"ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት" የተባለ የአምስት የፖለቲካ ድርጅቶች ቅንጅት በይፋ ተመሠረተ
ቅዳሜ፣ መስከረም 10 2018
"ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት" የተባለ የአምስት የፖለቲካ ድርጅቶች ቅንጅት በይፋ ተመሠረተ
ለሦስት ዓመት ተኩል በትብብር ሲሠሩ የቆዩ አምስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ዛሬ መስከረም 10 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ቅንጅት መሠረቱ።
"ኢትዮጵያ የህልውና አደጋ ውስጥ ናት" የሚለው ድምዳሜ የቅንጅቱ መመሥረት ዐቢይ መነሻ ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል።
ሰላማዊ ሰልፍን ጨምሮ ሌሎች የሰላማዊ ትግል ስልቶችን እንደሚከተል ያስታወቀው ይህ ቅንጅት አልፎም "በሰላማዊ መንገድ የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት" ጭምር እንደሚሠራ አስታውቋል። ቅንጅቱን የመሠረቱት የፖለቲካ ድርጅቶች የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ እናት ፓርቲ፤ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ናቸው።
የቅንጅቱ ስያሜ ምንድን ነው?
ዛሬ ቅዳሜ መስከረም 10 ቀን 2018 በይፋ የተመሠረተው የ5 ፓርቲዎች ቅንጅት "ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት" ወይም ባጭሩ "ለ ኢትዮጵያ" የተባለ ስያሜ ተሰጥቶታል። ቅንጅቱ የአመራር ምርጫ ማድረጉ የተገለፀ ሲሆን የመኢአድ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ጌጡን ሰብሳቡ አድርጎ መርጧል ተብሏል። የቅንጅቱ የውጭ ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊ የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት አብርሃም ሃይማኖት የመሰባሰባቸውን ዓላማ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
"ኢትዮጵያ የህልውና አደጋ ውስጥ ናት። በዚህ ሰዓት የብሔር ፖለቲካው እየፈተናት ነው። ፈታኝ ነገሮች አሉ። ከዚህ ፈተና ለመውጣት ደግሞ ጠንካራ የሰላማዊ ትግል ያስፈልጋል።"
ለመቀናጀት ዋና መስፈርት የሆኑ ጉዳዮች
ይህ ፓርቲዎችን ያቀናጀው ስብስብ "የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መቀበል፣ ከታሪኳ ጋር ብዙ ጠብ ውስጥ አለመግባት፣ እውነትና መርህ ላይ የተመሠረተ ተቃውሞ" መስፈርት አድርጎ የያዛቸው ነጥቦች መሆናቸውን አስቀድሞ አስታውቋል። የውጭ ጉዳይ ኃላፊው እንዳሉት ቅንጅቱ ሰላማዊ ትግልን እስከመጨረሻው ይከተላል።
የኢትዮጵያ የምርጫ ሥርዓት በርካታ የመራጭ ድምፅ ባክኖ እንዲቀር ያደርጋልቅንጅት መመስረቱ ይፋ በሆነበት ሥነ ሥርዓት ላይ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካዮች ተገኝተዋል ተብሏል። ኢትዮጵያ በአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓትመመራቷ በርካታ የመራጭ ድምፅ እንዲባክን ማድረጉን ከቀናት በፊት ለዶቼ ቬለ የጠቀሱ አንድ የሕግ ባለሙያ "ቅንጅት" ይህንን ለማስቀረት እንደሚያግዝ ገልፀው "ውህደት" ግን በላቀ ለሕዝብ ጥቅም ተመራጭ ነው ብለዋል፣ ምንም እንኳ ያንን ለማድረግ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የሚጠይቅ ቢሆንም።
ሰለሞን ሙጬ
ታምራት ዲንሳ