ትኩረት በአፍሪቃ፣ የሱዳንና የኮንጎ ጦርነቶች፣ ርዳታና ዲፕሎማሲ
ቅዳሜ፣ የካቲት 8 2017
አፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ አዲስ አበባ ላይ ሥለ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክና ሥለ ሱዳን ጦርነቶች እየተነጋገረ ነዉ።የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪብሊክ ፕሬዝደንት ግን ከአዲስ አበባዉ ጉባኤ ይልቅ ሙኒክ-ጀርመን ዉስጥ የሚደረገዉን ጉባኤ መርጠዉ ትናንት ጀርመን ገብተዋል።ዋና ጠላታቸዉ የሩዋንዳ ፕሬዝደንት ፖዉል ካጋሚ ግን አዲስ አበባ ናቸዉ።የአዲስ አበባና የሚኒክ ጉባኤዎች ሥለ ኮንጎም ሆነ ሥለ ሱዳን ጦርነቶች የሚወስኑት ሳይታወቅ ትናንት በሁለቱም ሐገራት የሚደረገዉ ዉጊያ ተባብሷል።የዛሬዉ ትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅታችን የኮንጎና የሱዳንን ጦርነቶችና የፖለቲከኞችን ሙከራን ይቃኛል።
የሱዳን ጦርነት፣ፀሎትና ዲፕሎማሲ
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ጦርነት በዛ አሉ።ከፍልስጤም-እስራኤል እስከ ዩክሬን፣ ከምያንማር እስከ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ በግጭት ጦርነት የሚያልቅ፣የሚሰቃየዉን ሕዝብ እየቆጠሩ ምዕመናን ለሰላም እንዲፀልዩ ተማፀኑ።ሰዳንና ሕዝቧ ከሚፀለይላቸዉ ቀዳሚዎቹ ናቸዉ።ቫቲካን-ከትናንት በስቲያ ሮብ።
«ጦርነት ሥለሚደረግባቸዉ ብዙ ሐገራት አስባለሁ።እሕትና ወንድሞቼ ለሠላም እንፀለይ።ጦርነት ሁልጊዜ ሽንፈት መሆኑን አትርሱ።የተወለድነዉ ሰዉ ለመንከባከብ እንጂ ለመግደል አይደለም።እስኪ የሰላምን መንገድ እንሻ።በየዕለቱ ፀሎታችሁ ለሰላም ተማፀኑ።ዩክሬን፣ ፍልስጤም፣እስራኤል፣ሱዳን፣ ምያንማር፣ ኮንጎ ዉስጥ ስንቶች እንደሚሰዉ አትዘንጉ።እባካችሁ ለሠላም ፀልዩ፣ ለሠላም ንሰሐ ግቡ።»
የዚያኑ ቀን ሮብ በሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ ምክትል ኃላፊ ኤድሞር ቶንድላና በሱዳንr ሕዝብ ላይ የሚደርሰዉ ጥቃት መበርታቱን፣ ግድያ መክፋቱን አስታወቁ።-ከኒዮርክ።
«በአጠቃላይ በሕዝቡ፣ በጤና ተቋማት፣በሌሎች የመሠረተ-ልማት አዉታሮችና በመሳሰሉት ላይ የሚደርሰዉ ጥቃት እየጨመረ ነዉ።ባጭሩ ሁኔታ በጣም መጥፎ ነዉ።ጥሩ ነገር አይታይም።ግጭቱ ቀጥሏል።ሰዎች አሁንም እየተፈናቀሉ ነዉ።»
የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ሁለት ዓመት ሊሞላዉ 5 ሳምንት ቀረዉ።እስካሁን ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ሲያንስ 60 ሺሕ፣ ሲበዛ 150 ሺሕ ሕዝብ አልቋል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ ጦርነቱ ሱዳንን በስደተኛና ተፈናቃይ ሕዝብ ብዛት ከዓለም አንደኛ አድርጓታል።48 ሚሊዮን ከሚገመተዉ ሕዝብ 30 ሚሊዮን ሕዝብ ሰብአዊ ርዳታ ጠባቂ ነዉ።ከዚሕ ዉስጥ 21 ሚሊዮኑ አንድም ረሐብ የጠናበት፣ ሁለትም ተፈናቃይና ስደተኛ ነዉ።
ኤድሞር ቶንድላና እንደሚሉት ለከፋ ችግር የተጋለጠዉን 21ድ ሚሊዮን ሕዝብ ለመርዳት ድርጅቱ በነብስ ወከፍ 50 የአሜሪካን ሳምንቲም እንኳ ማግኘት አልቻለም።
«ለችግረኛዉ ሕዝብ መርጃ የ4.2 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዲሰጠን ጠይቀናል።ይሕን የገንዘብ መጠን አስቸኳይ ርዳታ ለሚያስፈልገዉ ለ21 ሚሊኑ ሕዝብ ብናካፍለዉ ለእያንዳዱ ተረጂ በቀን የ50 ሳንቲም ሰብአዊ ርዳታ እንዲሰጠዉ ነዉ-የጠየቅ ነዉ።»
የሱዳንና የሩሲያ ወዳጅነት የአረብ ኤምሬቶች ሐሳብ
የሱዳን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዓሊ የሱፍ አሕመድ አል ሸሪፍ የሮሙን ተማፅኖ ወይም የኒዮርኩን ጥያቄ ሰምተዉ፣ለሐገራቸዉ ሰላም፣ ለሕዝባቸዉ ደሕንነት ፀልየዉ፣ ርዳታ ጠይቀዉ ይሆን-አይሆንምም ይሆናል።ሮብ ግን ሞስኮ ነበሩ።
የሱዳኑ ትልቅ ዲፕሎማት በሩሲያ ጉብኝታቸዉ የሞስኮ ባለሥልጣናትን ከመጋረጃ ጀርባ፣ የጦር መሳሪያ፣የሥብአዊ ርዳታ፣ የፖለቲካ ድጋፍም መጠየቃቸዉ አልቀረም። በይፋ የጉዟቸዉ ዓላማ ግን ሁለት ነዉ።
የሱዳን ተፋላሚዎች ዉጊያ እንዲያቆሙ፣ ለሕዝቡ ርዳታ እንዲደርስ ብሪታንያ ባለፈዉ ኅዳር ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ያቀረበችዉን ረቂቅ ደንብ፣ ሩሲያ ድምፅን በድምፅ በማሽር ሥልጣኗ ዉድቅ በማድረጓ-ሞስኮዎችን ለማመስገን-አንድ፣ሩሲያ ሱዳን ባሕር ጠረፍ ላይ የጦር ሠፈር ለመመስረት ሁለቱ መንግስታት የጀመረቱን ድርድር ለመቀጠል-ሁለት።
ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዓሊ የሱፍ «የሱዳንን ሉዓላዊነት የሚጥስ» ያሉትን ረቂቅ ደንብ ሩሲያ ማገድዋን ለሱዳን መንግስትና ሕዝብ «የማይዘነጋ» ና ታሪካዊ ዉለታ» በማለት ሞስኮዎችን አመስግነዋል።የሩሲያ ባሕር ኃይል ሠፈር የመገንባቱን ስምምነትና ሒደት ደግሞ «ያለቀ ጉዳይ» ብለዉታል።
«በዚሕ ጉዳይ ላይ ሙሉ በሙሉ ተስማምተናል።ምንም እንቅፋት የለም።ይሕ ቀላል ጥያቄ ነዉ።ተግባብተናል።»
አንድ ቀን-ሮብ፣ ሶስት ቦታዎች-ቫቲካን፣ ኒዮርክና ሞስኮ ሶስት ሁነቶች።-ሱዳን።የሱዳንን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ትረዳለች የምትባለዉ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በአፍሪቃ ሕብረት በኩል የሱዳንን ፖለቲካ ለመዘወር አንድ ሁለት ማለቷ ከወደ አቡዳቢ የተሰማዉም ባገባደድነዉ ሳምንት መጀመሪያ ነበር።ሰኞ።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አዲስ አበባ ላይ ከተሰየመዉ የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን በሱዳን ጉዳይ በተለይ በርዳታ አቅርቦቱ ላይ የሚመክር ልዩ ስብሰባ እንዲያደርግ ጠይቃለች።የሱዳን ተፋላሚዎች በመጪዉ የሙስሊሞች ቅዱስ የረመዳን ወር ተኩስ እንዲያቆሙ ጠይቃለች።ለሱዳን ሕዝብ መርጃ 200 ሚሊዮን ዶላር እንደምትሰጥ አስታዉቃለችም።
ካለፈዉ ጥር ጀምሮ በጦር ሜዳዉ ዉጊያ ድል እየቀናዉ የመጣዉ የሱዳን መከላከያ ጦር ግን «የጠላቴ ደጋፊዎች» የሚላቸዉን የአቡዳቢ ገዢዎችን ሐሳብ ዉድቅ አድርጎታል።የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ማሊክ አጋር የአቡዳቢ ገዢዎችን «በአፍሪቃዊት ሐገር ላይ ወንጀልና ወረራ የፈፀሙ» በማለት አዉግዘዋቸዋል።
የሱዳን ሕዝብ ባጠቃላይ የዳርፉር በተለይ ግን ከቫቲካን፣ ኒዮርክ፣ ሞስኮ፣አቡዳቢ፣ አዲስ አበባና ካርቱም ላይ የሚደረገዉን ፀሎት፣የሚሸረብ-የሚነጠል፣ የሚበጠስ የሚቀጠለዉን ፖለቲካ ዲፕሎማሲ በቅጡ ሊያቅ ቀርቶ መስማቱም አጠራጣሪ ነዉ።23 ወራት እንደኖረበት በኃይለኞች ዉጊያ፣የኃይል ርምጃና ዘረፋ እየተጨነቀ ነዉ።
የዳርፉርን ትልቅ ከተማ አል ፋሸርን ለመያዝና ላለማስያዝ ለወራት የሚዋጉት የሱዳን መከላከያ ጦርና የፈጥኖ ደራሹ ኃይላት ካለፈዉ ማክሰኞ ጀምሮ አል ፋሸር አጠገብ ዘምዘም በተባለዉ አካባቢ የሚገኘዉን የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያን የዉጊያ አዉድ አድርገዉታል።አምንስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ የተለያዩ የመብት ተሟጋቾችና የርዳታ ድርጅቶች እንዳሉት የስደተኞቹን መጠለያ ጣቢያ ቀድሞ ያጠቃዉ ፈጥኖ ደራሹ ጦር ነዉ።በጥቃቱ በ10 የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ተገድለዋል።በመቶ የሚቆጠሩ ቆስለዋል።
ለኮንጎ ጦርነት መፍትሔዉ አዲስ አበባ ወይስ ሙኒክ?
ሶስቱም ለተቃራኒ ዓላማ ግባቸዉ የሚመቻዉን ሥፍራና ጊዜ የመረጡ መስለዋል።ሼሴኬዲ፣ ካጋሚና M23።የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ፌሊክስ ሼሴኬዲ ትናንት አርብ ሙኒክ-ጀርመን ገብተዋል።የሼሴኬዲ ቀንደኛ ጠላት የሩዋንዳዉ ፕሬዝደንት ፖዉል ካጋሚ ባንፃሩ ትናትናዉኑ አዲስ አበባ ገብተዋል።
የደቡባዊ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ፣ የምሥራቅ አፍሪቃ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰጡና የሚሰጡት የፖለቲካ፣የዲፕሎማሲ፣ የጦር ኃይልም ድጋፍ ለንቋሳዉን የኪንሻ መንግስት ከሩዋንዳና በሩዋንዳ ከሚደገፈዉ አማፂ ቡድን ጥቃት ማዳን አልቻሉም።
ሥለዚሕ ሼሴኬዲ የኃያሉን ዓለም ድጋፍ አጥብቀዉ ይሻሉ።ሙኒክ የመጡትም እዚያዉ ሙኒክ ትናንት በተጀመረዉ የዓለም የፀጥታ ጉባኤ ላይ የሚካፈሉት መንግሥታት ርዋንዳን አዉግዘዉ ቢቻል በካጋሚ ላይ ጠንካራ ማዕቀብ እንዲጥሉ ለማግባባት ነዉ።
ካጋሚ ባንፃሩ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የዉስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል እየተባሉ ብዙ የአፍሪቃ ሐገራት «አይንሕ ላፈር» ቢሏቸዉም እዚያዉ አዲስ አበባ ዉስጥ ከአፍሪቃዉያን ወዳጅ-ጠላቶቻቸዉ ጋር መነታረኩን የመረጡ መስለዋል።ትናንት በዝግ፣ ዛሬ በይፋ የተጀመረዉ የአፍሪቃ ሕብረት ዓመታዊ መደበኛ ጉባኤ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጉዳይ ላይ ሁነኛ ዉሳኔ ማሳለፍ አለማሳለፉ ለዚሕ ዘገባ አልደረሰልንም።
የሼሴኬዲ ሥልት፣ የካጋሚ ድል
አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬን ሠላም አዲስ የነደፉት ዕቅድ አዉሮጶችን በሚያነጫንጭ፣ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አንድነትን በሚያንገጫግጭበት ወቅት ሼሴኬዲ ሙኒክ ላይ ሰሚ ማግኘታቸዉ በርግጥ አጠራጣሪ ነዉ።
ብቻ ለሙኒኩ ጉባኤ የዩክሬን- ምዕራባዉያን መንግሥታትና የሩሲያ ጦርነት ዐብይ ርዕሱ እንደሆነ ሁሉ የዘንድሮዉ የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ዋና ትኩረት የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጦርነት ነዉ።የሼሴኬዲ ሥልት፣የካጋሚ ብልሐት መሳት-መያዙን ለማወቅ ባለጉዳዮች ዓይን ጆሯቸዉን ሙኒክና አዲስ አበባ ላይ እንደለገቱ ቡካቩ ላይ ካጋሚ እንደገና ድል አደረጉ።በጠንካራዉ የሩዋንዳ ጦር የሚደገፈዉ M23 አማፂ ቡድን የቡካቩን አዉሮፕላን ማረፊያ ተቆጣጠረ።አርብ ቀትር ላይ መከረኛዉ ሕዝብ ሟች-ልጅ-ዉላጅ-ወዳጁን ጥሎ ሸሸ።እሳቸዉ አንዷ ናቸዉ።
«አባረሩን።ተሰቃየን።M23 እያሰቃየን ነዉ።እየሸሸን ነዉ።ሁለቱን ልጆቼን ይዤ እየሸሸሁ ነዉ።ሌሎቹ ሞተዋል።አራት ልጆቼ መተዋል።እነዚሕ ሁለቱ ብቻ ቀርተዉኛል።»
ቡካቩ የምሥራቃዊ ኮንጎ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ነዉ።የM23 አማፂያን ትናንት የተቆጣጠሩት አዉሮፕላን ማረፊያ ከቡካቩ 30 ኮሎ ሜትር ይርቃል።አዉሮፕላን ማረፊያዉ በየሥፍራዉ ለበተነዉ ሕዝብ ርዳታ የሚደርስበት ነበር።ለጊዜዉም ቢሆን ሁሉም ተቋረጠ።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ከፍተኛ ኮሚሽነር UNHCR ቃል አቀባይ ኢዩጂን ብዩን እንደሚሉት ከዚሕ ቀደም ጎማና አካባቢዉ የተደረገዉ ጦርነት ከ350 ሺሕ በላይ ሕዝብ ለሁለተኛ ጊዜ አፈናቅሏል።
የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሕዝብ መከራ
«ሰሜንና ደቡባዊ ኪቩ ግዛት ጎማና ሚኖቫ አካባቢዎች የነበሩ 70 ሺሕ የአስቸኳይ ጊዜ መጠለያ ጣቢያዎች በከባድ መድፍ በመደብደባቸዉና በመዘረፋቸዉ 350 ሺሕ ተፈናቃይ በየቦታዉ ተብትኗል።ከየመጠለያ ጣቢያዉ የተበነዉ ሕዝብ ምግብ አያገኝም።መጠለያም ጣሪያም የለዉም።»
ታዛቢዎች እንደሚሉትየM23 አማፂ ኃይል የምሥራቅ ኮንጎ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ቡካቩን ለመያዝ የሚያግደዉ ኃይል የለም።ብሩንዲ ከኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጋር የሚያገናኛትን ድንበር ዘግታለች።በሩዋንዳ ጦር ጭምር የሚደገፈዉ M23 ባለፈዉ ወር ምሥራቃዊ ኮንጎ ዉስጥ አዲስ ጥቃት ከከፈተ ወዲሕ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች፣ በ10 የሚቆጠሩ የዉጪ ሐገር ወታደሮች ተገድለዋል።በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠር ሰላማዊ ሕዝብ ተፈናቅሏል።
ነጋሽ መሐመድ