዋል፡፡

የመሬት አስተዳደር ፖሊሲ

የትብብሩ ምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ምርጫው ስንሻው፤ በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንደነገሩት በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ መሰጠቱን ገልጸው፤ ከነዚህ ውስጥ አንዱ የመሬት አስተዳደር ፖሊሲ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ “ዛሬ መንግስት በሚከተለው ፖሊሲ መሬት የህዝብም ነው፤ የመንግስትም ነው ይላል” ያሉት ኃለፋ፤ ይህ ሁሉንም ነገር የሊዝ (የኪራይ ህይወት) በማድረጉ የህዝቡን የባለቤትነት ስሜት የተነጠቀበት ሁኔታ መለወጥ እንዳለበት እናምናለን ብለዋል፡፡

የፌዴራላዊ አስተዳደር ስርዓት

በዚሁ የማኒፌስቶ ምረቃ ስነስርዓቱ መድረክ ላይ ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነትፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ጌጡ በትብብሩ ማኒፌስቶ ኢትዮጵያ የምትተዳደርበት የፌዴራላዊ ስርዓት ጥያቄ ውስጥ ባይገባም “ቋንቋ እና ዘርን መሰረት ያደረገ” ያሉትን አስተዳደራዊ ስርዓት ግን ተቃውመዋል፡፡ “የጥምረታችን የፌዴራሊዝም አወቃቀር ቋንቋና ዘርን መሰረት ያደረገው የፌዴራሊዝም አወቃቀርን ብቻ ነው የሚቃወመው” በማለት “ሌሎችን በህዝቡ መልካም ፍቃድ ይቀበላል” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በዚህም በመልካዓ-ምድራዊ የፌዴራሊዝም አወቃቀር ለማስተዳደር በፖሊሲያቸው ስለማቅረባቸው አንስተዋል፡፡ ይህንንም በምርጫው የሚመረጡ ከሆነ በዚያን ወቅት በሚወጡ ሕግጋት ውስጥ እንደሚያካትቱ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

ስለትብብሩ ቀጣይነት

አሁን ላይ ለምርጫ 2018 በመጣመር ትብብር የፈጠሩት የአራቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች እጣፈንታ ከምርጫው በኋላስ ምን ይገጥመው ይሆን? ተብለው በጋዜጠኞች የተጠየቁት የትብብሩ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ጌጡ፤ በምርጫ አዋጁ መሰረት ፓርቲዎች ቅንጅት ሲመሰርቱ በጊዜ የተገደቡና ለታወቀ አጀንዳ ብቻ ጥምረት እንዲመሰርቱ የሚፈቀድላቸው በመሆኑ አራቱ ፓርቲዎች ርዕዮተ-ዓለማቸውን ሳይነኩ መጣመራቸውን በመጠቆም ይህም ለውስን ጊዜ የሚቆይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ “ፕሮግራማችን ሳንነካ በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ብቻ ተነጋግረን ተቀናጅተናል” ያሉት ኃላፊው ቅንጅቱ ለተወሰነ አጀንዳ ብቻ ተፈቅዶ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚቆይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ከምርጫው በኋላ የቅንጅቱ ቀጣይ እጣፈንታን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም “ላለፉት ሶስት ዓመታት አገራዊ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ አብረው ሲሰሩ የቆዩት ፓርቲዎቹ በቀጣይ አጀንዳቸው የሚወስኑት ይሆናልም” በማለት ግንባርና ውህደት የመፍጠር እድሉም ግን ዝግ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

እአአ በ2022 በተካሄደ ምርጫ ወላይታ አካባቢ በአንድ የምርጫ ጣቢያ መራጭ ሲመርጥምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

“ስለምርጫው ወሳኝነት”


ለጊዜው ግን የቅንጅቱ ዓለማ ምርጫ ማካሄድ፤ በምርጫው መሳተፍ ነው ያሉት የትብብሩ ፕሬዝዳንት፤ እንደ ትብብሩ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫም በምንም መልኩ “ከምርጫ እንወጣለን የሚል ይዘት ያለው ሃሳብ አልተንጸባረቀም” ብለዋል፡፡ የፀጥታ ችግር ባለበት አከባቢ ለጊዜው በአደባባይ የሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ግን ስለመግታታቸው ተናግረዋል፡፡ ግጭቶች ከኃይል ይልቅ በመነጋገር ብቻ እንዲፈቱ መክረሃሳባቸው እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ንግግር ያደረጉት የትብብሩ ምክትል ፕሬዝዳንት መጋበ-ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት በምርጫ የሚፈጸም ሰላማዊ ትግል የህዝቡ ቆራጥ አቋም ከታከለበት ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አጽእኖት ሰጥተዋል፡፡ “በሰላማዊ ትግል ጠንካራ ሃሳብ ይዘን ህዝባችን እንዲመርጠን ተሰባስበናል” ያሉት መጋበ-ብሉይ አብርሃም፤ “በሁሉም አከባቢ ያለው ህዝብ ምርጫ ካርድ በማውጣት ይምረጠን”…“ሰላማዊ ትግል ከየትኛውም አምባገነናዊ ስርዓት ሲያላቅቅ በብዙ ዓለማት ተተግበሮ አይተናልና በሰላማዊ ትግል ላይ ተስፋ መቁረጥ ይቁም” ሲሉ ማብራሪያቸውን ቋጭተዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW