1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ትኩረት በአፍሪቃ፤ የሱዳን ጦርነት፣የአረብና የአሜሪካኖች አቋም፣ የማሊ ፓርቲዎች መታገድ

ነጋሽ መሐመድ
ቅዳሜ፣ ግንቦት 9 2017

ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖቹን ለፈጥኖ ደራሹ ጦር ያስታጠቀችዉ ወይም ግዢዉን ያመቻቸዉ ወትሮም ለጄኔራል ሐምቲ ጠንካራ ድጋፍ ትሰጣለች የምትባለዉ የተባበሩት አረብ አረብ ኤምሬቶች ናት ይባላል። የሱዳን መንግስት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን በዘር ማጥፋት ወንጀል ICJ በሚል ምሕፃረ ቃል በሚጠ,ራዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፍርድ ቤት ላይ ከስሷታል።

የዩናይትድ ስቴትስ የዲሞክራቲክ ፓርቲ እንደራሴዎች የሱዳንን ጦርነት አባብሳለች ለሚሏት ለተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አሜሪካ ልትሸጥ የተስማማችዉ የጦር መሳሪያ ዉል እንዲሰረዝ ጠይቀዋል።
ከግራ ወደቀኝ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝደንት ሼኽ መሐመድ ቢን ዘይድ አል ናሕያን ምስል፦ Alex Brandon/AP/dpa/picture alliance

ትኩረት በአፍሪቃ፤ የሱዳን ጦርነት፣የአረብና የአሜሪካኖች አቋም፣ የማሊ ፓርቲዎች መታገድ

This browser does not support the audio element.

ዘምዘም-ዳርፉር ከሚገኘዉ መጠለያ ጣቢያ ዳግም ለተፈናቀለችዉ እናት፣ ለአዚዛ ኢስማኤል ኢድሪስ፣ልጆቿና በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ብጤዎቻቸዉ ሕይወት መከ,ራ ነዉ።መራር።«የፈጥኖ ደራሽ ጦር ባልደረቦች ቤቶቻችንን አነደዱት።» ትላለች ኢዚዛ።

«ምንም ነገር አልቀረንም።ቤታችንን አጋዩት።ከ4ና 5 ቀናት በኋላ ወደ ጠዊላ ጉዞ ጀመርን።ግን መንገድ ላይ ያዙንና አዮቻችንን፣ፍራሾቻችንን፣ ብርድልብሶቻችንን ሁሉንም ዘረፉን።ባዶ እጅግ-እግራችን እዚሕ ደረሰን።»

ሶስተኛ ዓመቱን በያዘዉ በሱዳን የርስበርስ ጦርነት የተገደሉትን ሰዎች ቁጥር በትክክል የቆጠረዉ ወይም የቆጠረዉን በይፋ የሚናገር የለም።ገማቾች እንደሚሉት ግን ሟቹ ከ150 ሺሕ ቢበልጥ እንጂ አያንስም።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ ደግሞ 50 ሚሊዮን ከሚገመተዉ የሱዳን ሕዝብ ግማሽ ያሕሉ ለረሐብ ተጋልጧል።

13 ሚሊዮኑ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል ወይም ተሰድዷል።ለሕዝቡ ርዳታ የሚሰጠዉ ዓለም ተሰላችቷል።የተገኘዉን ርዳታ ለችግረኛዉ ለማቃመስ ሲሞከር ደግሞ ተፋላሚ ኃይላት መንገድ ይዘጋሉ፣ ርዳታዉን ይዘርፋሉ ወይም ተረጂዉን ይበታትኑታል።

 «ጠዊላ ዉስጥ የርዳታ ድርጅቶች ታገኛላችሁ ብለዉን ነበር።እዚያ ሥንደርስ ግን ማንም የለም።ለኛ እሕል ዉኃ የሚሰጠን ቀርቶ ለልጆቻችን አንዲት ብስኩት እንኳ የሚሰጠን አላገኘንም።»

