1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ትኩረት ለአፍሪቃውያን ስደተኞች

ዓርብ፣ የካቲት 10 2015

የእርስ በእርስ ግጭት ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት ፣ የአየርንብረት ለውጥ እና የምግብ ዋስትና መናጋት ያስከተለው ቀውስ አፍሪቃ አይታው ለማታውቀው ስደት እና መፈናቀል አጋልጧታል። ባለፈው የጎርጎርሳውያኑ 2022 ዓ/ም ግንቦት ወር በአፍሪቃ በሀገር ውስጥ ተገደው የተፈናቀሉትን ጨምሮ የተገን ጠያቂዎ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሚሊዮን ተሻግሯል።

Symbolbild Frauen Opfer Konflikt Südsudan
ምስል፦ GetttyImages/AFP/C. Lomodon

«ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ከአፍሪቃ አንጻር መዘናጋቱን ያቁም» የአፍሪቃ የደህንነት ጥናት ተቋም

This browser does not support the audio element.

የእርስ በእርስ ግጭት ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት ፣ የአየርንብረት ለውጥ እና የምግብ ዋስትና መናጋት ያስከተለው ቀውስ አፍሪቃ አይታው ለማታውቀው ስደት እና መፈናቀል አጋልጧታል። ባለፈው የጎርጎርሳውያኑ 2022 ዓ/ም ግንቦት ወር በአፍሪቃ በሀገር ውስጥ ተገደው የተፈናቀሉትን ጨምሮ የተገን ጠያቂዎ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሚሊዮን ተሻግሯል። የመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ግሽበት ፣ የኮቮድ 19 ያሳደረው ማህበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ፣ የኃይል አቅርቦት የዋጋ መናር እና በዩክሬን እየተካሄደ ያለው አስከፊ  ጦርነት በመላው ዓለም ያሳደረው ተጽዕኖ በአፍሪቃ ነገሮችን የከፋ አድርጓቸዋል።በአፍሪቃ ቀንድ ረሃብና ድርቅን መቋቋሚያ ስልት

የዓለማቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመለክተው ከሰሃራ በታች ባለው የአፍሪቃ ክፍል በጎርጎርሳውያኑ 2021 38,3 ሚሊዮን የነበረው የስደተኞች እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር ከአንድ ዓመት በኋላ ከ44 ሚሊዮን በላይ ተሻግሯል።

ምስል፦ Alemenw Mekonnen/DW

ከዚህ አሃዝ ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪቃ እና የአፍሪቃ ቀንድ የታላላቅ ሐይቆች አካባቢዎች የእርስ በእርስ ግጭት እና በአርባ አመታት ውስጥ አስከፊ ነው የተባለለት ድርቅ ለዜጎች መፈናቀል አይነተኛ ሚና ተጫውቷል።

በሩስያ እና ዩክሬን መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት የኃያሉን ሀገራት ትኩረት መውሰዱ ደግሞ አፍሪቃ ውስጥ ያለው ቀውስ እንዲዘነጋ ማድረጉን ነው የተመድ ዘገባ ያመለከተው።  የድርቅ መባባስ ስጋት በአፍሪቃው ቀንድ

በኢትዮጵያ ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ ለተከታታይ ዓመታት ዝናብ ባለመጣሉ ያስከተለው ድርቅ ከ1 ሚሊዮን በላይ የቁም እንስሳት እንዲያልቁ ምክንያት ሆኗል። በደቡብ ሱዳን ደግሞ በተቃራኒው የአየር ንብረት ለውጡ ጎርፍ አስከትሎ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን  ከቤት  ንብረታቸው አፈናቅሏል።

ምስል፦ Kossivi Tiassou/DW

በደቡባዊ፣ መካከለኛው እና ምዕራብ አፍሪቃም እንዲሁ በተመሳሳይ ግጭት እና የአየር ንብረት ለውጥ  ባስከተለው ድርቅ የእርዳታ ፈላጊው ህዝብ ቁጥር አህጉሪቱ በታሪኳ አይታ በማታውቀው መጠን አሻቅቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የዩክሬን ጦርነት የአለማቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት መውሰዱ አፍሪቃ ውስጥ ያለው ቀውስ ተገቢውን ድጋፍ እንዳያገኝ አድርጓል ሲል ሰሞኑን የአፍሪቃ የደህንነት ጥናት ተቋም  ያወጣዉ ዘገባ ያሳያል።

ምስል፦ Amanuel Sileshi/AFP

የዓለማቀፉ የሰብአዊ ጉዳዮች የበላይ ሃላፊ ማይክ ግሪፊትስ  በድርቅ የተመታውን የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ በጎበኙበት ወቅት ዓለም ፊቱን ወደ አፍሪቃ እንዲያዞር ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፈው ነበር።የምግብ ዋጋ መናር በአፍሪቃ

«እኔ እዚህ የመጣሁት ፣ የተቀረው ዓለም እዚህ ላለው ቀውስ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጥ ነው። የዓለማቀፉ ማህበረሰብ ትኩረቱን በቀውስ ውስጥ ባለችው ዩክሬን ላይ አድርጓል። ነገር ግን እዚህ ያለው ቀውስ ቢበልጥ እንጂ አያንስም ። »

ቀናት ለሳምንታት ፣ ሳምንታትም ለወራት ጊዜውን አሻገሩ ፤ ስደት ፣ መፈናቀል እና ተያይዞ የተከሰቱ ማህበራዊ ቀውሶች ዛሬም የለጋሾችን ደጅ ይጠናሉ፤ የኦለም አይን እና ጆሮ ግን ከአድማስ ወዲህ ማዶ አልሻገር አለ ።

ለወትሮም አፍሪቃ ውስጥ ያሉ ማህበራዊ ቀውሶችን በገንዘብ ለመደገፍ ስር የሰደዱ እና በርካታ ውስብስብ ችግሮች ይቀርቡባቸው ነበር። የዩክሬን ጦርነት ሲከተል እና የእርዳታ እጆች መታጠፍ ሲጀምሩ ግን ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ አደረጉት ።

ምስል፦ Ina Fassbender/AFP/Getty Images

ወ/ሮ ፓቪን ኒጋላ የምስራቅ መካከለኛው እና የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ የቀጠናው የኦክስፋም ኃላፊ ናቸው። አስከፊውን ድርቅ ሲገልጹ ። «ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዚህ አካባቢ ያየነው ሁኔታ ባለፉት አርባ ዓመታት ያልተከሰተ ድርቅ ነው የተከሰተው ። ይህ ደግሞ ሁኔታዎች እጅግ አባብሷቸዋል። የአየር ንብረት ለውጡ የሰው ልጅን እየተበቀለ ያለ ነው የሚመስለው።»13 ሚሊዮኖችን ለረሐብ ያጋለጠው ድርቅ

ከአፍሪቃ የደህንነት ጥናት ተቋም ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ስደት መፈናቀሉ የበረታባት አፍሪቃ ከለጋሽ ሃገራት እና ተቋማት ትኩረት በማጣቷ ብቻ በተጠናቀቀው የጎርጎርሳውያኑ ዓመት ግብረሰ ሰናይ ድርጅቶች በዕለት ደራሽ የዕርዳታ ስራቸው ላይ እክል ፈጥሮባቸዋል። የምግብ እና የንጹህ መጠጥ ዉሃ  አቅርቦቱን ለመቀነስ ተገደዋል፤ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ደግሞ እስከ ከ50 በመቶ በላይ እንዲቀንሱ መገደዳቸውን ነው የተቋሙ ሪፖርት ያመለከተው።

ባለፈው የጎርጎርሳውያኑ 2022 በዓለማችን ከተመዘገቡ 10 አስከፊ የሰብአዊ ቀውሶች 10ም  አፍሪቃ ውስጥ መገኘታቸው የዓለም ጆሮ ዳባ ልበስ እስከ መቼ ሲል  የደህንነት ተቋሙ ሪፖርት ይጠይቃል። የመገናኛ ብዙኃን ሚና እና የመንግስታት በጎ ምላሽ የተወሳሰበው የአፍሪቃውያን ስደተኞች ቀውስ እንዲረግብ አንዱ የመፍትሄ አካል እንደሆነም ያስረዳል።የአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂዎች በአፍሪቃ

ምስል፦ Mariel Müller/DW

ምዕራባውያኑ ለዩክሬን ጦርነት ያሳዩትን ርብርብ ያህል ጥቂት ስለ አፍሪቃ ስደተኞች የመፍትሄ መንገድ ማመላከት ቢችሉ ፤ ሲል ምክረ ሃሳብ የሚያቀርበው ተቋሙ ፤ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ፤ ስደተኛ ተቀባይ እና ለውስጥ ፍልሰት ተጋላጭ ሃገራት ከባለድርሻ አካላት ጋር የተናበበ እና ውስብስቡን ቀውስ በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ስልት መንደፍ ይጠበቅባቸዋል ሲልም አስገንዝቧል። 

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሰ

 

 

 

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW