ትኩረት በአፍሪቃ፤ የሊቢያ መቅሰፍት፤ የጊኒ ቢሳዉ ነፃነት
ቅዳሜ፣ መስከረም 12 2016
የሊቢያን የባሕር ዳርቻ ዉብ ከተማ ደርናን በቅፅበትና ላፍታ ከጎረቤትዋ የሜድትራኒያን ባሕር ጋር ካመሳሰለት 10 ቀን አለፈ።ዉኃ!!! ዉኃ የነዋሪዎችን ዉላጅ፣ዘመድ ወዳጅ፣ ሐብት ንብረት አጥፍቶ ጭቃ፣ዝቃጭና ትቢያዉን ከምሮ-ጎደል፣ ገሸሸ፣ገለል ፈሰስ ከማለቱ አሁን ቀሪዎች በድንጋጤ፣ ሐዘን-ይቆራመዱ፣ በንዴት እልሕ ብስጭት ይንተከተኩ ያዙ።
«ሊቢያዎች አሁን ድንጋጤ ላይ ናቸዉ።ሐዘን ላይ ናቸዉ።ይሁንና ድንጋጤ-ሐዘኑ በረድ-ሰከን ሲል በባለሥልጣናቱ ላይ ያለዉ ቁጣ ይንራል።ባለስልጣናቱ አደጋዉን ለመከላከልና ከደረሰ በኋላም ሰዎችን ለማዳን አለመጣራቸዉ ሕዝቡን አስቆጥቶታል።ቁጣዉ በተለይ ኸሊፋ ሐፍጣር በሚያዙት የሊቢያ ብሔራዊ ጦር ላይ የመረረ ነዉ።»
ይላሉ በአዉሮጳ ምክር ቤት የዉጪ ግንኙነት የፖለሲ አጥኚ ታሬክ ሜገሪሲ።
በኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ያገዛዝ ዘመን ሊቢያዎችን ነፃ ሊያወጡ አሜሪካ መሽገዉ፣ ለአሜሪካኖች ሲሰልሉ፣ በአሜሪካኖች ገንዘብ ሲንደላቀቁ የነበሩት ኸሊፋ ሐፍጣር ለሊቢያ በጣሙን ለምስራቅ ሊቢያዎች የዘራፊ፣ገዳይ፣ አሰቃዮች አዉራ ከሆኑ 11 ዓመት ደፈኑ።የደርና ሕዝብ ሙቱን ቀብሮ፣ ቁስለኛዉን ቆጥሮ፣የጠፋ ሐብት ንብረቱን አስልቶ ሳያበቃ አሁን እንኳን የሐፍጣር ወታደሮች ርዳታ አቀባዮችን ሳይቀር ያሰቃያሉ።የርዳታ ቁሳቁሶችን ይዘርፋሉ።«ከአደጋዉ የተረፉትን ሰዎች ሳይቀር ይዘርፋሉ» ይላሉ ታሪክ ሜገሪሲ
«የአደጋ ሠራተኞችን ያዋክባሉ። ርዳታ እንዳይደርስ ይከለክላሉ።የርዳታ ቁሳቁስ ይሰርቃሉ።ከአደጋዉ የተረፉ ሰዎችን ይመዘብራሉ።»
ምሥራቅ ሊቢያዉያን በሐዘን፣ሰቀቀን፣ የልብ ስብራቱ መሐል የአካባቢዉን ባለስልጣናት ባደባባይ ሰልፍ ሲያወግዙ የስደተኞች ወላጅ፣ወዳጅ ዘመዶች ግን ይቀብሩት አስከሬን፣ ያሳክሙት ቁስለኛ፣ ይዳብሱት ተራፊ አጥተዉ----እንዲያዉ በሩቅ-ርቀት «እሕሕ» እንዳሉ ነዉ።የጎርፍ አደጋ በሊቢያ፤ የአደጋዉን መጠን መቀነስ ይቻል ነበር?
ግብፃዊቱ ወይዘሮ አይሻ አል-ዓለም የመጀመሪያ ልጃቸዉን ወግ-ማዕረግ ሊያዩ ቀን እያሰሉ ነበር። ከሁለት ወር በኋላ እንዲያገባ አንዲቱን ቆንጆ አጭተዉለታል።ልጅ፣ ለጥሎሹም፣ለድግሱም፣ ደግሞ ለጎጆ መዉጪያም ትንሽ ልስራ ብሎ ወደ ምስራቅ ሊቢያ ወረደ።«ድምፁም የለም» አሉ እናት አይሻ እንባ እየተናነቃቸዉ፤ «10 ቀን አለፈዉ» አከሉ ከትናንት በስቲያ።
ሊቢያ፣ ለአፍሪቃ፣ ለአረብ፣ ለእስያ ስደተኞች መስሪያም፣ መኖሪያም ከሁለቱም በላይ ወደ አዉሮጳ መሸጋገሪያ ሐገር ናት።ከጎርፉ በፊት ምስራቃዊ ሊቢያ ዉስጥ 230 ሺሕ ስደተኞች እንደሚኖሩ ይገመታል።ደርና ከተማ ብቻ 80 ሺሕ ስደተኛ ነበር።በአደጋዉ መሞታቸዉ ከተረጋገጠዉ 11 ሺሕ ሰዎች፣ ያሉበት ከማይታወቀዉ 10 ሺሕ ዉስጥ በትንሽ ግምት 4 ሺዉ የዉጪ ስደተኞች ናቸዉ።በሊቢያ የጎርፍ አደጋ ዐሥር ሺህዎችን ቀጠፈ
በትክክል የቆጠረዉ ግን የለም።እስካሁን አስከሬናቸዉ ከተገኘዉ 500 ስደተኞች ዉስጥ 276ቱ የሱዳን፣6ቱ የባንግላዴሽ፣ 110ሩ የሶሪያ ዜጎች መሆናቸዉን የተለያዩ ድርጅቶች አስታዉቀዋል።የተቀሩትን በቅጡ የለየ፣ የቆጠረ በወጉ የቀበራቸዉም የለም።እሱ ግን ተርፏል።
ማን ይናገር-የነበረ
«ስሜ መሐመድ አብዱልራብ ነዉ።የኢድሊብ፣ ሶሪያ ተወላጅ ነኝ።28 ዓመቴ ነዉ።ደርና ከተማ ዉስጥ ነበርኩ።በጎርፉ በመጎዳቴ አሁን ቤንጛዚ ሆስፒታል እየታከምኩ ነዉ።»
።መሐመድ ሕይወቱን ለማትረፍ ሲፍጨረጨር፣ እንደሱዉ ከዉኃና ዉሐ ከሚያገላብጠዉ ፍርስራሽ፣ጉምድማጅ ጋር ሲታገሉ ያያቸዉን ሰዎች አሳዛኝ ፍፃሜ ይተርካል።
«ጣራ ላይ የወጡ ልጆች ሲጮኹና ሲያለቅሱ አይቻለሁ።የሚያድናቸዉ ፍለጋ እጃቸዉን እያወዛወዙ ይጮኹ ነበር።እልታደሉም እያየኋቸዉ---ጎርፉ ጠረጋቸዉ።ዉኃ የተፋቸዉ የአንድ ወይም የሁለት ቀን እድሜ ያላቸዉ ጨልቃ ሕፃናትም ነበሩ።»
መሐመድ ብዙ አዋቂዎችም ጎርፍ ሲያንከባልላቸዉ፣ ሌሎቹ ብቅ ጥልቅ እያሉ ለመዳን ሲታገሉ፣ ሌሎቹ ሲጮኹ አይቷል።ልቡን የነካዉ ግን የትናንሾቹ ነዉ።
«ብዙ ልጆች አይቻለሁ።ሁሉም ሄዱ።ሳያቸዉ፣ ፈጣሪዬን የተማፀንኩት ብዙ ሳይሰቃዩ ነብሳቸዉን ቶሎ እንዲያወጣት ነዉ።እኔም የዳንኩት በተዓምር ነዉ።ጎርፉ ግራ ቀኝ ሲያላጋኝ ቆይቶ፣ ድንገት አንድ የግንድ ጉማጅ አግኝቼ ተጠመጠምኩበትና መንሳፈፍ ያዝኩኝ።ወኃዉ ጎደል ያለበት ቦታ ስደርስ ወጣሁ።በጣም አስፈሪ ጊዜ ነበር።ሞትን በጣም በቅርብ አየሁት።»
ነዳጅ ዘይት የሚዛቅ፣ የሚሸጥ፣ ስደተኛ የሚርመሰመስባት ያቺ ሰሜን አፍሪቃዊት ሐገር በተመዘገበ ታሪኳ የዘንድሮዉን ዓይነት የተፈጥሮ መቅሰፍት አጋጥሟት አያዉቅም። በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጦር ድብደባና በአማፂያን ዉጊያ የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ መንግስት ከፈረሰ እንደ ግሪጎሪያዉያን አቆጣጠር ከጥቅምት 2011 ወዲሕ ማዕከላዊ መንግስት የላትም።ማሕደረ ዜና፣ የተመድ 78ኛ ጠቅላላ ጉባኤና የዓለም ቀዉስ
የሐገሪቱ ፖለቲከኞች ትሪፖሊና ቶብሮክ ላይ ሁለት መንግስት መስርተዉ የሐገርና ሕዝባቸዉን ሐብት ለመዝረፍ አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ጋር ይናጫሉ።ሰሞኑን በጎርፍ የተጥለቀለቀችዉ የደርና ከተማ የኸሊፋ ሐፍጣር ወታደሮችና ተቀናቃኞቻቸዉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2018ና 19ኝ በገጠሙባት ጦርነት ክፉኛ ተጎድታለች።
በጦርነቱ የተጎዳዉን የመሠረተ ልማት አዉታሯን መልሶ ለመገንባት 300 ሚሊዮን ዲናር (ወደ 70 ሚሊዮን ዶላር ገደማ) ተመድቦ ነበር።
የተገነባ የለም።ገንዘቡም የለም።የዳግም ግንባታዉ የበላይ አስተባባሪ የከተማዋ ከንቲባ ናቸዉ።ከንቲባዉን የሾሙት ኸሊፋ ሐፍጣር ናቸዉ።ከንቲባዉ የምስራቅ ሊቢያ መንግስት ምክር ቤት የሚባለዉ ስብስብ አፈ-ጉባኤ የአጉይላ ሳሌሕ ዘመድ ናቸዉ።የድረ ቃዛፊዋ ሊቢያ---ቁንፅል ታሪክ።በሊቢያ የሚገኙ ስደተኞች እንግልት
የጊኒ-ቢሳዉ 50ኛ የነፃነት ዕለት
ከሊቢያ ደቡብ ምዕራብ አትላንቲክ ዉቅያኖስ ጥግ የምትገኘዉ ትንሺቱ አፍሪቃዊት ሐገር ጊኒ ቢሳዉ ረጅም ዘመን ካስቆጠረዉ ከፖርቱጋል ቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጣችበትን 50ኛ ዓመት ነገ ታከብራች።መስከረም 24፣ 2023 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።
የፖርቱጋል ሐገር አሳሽና ባሪያ ፈንጋዮች የዛሬዋን ትንሽ ሐገር ከረገጡበት ከ1455 ጀምሮ እስከ 1973 ድረስ በፖርቱጋሎች ስትገዛ ዘመናት አስቆጥራለች።
በ1960ዎቹ አፍሪቃ ዉስጥ ብቅ ካሉት እዉቅ የነፃነት ተዋጊ አብዮተኞች አንዱ የሆኑት አሚልካር ካቢራል በመሩት የነፃነት ትግል ከቅኝ ገዢዉ ጦር ጋር ሲፋለሙ ከነበሩት ታጋዮች ማኑኤል ሴኩሬ አንዱ ናቸዉ።የነፃነት ታጋዮቹ ትግል ለድል በቅቶ ጊኒ-ቢሳዉ ነፃነትዋን ስታዉጅ ሴኩሬ የ24 ዓመት ወጣት ነበሩ።ዘንድሮ የ74 ዓመት አዛዉንት
አዛዉንቱ እንደሚሉት የ50 ዓመቱ የነፃነት ጉዞ፣ የዛሬ ኑሯቸዉ፣ የሐገር ሕዝባቸዉ ሁኔታም በርግጥ ያኔ እንዳሰቡ-እንደተፋለሙለትም አይደለም።
«ከ11 ዓመት የነፃነት ትግል በኋላ፣ በተለይ ጡረተኞችን በተመለከተ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ ነን።አንድ የቀድሞ ተዋጊ የጡረታ አበሉ በወር 40 ሺሕ ሴፋ (60 ዩሮ ገደማ) ነዉ።ለነፃነት እግርና እጁን ላጣ ታጋይ ይሕ አይገባዉም ነበር።በትግሉ ያልተካፈሉት የዘመኑ ገዢዎቻችን ሁሉም በሙስና የተዘፈቁ ናቸዉ።የመንግስት ሥልጣን ሲይዙ የቀድሞ ታጋዮችን ጉዳይ ጭራሽ አይነጋገሩበትም።»
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ ከጊኒ ቢሳዉ ሕዝብ 64 በመቶዉ ደሐ ነዉ።20 በመቶዉ ከድሕነት ትንሽ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ይገኛል።የቀድሞዉ ታጋይ የፖለቲካዊ ነፃነቱ ጥሩ ግብ በምጣኔ ሐብቱ አልተደገፈም ባይ ናቸዉ።
«ዛሬ ከቡባ እስከ ቢሳዉ ያለዉ መንገድ ቁሻሻ ነዉ።ከቢሳዉ እስከ ቁይታፊን ያለዉም አዉራ ጎዳና በጣም የተለበላሸ ነዉ።ሥልጣን ላይ ያለዉ ፓርቲ የፕሮግራሙን የመጀመሪያ ዓላማ ሐገሪቱን ነፃ ማዉጣት ነበር።ከግብ አድርሷል።የራሳችን ባንዲራና ብሔራዊ መዝሙር አለን።በልማቱ በኩል ግን ዜሮ ነዉ።አሚልካር ካብራይ ያለሙት ግብ ጨርሶ አልደረስንም።»
አጉስቲኖ ሮቤርቶ ፔሬይራ እንደ ሴኩሬ ሁሉ ለሐገራቸዉ ነፃነት የተፋለሙ አዛዉንት ናቸዉ።ለአባት ሐገር ነፃነት በመዋጋቴ «የሚፀፅተኝ የለም» ይላሉ-አዛዉንቱ።በግላቸዉ ግን «ያተረፍሁት የለም።»የአሚልካር ካብላር የጋራ ነፃነት
«በነፃነት ትግሉ በመካፈሌ የሚቆጨኝ የለም።የኔን፣ የቤተሰቤንና የልጆቼን ችግር የሚያቃልል ግን ምንም ያገኘሁት ነገር የለም።ይሁንና አባት ሐገርን ነፃ የማዉጣቱን ተልዕኮና ክብር ግን አሳክቼያለሁ።»
የዘመናት መጥፎ አገዛዝ
በጊኒ ቢሳዉ የነፃነት ታሪክ ከፕሬዝደንት ሆዜ ማሪዮ ቫስ በስተቀር በህዝብ የተመረጠ መሪ 5 ዓመት የሚዘልቀዉን የመጀመሪያ ዘመነ-ሥልጣኑን ያጠናቀቀ የለም።ትንሺቱ አፍሪቃዊት ሐገር 4ቴ ወታደራዊ መፍንቀለ መንግስት ተደርጎባታል።የመጨረሻዉ በ2012 የተደረገዉ ነዉ።
በ2012 በመፈንቅለ መንግስት ሥልጣን የያዙት የቀድሞዉ ጄኔራል ፕሬዝደንት ዑመሮ ሲሶኮ ራሳቸዉ ሐቻምና የካቲት ከተቃጣባቸዉ መፈንቅለ መንግስት ለጥቂት ነዉ ያመለጡት።
በምርጫ ይሁን በመፈንቅለ መንግስት ሥልጣን የሚይዙት የጊኒ ቢሳዉ መሪዎች እንደ አብዛኞቹ የአፍሪቃ ብጤዎቻቸዉ ሁሉ ቀዳሚዎቻቸዉን ከሚወቅሱ፣ ከሚከሱበት ሙስና፣ የአስተዳደር ብሉሽነትና ግልኝነት በተራቸዉ ስለሚዘፈቁበት ሐገሪቱ ከድሕነት አዙሪት አልተላቀቀችም።
ነጋሽ መሐመድ