ትላለች አዚዛ።ሰሚ ያጣ ሮሮ።በልማዱ ዓለም አቀፍ የሚባለዉ ማሕበረሰብ የሱዳኖችን እልቂት፣ ሥቃይ ሰቆቃ ችላ ያለዉ መስሏል።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን ለማስተናገድ ጠብ እርግፍ ሲሉ የሰነበቱት የዓረብ ሐገራትም የየሚደግፉት ሐይል በጦርነቱ የበላይነት እንዲያገኝ ከመሻኮት ባለፍ ጦርነቱን ለማስቆም የሚፈልጉ አልመሰሉም።

የሳዑዲ አረቢያ ገዢዎች ቃልና ተስፋ

እርግጥ ነዉ የፋርስ ባሕረ ሠላጤ የትብብር ምክር ቤት የተባለዉ ማሕበር የሚያስተናብራቸዉ የ6ቱ የአካባቢዉ ሐገራት መሪዎች ከአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ጋር ባደረጉት ጉባኤ የአረቦችን አቋም ያንፀባርቃል በተባለዉ መግለጫ ላይ የሳዑዲ አረቢያዉ አልጋ ወራሽ  ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን ሱዳንን መጥቀሳቸዉ አልቀረም።

«ቀዉሶችና ግጭቶች እንዲቆሙ የሚደረጉ ጥረቶችን እናበረታታለን።ከዚሕ አኳያ በየመን አጠቃላይ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲገኝ በሐገሪቱ የፖለቲካ ኃይላት መካከል ድርድር እንዲደረግ ሳዑዲ አረቢያ ጥረቷን ትቀጥላለች።የሱዳኑ ቀዉስ በሳዑዲ አረቢያና በአሜሪካ ድጋፍ የሚደረገዉ የጅዳ መድረክ እንዲቀጥል የምናደርገዉን ጥረትም እንቀጥላለን።»

ለማለት ያክል አሉ።ዉጊያዉም ቀጥሏል።ሁለት ዓመት በታንክ፣ መድፍ፣መትረየስ፣ ጠመንጃና ጄት ይደረግ የነበረዉ ዉጊያ በቅርቡ ወደ ሰዉ አልባ አዉሮፕላን (ድሮን) ተቀይሯል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር በሰዉ አልባ አዉሮፕላን በተደጋጋሚ የመታት የሱዳን የወደብ ከተማ ፖርት ሱዳንምስል፦ AFP

ካለፈዉ ጥር ወዲሕ በተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ ሽንፈት የገጠመዉ የጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሐምቲ) ፈጥኖ ደራሽ ጦር ከርቀት በሚዘዉራቸዉ ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች (ድሮኖች) በተለይ ፖርት ሱዳን የሚገኙ የመከላከያ ጦር ሠፈሮችን፣ የጦር መሳሪያ ማከማቻ መጋዘኖችን፣ ነዳጅ ማከማቻዎችን፣ ለሰላማዊ አገልግሎት የሚዉሉ ወደቦችን፣ የርዳታ ቁሳቁሶችን እያጋየ ነዉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒ ጉተሬሽ ባለፈዉ ሳምንት በቃል አቀባያቸዉ በፋርሐን ሐቅ በኩል እንዳሉት የሰዉ አልባ አዉሮፕላኖቹ ድድባ ባስቸኳይ መቆም አለበት።

«መግለጫችን፣ ለሱዳን የሰብአዊ ዕርዳታ በሚገባበት በዋናዉ ወደብ በፖርት ሱዳን ላይ በቅርቡ የሚፈፀመዉ የሰዉ አልባ አዉሮፕላን ድብደባ፣ ዋና ፀፈሐዉን በጣም ያሰሳበ መሆኑን የሚያመለክት ነዉ።ድብደባዉ ለሱዳን የሚሰጠዉን የሰብአዊ ርዳታ የሚያደናቅፍ፣ርዳታ ለማድረስ የሚደረገዉን ጥረት ይበልጥ የሚያወሳስብ ነዉ።ይሕ (ጦርነቱን) ይበልጥ የሚያባብስ ርምጃ በርካታ ተጨማሪ ሰላማዊ ሕዝብን ሊጨርስ እንደሚችልና የመሰረት ልማት አዉታሮችን ይበልጥ እንደሚያጠፋ አስጠንቅቀዋል።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መግለጫ በተሰማ በአራተኛዉ ፈጥኖ ደራሽ ጦር ዒላማዉን ከፖርት ሱዳን ወደ ርዕሠ-ከተማ ካርቱም አዙሮ የካርቱም የዉኃ ማጠራቀሚያ ጋኖችን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈ,ያ መስመሮችንና ሌሎች የመሠረተ-ልማት አዉታሮችን በሰዉ አልባ አዉሮፕላን እያደባያቸዉ ነዉ።

         የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጣልቃ ገብነትና የአሜሪካኖች መንታ አቋም

ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖቹን ለፈጥኖ ደራሹ ጦር ያስታጠቀችዉ ወይም ግዢዉን ያመቻቸዉ ወትሮም ለጄኔራል ሐምቲ ጠንካራ ድጋፍ ትሰጣለች የምትባለዉ የተባበሩት አረብ አረብ ኤምሬቶች ናት ይባላል።ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን የሚመሩት የሱዳን መንግስት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን በዘር ማጥፋት ወንጀል ICJ በሚል ምሕፃረ ቃል በሚጠ,ራዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፍርድ ቤት ላይ ከስሷታል።

የአቡዳቢ ባለሥልጣናት ግን ወቀሳዉንም ክሱንም ዉድቅ አድርገዉታል።የዩናይትድ ስቴትስ የዴሞክራቲክ ፓርቲ የምክር ቤት እንደራሴዎች በበኩላቸዉ የሱዳኑን ጦርነት አባብሳለች ለምትባለዉ ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዩናይትድ ስቴትስ የጦር መሳሪያ እንዳትሸጥ የሚያገድ ረቂቅ ደንብ አዘጋጅተዋል።

አራት የዴሞክራቲክ ፓርቲና አንድ የግል እንደራሴ በጋራ ለዩናይትድ ስቴትስ ሕግ-መወሰኛ ምክር ቤት ወይም ሴኔት ያቀረቡት ደንብ አሜሪካ ከዚሕ ቀደም ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የጦር መሳሪያ ለመሸጥ ያደረገችዉ 3 ዓይነት ዉል እንዲታገድ የሚጠይቅ ነዉ።የዋሽግተንና የአቡዳቢ ባለሥልጣናት ከዚሕ ቀደም በተዋዋሉት መሠረት ዩናይትድ ስቴትስ 1.32 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ተዋጊ ሔሊኮፕተር፣ የ130 ሚሊዮን F15 ተዋጊ ጄት እና የ150 ሚሊዮን የተዋጊ አዉሮፕላን መለዋወጪያዎችን ለአቡዳቢ ትሸጣለች።

የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን የሪፕሊካን ፓርቲና መስተዳድር የሚቃወሙት የምክር ቤት እንደራሴዎች ዋሽግተን ዉስጥ ያለፈዉን ሽያጭና ግዢ ለማሳገድ የሕግ አንቀፅና ቃላትን ሲቀምሩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አቡዳቢ ዉስጥ ለሼኽ መሐመድ ቢን ዘይድ አል ናሕያን የ200 ቢሊዮን ዶላር ጦር መሳሪያና ሸቀጥ ለመስሸጥ ተስማምተዋል።

ካርቱም ዉኃ እንደተጠማች፣ መብራት እጦት እደተዳፈነች ቀን ቀንን ወለደ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ 50 ሚሊዮን ከሚገመተዉ የሱዳን ሕዝብ ግማሽ ያሕሉ ለረሐብ ተጋልጧል።13 ሚሊዮኑ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል ወይም ተሰድዷልምስል፦ picture alliance / AP Photo

                               የማሊ የዴሞክራሲ ተስፋ የገጠመዉ እንቅፋት

የማሊ ጊዚያዊ ወታደራዊ መንግስት ባለፈዉ ማክሰኞ የሐገሪቱን የፖለቲካ ማህበራትና ድርጅቶችን በሙሉ አግዷል።ወታደራዊዉ መንግሥት የፖለቲካ ማሕበራትን ያገደዉ ርዕሰ ከተማ ባማኮ ዉስጥ «ዴሞክራሲያዊ» የተባለ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አቀንቃኞችን ካሰረ፣እዚያዉ ባማኮ ዉስጥ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት የሚሹ ወገኖች ባደባባይ ሰልፍ ጥቄያቸዉን ካሰሙ ከዕለታት በኋላ ነዉ።

የማሊ መንግሥት የሚቆጣጠራቸዉ መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት የፖለቲካ ፕርቲዎቹ እንዲታገዱ የሚያዘዉን አዋጅ ያፀደቁት የሐገሪቱ ወታደራዊ መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ ናቸዉ።የትዕዛዙ ምክንያትም «ሕግና የሕዝብ ሥርዓትን ለማስከበር» ነዉ።አዋጁ የታገዱት የፖለቲካ ማሕበራትና ድርጅቶች «አባላት እንዳይሰበሰቡም ያግዳል።

                      ለዴሞክራሲ ታሪካዊ እንቅፋት

መንበሩን ለንደን ያደረገዉ የቻተም ሐዉስ የጥናት ተቋም ባልደረባ ፓዉል ሜልይ እንደሚሉት ማሊ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ደምቃ የምትታይ ሐገር ናት። በተለይ እግአ በ1990ዎቹ የተቀጣጠለዉ የዴሞክራሲ ጥያቄ ባስከተሏቸዉ መፍንቅለ መንግሥቶች በግልፅ ትታወቃለች።

ሜልይ እንደሚሉት የፖለቲካ ማሕበራት መታገዳቸዉ ለዚያች ሐገር ዴሞክራሲ ታላቅ ዉድቀት ነዉ።

«ባለፉት ጥቂት ቀናት ማሊ ዉስጥ የተደረገዉ ነገር ለዴሞክራሲ እንቅፋት ነዉ።ሐገሪቱ በተቃዉሞና በ1990ዎቹ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በገፏቸዉ መፈንቅለ መንግስቶች ትታወቃለች።አልፎ አልፎ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስቶች ቢቋረጥም ለረጅም ጊዜ የተመረጠ መንግስት የነበራት ሐገርም ናት።»

የማሊ የፖለቲካ ማሕበራት፣ ድርጅቶችና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን የታገዱት ለምን ያሕል ጊዜ እንደሆነ የማሊ ወታደራዊ መንግሥት ባለሥልጣናትም ሆኑ መገናኛ ዘዴዎች በግልፅ ያሉት ነገር የለም።የፖለቲካ ተንታኝ ፓዉል ሜልይ እገዳዉ ለረጅም ጊዜ መቆየቱን ሕዝቡ የሚቀበለዉ አይመስለኝም ይላሉ-ተንታኙ።

«የዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ለረጅም ጊዜ ተዘግተዉ መቆየታቸዉን የማሊ ሕዝብ ይቀበለዋል ብዬ አላስብም።»

የማሊ የሕግ ባለሙያ ቶማኒ ኦዉመር ዲያሎ ግን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መታገድ ሕጋዊ ጥያቄ ለማንሳት ምንም ዓይነት ቀዳዳ አይከፍት ባይ ናቸዉ።የሕግ ሥርዓቱ ዳግም ካልተከፈተ የተደራጀ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በሙሉ ሕገ ወጥ ነዉ።

ምርጫ ተራዝሟል፣ ተቃዉሞም ታግዷል

ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ የመሯቸዉ የማሊ የጦር መኮንኖች እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2020ና በ2021 ካደረጉት መፈንቅለ መንግሥቶች ወዲሕ ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሐገር  በወታደራዊ ሥርዓት እየተገዛች ነዉ።የወታደራዊ መንግስቱን የመሪነት ሥልጣን የያዙትም ራሳቸዉ  ኮሎኔል ጎይታ ናቸዉ።ኮሎኔል ጎይታ ባጭር ጊዜ ዉስጥ ምርጫ እንደሚደረግ ቃል ገብተዉም ነበር።

ይሁንና የካቲት 2024 (እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር) ይደረጋል ተብሎ የነበረዉ ምርጫ «ቴክኒካዊ» በተባለ ምክንያት ሳይደረግ ቀርቷል።ባለፈዉ ሚያዚያ ደግሞ የማሊ ጊዚያዊ መንግሥት ሚንስትሮች የኮሎኔል ጎይታ የመሪነቱን ሥልጣን እንደ ግሪጎሪያኑ እስከ 2030 ድረስ እንደያዙ እንዲቀጠሉ ወስነዋል።

የማሊ ወታደራዊ መንግሥትን በመቃወምና በመደገፍ በቅርቡ ባማኮ ማሊ ዉስጥ ከተደረጉ ተቃራኒ የአደባባይ ሠልፎች በከፊል።ከሰልፉ በኋላ የማሊ ወታደራዊ መንግሥት የፖለቲካ ፓርቲዎችን አግዷልምስል፦ AFP

ይሕም ጠንካራዉ ኮሎኔል እስካሁን አምስት ዓመት ያሕል የቆዩበትን የመሪነት ሥልጣን ወደፊትም አምስት ዓመት ይቀጥሉባታል ማለት፣-እድሜ ከሰጣቸዉ፣ ወይም መፈንቅለ መንግስት ከሳታቸዉ።

ባለፉት አምስት ዓመታት በፈረንሳይ የሚመራዉ የምዕራባዉያን ጦር ከማሊ ወጥቶም የማሊ ደፈጣ ተዋጊዎች ግሥጋሴ ተገድትቷል።የሐገሪቱ አጠቃላይ ሠላም፣መረጋጋትና የህዝቡ የፖለቲካ ነፃነት  ግን ተንታኞች እንደሚሉት አሁንም  መሻሻል አላሳየም።ባለፈዉ ማክሰኞ የፖለቲካ ፓርቲዎች መታገዳቸዉ ደግሞ የዴሞክራሲያዉ ሥርዓትን ተስፋ ጨርሶ እንዳያጠፋዉ አሥግቷል።

ከጀርመኑ ወግ አጥባቂ የክርስቲያን ዴሞክራሲያዊ ሕብረት (CDU) ጋር የቅርብ ግንኙነት ያለዉ የኮንራድ አደናወር መታሰቢያ ጥናት ተቋም ባልደረባ ኡልፍ ሌሲንግ እንደሚሉት የማሊ ወታደራዊ መንግስት ርምጃ ምርጫ ይደረጋል ብሎ ለሚጠብቀዉ ሕዝቡ ተስፋ አስቆራጭ ነዉ።

«የማሊ መንግሥት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማገዱ፣ አንድ ርምጃ ወደ ኋላ መመለስ ነዉ።ዘንድሮ ምርጫ ይደረጋል ብሎ ለሚጠብቀዉ ሕዝብ ደግሞ ተስፋ አስቆራጭ ነዉ።»

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲያ ሥርዓት መመሥረት የሚያደርጉትን ትግል እንደሚቀጥሉ እስታዉቀዋል።ለሕገ መንግሥት መከበር የወጣቶች ሕብረት የተባለዉ ትብብርም አባላቱ የማሊ ሕገ-መንግሥት እንዲከበር የሚያደርጉትን ትግል  ለማጠናከር ቃል ገብቷል።የትብብሩ አባል ኤይሳታ ልይ እንደምትለዉ ማሊ ዉስጥ የዴሞክራሲያዊ መርሆችን ለማስከበር እሷና ብጤዎችዋ በፅናት ይታገላሉ።

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW