1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ትኩረት በአፍሪቃ፤የማላዊ ነርሶች በእስራኤል እንዲሰሩ የተደረሰው ስምምነት እና የኮንጎ ቀውስ

ፀሀይ ጫኔ
ቅዳሜ፣ ግንቦት 23 2017

የማላዊ ነርሶች ወደ እስራኤል ሂደው እንዲሰሩ የሀገሪቱ መንግስት ከእስራኤል ጋር ስምምነት ፈርሟል፤ ስምነቱ በሀገሪቱ ድጋፍ እና ተቃውሞ ገጥሞታል። በሌላ በኩል በዲሞክራቲክ ኮንጎ የቀድሞው ፕሬዚዳንት የጆሴፍ ካቢላ አማፅያንን መቀላቀላቸው የሀገሪቱን ሰላም አደጋ ላይ ይጥላል በሚል ስጋት አሳድሯል።

Malawi Cholera-Epidemie
ምስል፦ Thoko Chikondi/AP Photo/picture alliance

ትኩረት በአፍሪቃ፤የማላዊ ነርሶች በእስራኤል እንዲሰሩ የተደረሰው ስምምነት እና የኮንጎ ቀውስ

This browser does not support the audio element.

የጤና እንክብካቤ ባለሙያዎች በፍተኛ ደረጃ ስራ አጥ በሆኑባት በማላዊ እና በእስራኤል መካከል የሰለጠኑ ነርሶችን እና አዋላጆችን ወደ እስራኤል የጤና ተቋማት ለመላክ  ስምምነት  አድርገዋል።የማላዊ መንግስት እንደገለፀው በሚያዚያ  ወር የተፈረመው የሁለትዮሽ ስምምነት ለማላዊ የጤና ባለሙያዎች ስራ እና  አዳዲስ ክህሎቶችን እንዲያገኙ እንዲሁም  ቤተሰቦቻቸውን  በገንዘብ መደገፍ እንዲችሉ ይረዳል።ይህ ስምምነት እንደ ክርስቲና ጄሬ ላሉ በጉጉት ለሚጠብቁ ስራ አጥነት የማላዊ ነርሶች እድል ይሰጣል። «በእርግጠኝነት እሄዳለሁ።ለሦስት ዓመታት ያህል ሰልጥኛለሁ ።ብቁ ነኝ።  ለቃለ መጠይቅ እንኳን አልተጠራሁም። አዎ ማላዊ ቤቴ ነው።ነገር ግን ሥራ ማግኘት ሳልችል ብዙ የኮሌጅ ክፍያ ባወጣሁበት አገር ለምን እቆያለሁ?።» ብላለች። ሌላዋ የሰለጠነች ነርስ ኤልዛቤት ጎንድዌ ተመሳሳይ ምኞት አላት። «በማላዊ መንግሥት ሳልቀጠር ለረጅም ጊዜ ቆይቻለሁ። ስለዚህ ከእስራኤል መንግሥት ጋር በተደረገው በዚህ ስምምነት በጣም ተደስቻለሁ። ምክኒያት እዚ ማላዊ ውስጥ  ኑሮ በጣም ውድ ነው። ስለዚህ ዘመዶቼን እና ቤተሰቤን መርዳት አልቻልኩም። ስለዚህ ይህ ለእኔ ታላቅ እድል ነው።» 

ትችት በማላዊ-እስራኤል የጤና አጠባበቅ ሰራተኞች ስምምነት ላይ 

ያም ሆኖ የተካኑ የጤና ባለሙያዎችን ወደ ውጭ የመላክ ሀሳብ ሁሉንም ሰው ሊያስደስት አልቻልም። በጎርጎሪያኑ 2023 ዓ/ም በተደረገ ተመሳሳይ ስምምነት ማላዊያውያን በእስራኤል የግብርና ዘርፍ ለመስራት ሄደው ነበር።በዚህ  ወቅት ታዲያ በማላዊ ሰራተኞች ላይ የጉልበት ብዝበዛ፣ ደካማ የስራ ሁኔታ እና የስራ ውላቸውን በመጣስ ከሀገር እንዲባረሩ ተደርገዋል የሚሉ ዘገባዎች በመውጣታቸው ቅሬታ ተፈጥሮ ነበር።በተጨማሪም ተቺዎች እንደሚሉት  የማላዊ የጤና ስርዓት የሰለጠነ ባለሙያ ችግር  ያለበት በመሆኑ ፤የሰለጠኑ ሰዎችን ማጣት ተገቢ አይደለም ይላሉ። የማሊ የሀኪም እና ታካሚ ጥምረታ፤ በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) ከሚመክረው አንድ ሀኪም ለ1,000 ታካሚዎች በአንድ ሦስተኛ ያህል ያነሰ ነው።ስምምነቱ የበማላዊ መንግስት እንደ ድል የታየ ቢሆንም፤ ታዛቢዎች የማላዊ ዜጎችን ጥቅም ከግምት ውስጥ ከማስገባት ይልቅ እንደ ፖለቲካዊ እርምጃ በመመልከት የመንግስትን ዓላማ በጥርጣሬ እያዩት ነው።

በተጨማሪም ማላዊ እስራኤልን በተመለከተ የምትከተለው ፖሊሲ፤ በደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማህበረሰብ (SADC) ውስጥ ካሉት ሌሎች አገሮች አዝማሚያ ጋር አይጣጣምም። በተለይም ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በሃማስ ላይ ባካሄደችው ጦርነት በጋዛ የጦር ወንጀሎች ተፈፅመዋል በማለት የእስራኤል አመራርን  ተችታለች። በአንፃሩ ማላዊ በ2024 በቴል አቪቭ ኤምባሲ የከፈተች ሲሆን፤ በእስራኤል ዘንድም ጠንካራ አጋር ሆና ትታያለች።በአጠቃላይ የማላዊ መንግስት ብዙ ወጭ በማውጣት ያሰለጠናቸውን የጤና ባለሙያዎች ችሎታቸውን እና እውቀታቸውን ይዘው ወደ ውጭ አገር እንዲሄዱ ሲበረታታ ማየት፣ በማላዊ ውዝግብ ቀስቅሷል።በሌላ በኩል ማላዊ ውስጥ በመስራት ላይ የሚገኙት ሜርሲ ምዋሊሊኖ ለDW  እንደተናገሩት አንዳንድ ነርሶች በቀን የሚያገኙት 3,453 የማላዊ  ገንዘብ /ክዋቻ/ ወይም ($2፣ €1,75) ብቻ ነው። ያም ሆኖ  በማላዊ የጤና አጠባበቅ ስርዓት ውስጥ እንደ ምዋሊሊኖ ስራ ያገኙት ነርሶች ሩብ ያህሉ ብቻ ናቸው።

የማላዊ የጤና አጠባበቅ ሠራተኞች በእስራኤል ምን ይገጥማቸዋል?

በሌላ በኩል ለማላዊ ሰራተኞች ተገቢው ጥበቃ እየተደረገላቸው ስለመሆኑ እና በእስራኤል ውስጥ ስላለው የሥራ ሁኔታ አሳሳቢ ጉዳዮች ተነስተዋል። የማላዊ የግብርና ሰራተኞች ወደ እስራኤል የላከው ድርጅት ሰራተኞቹ ስለአስቸጋሪው የስራ ሁኔታቸው ቅሬታ ካቀረቡ እና ስራቸውን ለቀው መደበኛ ባልሆነው ዘርፍ ለመስራት ወይም በእስራኤል ጥገኝነት ከጠየቁ በኋላ ስራውን አቁሟል። ለሜርሲ ምዋሊሊኖ ግን በእስራኤል እና በማላዊ መካከል የተደረገው የሁለትዮሽ ስምምነት የደህንነት ስሜት ይፈጥራል።«የማላዊ መንግስት ይህንን ስምምነት ከማላዊ የነርሶች እና አዋላጆች ብሄራዊ ድርጅት ጋር በማጣመር እያጠናቀቀ ነው፣ እሱም ነርሶቹን ወደዚያ ከመላካቸው በፊት እነዚያን ሁሉ ሁኔታዎች የመመልከት ኃላፊነት አለበት።»ብለዋል።ወደዚያ መሄድ የሚፈልጉ ባለሙያዎች ከ200 እስከ 300 የአሜሪካን ዶላር እንደሚያገኙ ገልፀዋል።አደገኛ በሆነው የእስራኤል ክፍል ጦርነት ባለበት ቦታ ሊሰሩ ስለሚችሉ የማላዊ ዜጎች ሁኔታ ሲጠየቅ፣ ይህ አሳሳቢ መሆኑን  ሙዋሊኖ አምኗል።ስለሆነም «በደህንነት ስጋቶች ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ ያሉ ሰዎች ለመሄድ አይገደዱም።» ብለዋል።

የማላዊ ነርሶች ወደ ሀገራቸው ይመለሱ ይሆን?

እንደ ኢስተር ማላንጋ ላሉ  ተቀጣሪዎች ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅ መስራት ባህል እና አካባቢም ፈታኝ ሊሆን ይችላል።«ከአዲስ ቋንቋ፣ ባህል እና የስራ አካባቢ ጋር መላመድ ፈታኝ ሊሆን ይችላል፣ እና በግል ህይወቴ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል። መጀመሪያ ላይ በእስራኤል ከአንድ እስከ ሁለት አመት ለመስራት አስባለሁ።».ብለዋል።የማላዊ ባለስልጣናት ውሉ ሲያልቅ ተመልሰው ወደ ሀገራቸው የሚመጡ ነርሶች እና አዋላጆች በእስራኤል ቆይታቸው ጥሩ ችሎታ ይዘው ይመለሳሉ በማለት ፖሊሲውን አወድሰዋል።

እስራኤል ቴል አቪብ የሚገኘው የሶራስኪ የህክምና ማዕከልምስል፦ polk430/Depositphotos/IMAGO

ለማላንጋም ይህ ማራኪ የሆነ አማራጭ ነው።«ወደ እስራኤል መሄድ የታካሚ እንክብካቤን ለማሻሻል እና  ስለተለያዩ የጤና ሥርዓቶች፣ አቀራረቦች እና ቴክኖሎጂዎች ለማወቅ እና ወደ ማላዊ ለማምጣት ይረዳኛል" ስትል ለDW ተናግራለች።»ያም ሆኖ ስንደ ክርስቲያና ጃሬ ያሉ ነርሶች ወደ ማላዊ ስለመመለሳቸው እርግጠኞች አይደለሉም።«ወደ እስራኤል መሄድ አስደሳች ነገር ነው፣ እና ተመልሼ የምመጣ አይመስለኝም።» በማለት ገልፃለች።

የጆሴፍ ካቢላ ወደ ኮንጎ መመለስ ጨዋታ ቀያሪ ነውን?  

በኤም 23 የሚመራው አማፂ ቡድን  የቀድሞ የኮንጎ መሪ ጆሴፍ ካቢላ በእነሱ ቁጥጥር ስር በምትገኘው ጎማ  ደህንነታቸው ተጠብቆ እንደሚገኙ ገልጿል።  ካቢላ የፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲ መንግስትን በመተቸት ዳግም ወደ  ስልጣን የመመለስ  አዝማሚያ እያሳዩ ነው። የኮንጎ ወንዝ አሊያንስ (ኤኤፍሲ) እና ኤም 23 አማፂ ቡድኖችጆሴፍ ካቢላ የኮንጎ መንግስት ሃይሎች ሊያገኟቸው  በማይችልበት ሁኔታ በጎማ እንደሚገኙ ገልፀዋል።በጎርጎሪያኑ  ከ2001 እስከ 2019 የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ (ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ) መሪ ሆነው ያገለገሉት ካቢላ በአንድ ወቅት የወቅቱ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲ ጠንካራ አጋር ፤የኤም 23  አማፂ ቡድን ደግሞ ነቃፊ ነበሩ።

ነገር ግን ካቢላ በ2019 ከስልጣን ሲወርዱ "የእድሜ ልክ ሴናተር" ተብለው የነበረ ቢሆንም፤ የቲሴኬዲ መንግስት የካቢላን ያለመከሰስ መብት ለማንሳት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ።በሁለቱ ወገኖች መካከል መቃቃር ተፈጠረ። ካቢላም የቲሴኬዲ መንግትን በይፋ መተቸት ጀመሩ።አንዳንድ የፖለቲካ ታዛቢዎች የካቢላ በአማፅያን ቁጥጥር ስር ባለ ቦታ እንደገና መታየታቸው በሃይማኖት መሪዎች እየተመሩ ያሉትን የሽምግልና ጥረቶች አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ብለዋል።ሆኖም የግጭት አፈታት ባለሙያ  የሆኑት ኤሎዲ ንታሙዚንዳ ካቢላን ወደ ጎን ማድረግ  ጥቅም  የሌለው መሆኑን ለDW ተናግረዋል።የኮንጎ አብዮት መፅሀፍ ደራሲ ኢቦን ሙያ የመንግስት ምላሽ የተጋነነ ነው ይላሉ። «ለካቢላ መመለስ የመንግስት ምላሽ የተጋነነ ይመስላል።ይህ በመንግስት እና በተቃዋሚ ዎች መካከል ባለው ግንኙነት ውስጥ አደገኛ ቅድመ ሁኔታን ያስቀምጣል።እኛ ጦርነት ውስጥ ነን።እና ፕሬዚዳንቱ ሀገሪቱን አንድ ለማድረግ እየሞከሩ ነው።የፖለቲካ ስርዓቱን አንድ ክፍል በማስቀረት ሀገሪቱን አንድ ለማድረግ መሞከር ጥሩ መንገድ ነው ብዬ አላምንም።» ሲሉ ተናግረዋል።

የቀድሞው የኮንጎ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ እና የወቅቱ ፕሬዚዳንት ፊሊክስ ትሺሴኪዲ በ2019 ስልጣን ሲረካከቡ። ምስል፦ Jerome Delay/dpa/picture alliance

በኪንሻሳ የሚገኘው ኢቡቴሊ የምርምር ተቋም የፖለቲካ ዳይሬክተር ትሬሶር ኪባንጉላ ፤መንግስት አደጋውን ለመከላከል እየሞከረ ቢሆንም፤ካቢላ መንግስትን እንደ ጥላ የሚከተል ሀይል ነው  ሲሉ ገልፀውታል።ከዚህ አንፃር የኮንጎ መንግስት ካቪላ የተቀላቀሉትን የኤም 23 አማፅያንን ለመደራደር እንደሚፈልግ ሲገልፅ ቆይቷል።ነገር ግን እንደ ኪንሻሳው ነዋሪ ጆሴብ ካላላ ያሉ ኮንጓውያን የመንግስትን ሀሳብ ብዙ አይደግፉትም።«ፕሬዚዳንቱ ከዓመት በፊት ወስኗል።ከእነሱ ጋር አልደራደርም ብሏል።ከሌቮች እና ከገዳዮች ጋር በቼም አልደራደርም ብሏል። ዛሬ ከእነዚህ ሰዎች ጋር መደራደር ከፈለገ፤ ወደ የት እየሄድን ነው?ለምን ይህንን ተቀበለ?ለጎንጎ ህዝብ ህይወትስ ምንድነው የሚያመጣው?»ብለዋል።በአማፂያን ቁጥጥር ስር ባለችው ቦካቡ ነዋሪ የሆኑት ፋዲል ሙቦሌ ግን ችግሩ በውይይት ይፈታ ባይ ናቸው።«እንደ አፍሪካዊ  ችግር ሲኖርብን፤ የቤተሰብ አባላት በጠረጴዛ ዙሪያ እንቀመጣለን።እንደ ማህበረሰብ ለገጠመን ችግር መፍትሄ ለመፈለግ እንወያያለን።ለዚህም ነው የተለያዩ ፓርቲዎች ወደ ንግግር ጠረጴዛ እንዲመጡ ጥሪ የምናደርገው።እንደ ኮንጓዉያን ስለኮንጎ እና ስለገጠሙን ወቅታዊ ችግሮች ለማውራት።»

የሞቡቱ ሴሴ ሴኮ አምባገነን መንግስትን የተቃወሙት፤የሟቹ የኮንጎ ፕሬዝዳንት ሎረን ዴሲር ካቢላ ልጅ እንደመሆናቸው መጠን፤ ጆሴፍ ካቢላ የወጣትነት ዘመናቸውን ያሳለፉት በታንዛኒያ ነው። ከዚያ በኋላ በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ አባታቸው የሚመሩት የአማፂው የኮንጎ-ዛየር ነፃ አውጪ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረት  (AFDL) ወታደራዊ መሪ ነበሩ።የካቢላ አማፂ ቡድን  ከሌሎች ጋር  በመሆን፤በጎርጎሪያኑ 1997 የሞቡቱ መንግስትን ሲያስወግድ፤ተጨማሪ የውትድርና ስልጠና በመውሰድ ወጣቱ ካቢላ በኮንጎ ጦር ሃይሎች (FARDC) ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያዙ።የካቢላ የፕሬዚደንትነት ዘመንበጎርጎሪያኑ ጥር 16 ቀን 2001 ዓ/ም የተፈፀመውን የአባታቸውን የሎረን ካቢላ ግድያ ተከትሎም  የ29 ዓመቱ  ጆሴፍ ካቢላ የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ጨበጡ። ካቢላ በወቅቱ  ጦርነት ውስጥ የነበረችውን እና በማዕድን የበለፀገችውን ሀገር  የኮንጎ ፕሬዝዳንት ለመሆን ፈቃደኛ እንዳልነበሩ ይነገራል።ግጭቱ፤ በመንግስት ደጋፊ ኃይሎች እንዲሁም እንደ አንጎላ፣ ዚምባብዌ እና ናሚቢያን የመሳሰሉ አለም አቀፍ አጋሮች እና በሩዋንዳ ከሚደገፉት እና በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ትላልቅ ግዛቶችን ከያዙ ተዋጊዎች ጋር በሰፊው የሚካሄድ ነበር።

ሎረን ዴሲሬ ካቢላ፤ማቹ የዲሞክራቲክ ኮንጎ የቀድሞ መሪምስል፦ picture-alliance/AP/D. Guttenfelder

ካቢላ በጎርጎሪያኑ፤ 2006 በተካሄደው ምርጫ አሸንፈው ኮንጎን እስከ 2018 ዓ/ም መርተዋል።በስልጣን ዘመናቸው የተረጋጋ መንግስት እንዲኖር ለማድረግ የሚከሩ ቢሆንም፤  በብቃት ማነስ፣ አድልኦ እና ሙስናን በመሳሰሉ ውንጀላዎች የስልጣን ዘመናቸው እንዲያበቃ ምክንያት ሆኗል። በካቢላ የስልጣን ዘመን ሀገሪቱን ለውጭ ባለሃብቶች መክፈት እና ኢኮኖሚ ማሳደግን የመሳሰሉ አንፃራዊ ስኬቶች ቢኖሩም አብዛኛው የኮንጎ ህዝብ ከድህነት ወለል በታች ቀርቷል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የንግድ አጋሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ  የሀገሪቱን የማዕድን ሀብት ከአገሪቱ ተነቅሎ ወደ ውጭ እንዲወጣ በማድረግም ይተቻሉ።በ2011 በተካሄደው ምርጫ ካቢላ በስልጣን ላይ እንዲቆዩ አድርጓል፣ ነገር ግን ተቃናቃኞቻቸው እየበዙ መጡ። አሁን ተቀላቀሉት የተባለው  እና  ሩዋንዳ የሚደገፈው ኤም 23 ያሉ አማፂ ቡድኖች እንደገና ብቅ አሉ። በካቢላ አስተዳደር ላይ የተነሱ ተቃውሞዎች እና ራስን የማበልጸግ ትችት ብዙ ጊዜ በኃይል ለመቀልበስ ተሞክሯል። የካቢላ የስልጣን ዘመን በ2016 ሲያልቅ ምርጫውን እስከ 2018 በማዘግየትም በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ብርቱ ትችት ገጥሟቸዋል።በተጨማሪም በኮንጎ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ሊቋቋሙት የማይችሉት እየሆነ  ነበር።በዚህ የተነሳ፤በጎርጎሪያኑ 2019 ዓ/ም በተደረገ ምርጫ ካቢላ በሰላማዊ መንገድ ሥልጣናቸውን ለፌሊክስ ቲሺሴኬዲ አስረከበዋል። ምንም እንኳን ታዛቢዎች በምርጫው ውጤት ላይ እምነት ባይጥሉም፤ ካቢላ ግን ከፖለቲካው ያፈገፈጉ መስለው ታይተዋል።

የቀድሞው የዲሞክራቲክ የኮንጎ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላምስል፦ Luis Tato/AFP

የቀድሞው እና የወቅቱ የጎንጎ ፕሬዚዳንቶች መቃቃር 

በ 2020 ዓ/ም ግን ሁለቱ ወገኖች በመቃቃራቸው በፖለቲካ ፓርቲዎቻቸው መካከል ያለው ትብብር አበቃ። ከ 2023 ጀምሮ የቲሺሴኪዲ አገዛዝ ካቢላን ከኤም 23 አማፂ ጋር ወግኗል ሲል ከሷል። በዚህ ምክንያት ፕሬዚዳንት ቲሺሴኪዲ፤ የካቢላን ህዝብ ለተሃድሶ እና ለዲሞክራሲ ፓርቲን ያገዱ ሲሆን የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ያለመከሰስ መብትም አንስተዋል።የ53 ዓመቱ ካቢላ ያለመከሰስ መብታቸው ከተነሳ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅርቡ በበይነመረብ በለቀቁት ቪዲዮ ዝምታውን ሰብረዋል።በዚህ ቪዲዮም፤የቲሺሴኪዲ አመራር በሙስና፣ ዲሞክራሲን በማናጋት እና በኮንጎ በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ግጭቶችን በአግባቡ አለመያዙን ተችተዋል።«አምባገነኑ ሥርዓት ማብቃት አለበት፣ ዴሞክራሲና መልካም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አስተዳደር መመለስ አለባቸው።» ብለዋል።አንዳንድ የኪንሻሳ ነዋሪዎች ግን የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ርምጃ ተችተዋል።«በጣም ያሳዝናል።የሴናተር ኮፍያ ለብሰው ለ18 ዓመታት ሀገር የመሩት የቀድሞ  ፕሬዚዳንት የነፃነት መፈክር ይዘው ምስኪኖችን በሚገድል አማፂ ቡድንን ሲመሩ ማየት።ብቸኛው ዓላማ ደግሞ ስልጣን መልሶ ለማግኘት ነው።» ብለዋል።

የካቢላ ተጽእኖ እየቀነሰ ነው?

በ 2025 የካቢላ ከኮንጎ መንግስት ጋር ያላቸው ግንኙነት ይበልጥ ሻክሯል። "በሀገሪቱ ዛሬ ለካቢላ ጠንካራ ናፍቆት የለም" ሲሉ የፖለቲካ ተንታኝ ኪባንጉላ ተናግረዋል። ቢሆንም፣ ትሴኪዲ ካቢላ ከM23 አማፂ ጋር “አመጽ” እያሴረ ነበር በማለት ክሱን አፋፍሟል። በምስራቅ ኮንጎ የኤም 23 ወታደራዊ ስኬት ባለድርሻ አድርጎም ይመለከተዋል።.የቲሽሴኪዲ ገዢ ፓርቲ UDPS አባል ዴኦ ቢዚቡ ካቢላን በግብዝነት ከሰዋል። ቢዚቡ ለDW እንደተናገሩት "ይህ እብደት ነው እራሱን እንደ አይበገሬ ሰው ለማየት እየሞከረ፣ ነው። ካቢላ ወደ ስልጣን ለመመለስ  6 አመታትን በሙከራ አሳልፏል።"ጊዜው እንዳለቀ ሊረዳው ይገባል."በማለት ገልፀዋል።የግጭት ተንታኝ ፊሊፕ ዱዱ ካጋንዳ ለDW እንደተናገሩት የካቢላ መመለስ የኮንጐን አንድነት አደጋ ላይ ይጥላል።

በሌላ በኩል የቲሺሴኪዲ መንግስት ለምስራቅ ኮንጎ አለመረጋጋት ሩዋንዳን ለመወንጀል ሞክሯል።ሩዋንዳ ውንጀላውን አስተባብላ ኮንጎዎች የጸጥታ ችግሮቻቸውን ራሳቸው መፍታት አለባቸው ስትል ሞግታለች።በሩዋንዳ የሚደገፉት የኤም 23 አማፂዎች በምስራቅ ኮንጎ የሚገኙ አናሳ  ቱትሲዎችን ለመታደግ  እንደሚታገሉ ይገልፃሉ።ያም ሆኖ ሩዋንዳ ቀውሱን በአካባቢው ያለውን የማዕድን ሀብት ለመመዝበር  እየተጠቀመችበት ነው በሚል ትተቻለች። 

ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW