1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
የፕሬስ ነጻነትኢትዮጵያ

ትናንት ከሥራ ቦታው የተወሰደው የአዲስ ስታንዳርድ ማኔጂንግ ኤዲተር ያለበት አልታወቀም

ሰለሞን ሙጬ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 8 2018

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የአዲስ ስታንዳርድ ማኔጂንግ ኤዲተር ሚሊዮን በየነ ያለበትን ለመለየት እና ነጻ ለማውጣት የአቅማቸውን ጥረት እንዲያደርጉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ ወይም ሲጂጄ ጥሪ አቀረበ። ሚሊዮን ከመሥሪያ ቤቱ የተወሰደው ትላንት ረፋድ እንደሆነ ጃኬን አሳታሚ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አስታውቋል።

አዲስ ስታንዳርድ
ማንነታቸው ባልታወቁ እና ሲቪል የለበሱ በተባሉ ሰዎች ከሥራ ቦታው ትናንት ረፋድ የተወሰደው የአዲስ ስታንዳርድ ማኔጂንግ ኤዲተር ሚሊዮን በየነ እስካሁን ያለበት ቦታ እንደማይታወቅ ተገለፀ። ምስል፦ Eshete Bekele/DW

ሲፒጄ ባለሥልጣናት ጋዜጠኛ ሚሊዮን በየነን ለማግኘትና ለማስፈታት የሚችሉትን እንዲያደርጉ ጠየቀ

This browser does not support the audio element.

የአዲስ ስታንዳርድ መገናኛ ዐውታር ማኔጂንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ሚሊዮን በየነ ትናንት ሚያዝያ 7 ቀን 2018 ዓ.ም. ረፋድ 4፡40 ገደማ "ማንነታቸው ባልታወቁ እና ሲቪል ልብስ በለበሱ ሰዎች ከቢሮው ተወስዶ 24 ሰዓታት ሊሞላው ቢቃረብም እስካሁን ያለበት ቦታ አልታወቀም" ሲል አሳታሚው ጃኬን ፐብሊሺንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዛሬ ሐሙስ አስታውቋል።

ድርጅቱ "በርካታ" ያላቸው ሲቪል የለበሱ ግለሰቦች የአዲስ ስታንዳርድ መሥሪያ ቤት ወደሚገንበት ሕንፃ ተከታትለው ሲገቡ ይታያል ሲል በደኅንነት የምስል መቅጃ - ካሜራ መመልከቱን ገልጧል።

"ቢያንስ ሦስት ባርኔጣና ጭምብል ያደረጉ እና ሌላ ግለሰብ ድርጊታቸውን ሲያቀናጁ ታይተዋል" ያለው ድርጅቱ "ጋዜጠኛው በቡድኑ ታጅቦ ከቢሮው ሲወጣ ይታያል፣ ድርጊቱም በታቀደና በተደራጀ መልኩ" ሲፈፀም ይስተዋላል ብሏል።

የአዲስ ስታንዳርድ ዋና አዘጋጅ ዮናስ ከድር ባልደረባቸው ላይ የተፈፀመው ክስተት አስደንጋጭ መሆኑን ጠቅሶ "ድርጊቱን አጥብቀን እናወግዛለን" ብሏል።

"እስካሁን የት እንዳለ አናውቅም"

የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እና የመሪ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ሚሊዮን በየነ በእነሱ ቁጥጥር ሥር አለመሆኑን እንዳረጋገጡለት የጠቀሰው አሠሪው ድርጅት፣ "ይህ እገታ የተፈጸመው ባለፉት ጥቂት ወራት በአዲስ ስታንዳርድ የዜና ክፍል እና ሥራዎች ላይ ተደጋጋሚና እየበረታ የመጣ የጸጥታና የአስተዳደራዊ ጫናዎች ባሉበት ወቅት ነው" ብሏል።

ዋና አዘጋጁ ባልደረባቸው ከሥራው ጋር በተገናኘ ይህ ድርጊት እንደተፈፀመበት ገልጿል። "ከሥራው ጋር የተገናኘ ነው። ለጥያቄ ትፈለጋለህ" በሚል ነው።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የአዲስ ስታንዳርድን የምዝገባ ምስክር ወረቀት ሰርዟል

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አዲስ ስታንዳርድ "የሚዲያ ሥነ ምግባርን፣ የኢትዮጵያ ሕጎች እና የሀገርንና የሕዝብን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ በማሰራጨት ላይ ይገኛል" ሲል ከየካቲት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የምዝገባ ምስክር ወረቀቱን ሰርዟል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የአዲስ ስታንዳርድን የምዝገባ ምስክር ወረቀት ሰርዟልምስል፦ Ethiopian Media Authority

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (ሲፒጄ) የተሰረዘው የአዲስ ስታንዳርድ የበይነ-መረብ የምዝገባ ምስክር ወረቀት እንዲመለስ በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ጠይቆ፣ ርምጃውን "በኢትዮጵያ ወሳኝ ዘገባዎችን ለማዳከም የታቀደ የተቀናጀ ዘመቻ አካል” ብሎት ነበር። የአዲስ ስታንዳርድ ዋና አዘጋጅ ዮናስ ከድርም በዚሁ ይስማማል።

"ሥራችን ላይ ጫና አለ። ጋዜጠኝነት በተለይ ደግሞ ነጻ ጋዜጠኝነት በርጋታ ዋጋ የሚያስከፍል ነገር ነው፣ ሕዝብን ለማገልገል ስንል ሥራችንን እንቀጥላለን።"

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (ሲፒጄ) ያደረገው ጥሪ

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (ሲፒጄ) በጉዳዩ ላይ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋዜጠኛ ሚሊዮን በየነን "ለማግኘት እና ለማስፈታት የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ" ጥሪ አቅርቧል"

የሲፒጄ አፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋዜጠኛ ሚሊዮን በየነን ማን እንደወሰደው በፍጥነት እንዲለዩ፣ መፈታቱን እንዲያረጋግጡ እና ያንን ያደረጉትን ተጠያቂ ማድረግ አለባቸው።” ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የፌዴራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጄላን አብዲ ጋዜጠኛው በተቋማቸው ቁጥጥር ሥር አለመሆኑን እና ሊነግሩን የሚችሉት አዲስ ነገር እንደሌለ ገልፀዋል።

ጃኬን አሳታሚ "ለሠራተኞቹ ደኅንነት፣ ለፕሬስ ነፃነት እና ለሕግ የበላይነት መርኾዎች" ቁርጠኛ መሆኑን ገልጾ፣ የሚመለከታቸው ያላቸው አካላት "ጉዳዩን የሚመጥን ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡት" ጠይቋል።

ሰለሞን ሙጬ

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW