ትኩረት በአፍሪቃ፣ የCOP30 ትዩዩ-ጉባኤ፣ የኤል ፋሻር እልቂት ያስከተለዉ ዉግዘትና ማዕቀብ
ቅዳሜ፣ ኅዳር 13 2018
የጉባኤ ተቃራኒ ጉባኤ-ብራዚል
የዓለም መሪዎች፣ባለሥልጣናት፣ዲፕሎማቶችና ባለሙያዎች የአየር ንብረት ለዉጥ በሚያደርሰዉ ቀዉስና ቀዉሱን በሚቋቋሙበት ሥልት ላይ ቤለም ብራዚል ዉስጥ ሲነጋገሩ፣ የዉይይት ጉባኤዉን ሒደትና ዉጤትን የሚጠራጠሩ ወይም የሚቃወሙ ወገኖች ባንፃሩ የራሳቸዉ ጉባኤ አዘጋጅተዋል።«የሕዝብ ጉባኤ» ብለዉታል-ትዩዩን ጉባኤ።ዋናዉ ጉባኤ ከሚደረግበት ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ፓራ በተባለዉ የብራዚል ፌደራል ዩኒቨርስቲ ዉስጥ ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ በተሰየመዉ ጉባኤ ላይ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ተካፍለዋል።
ጉባኤተኞች ከተነጋገሩባቸዉ ጉልሕ ርዕሶች አንዱ የዓየር ንብረትን በመበከል ምንም ወይም ትንሽ ጫና የምታሳርፈዉ፣ ነገር ግን ሌሎች ባደረሱት ብክለት ብዙ የተጎዳቺዉ የአፍሪቃና የሕዝቧ ችግር ነበር።ናጄሪያዊቱ የተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋች ኦዱዱአባሲ አሱኮ ከጉባኤተኞቹ አንዷ ናት።የዛሬ ሶስት ዓመት ግብዣዉ የደረሳት በCOP30 ጉባኤ ላይ እንድትካፈል ነበር።በመጋበዟ ተደሰተች፣ ዝግጅቷንም ቀጠለች።የደስታዋ ምክንያት፣ የዝግጅቷም ትኩረት በተጋበዘችበት ትልቅ ጉባኤ ላይ ለመካፈል አልነበርም።«ትይዩዉ ጉባኤ እንደሚደረግ ስለማዉቅ እንጂ» ትላለች።
ቁጥጥር፣ ጥንቃቄ፣ ድብቅብድ የሌለበት ጉባኤ
«በሕዝብ ጉባኤ የሚሰማንን ለመናገር ነፃ ነን፣ገደብ የለብንም።» ትላለች አሱኩ።«በCOP ጉባኤ ሁሉም ነገር---የምትለብሰዉ ቲ ሸርት እንኳ ሳይቀር የሚወሰንልሕ በሌሎች ነዉ።» አከለች።
ትዩዩዉን ጉባኤ ያስተናገደዉ የፓራ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ኢነስ አንቶኒያ ሳንቶስ ሪቤይሮም የናይጄሪያዊቱን የተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋች አስተሳሰብ ይጋራሉ።
ጉባኤተኞቹ የተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋቾች፣ አጥኚዎች፣ አንጡራ ነዋሪዎች፣ የባሕላዊ እሴቶች፣ አሰራርና አመራረት ደጋፊዎች---- ዓይነታቸዉም እንደ ብዛታቸዉ ብዙ፣ መፈክር፣ ሙዚቃ፣ጥያቄ፣ ሰልፋቸዉም እንደ ጉባኤያቸዉ ርዕሶች ቅይጥ ነዉ።
የአፍሪቃ ድምፆች ለፍትሐዊ የአየር ንብረት
ናጄሪያዊቱ የተፈጥሮጥበቃ ተሟጋች ኦዱዱአባሲ አሱኮ ያዉ ጥቁር ናትና በሰልፍ፣ ጉባኤ ዉይይቱ መሐል በተደጋጋሚ ከጥቁር ብራዚላዉያን ማሕበረሰብ ጋር ትደባለቅ ነበር።«ኮሎምቦላስ» ተብለዉ የሚጠሩት ጥቁሮች ከአፍሪቃ በባርነት ተፈንግለዉ ብራዚል የሰፈሩ የጥንታዊ አፍሪቃዉያን ዝርያ ናቸዉ።በአብዛኛዉ የምዕራብ አዉሮጳና የአሜሪካ ባሪያ ፈንጋዮች በቅድመ፣ ቅም አያቶቻቸዉ ላይ ለዋሉት ግፍ ካሳ እንዲከፍሉ ይጠይቃሉ።
አሱኮም ሆነች ሌሎች አፍሪቃዉያን የጉባኤዉ ተሳታፊዎች የጥቁሮቹን የካሳ ጥያቄ ይደግፋሉ።ናጄሪያ ዉስጥ በተለይ ኒጀር ዴልታ ከሚባለዉ አካባቢ የሚወጣዉ ነዳጅ ዘይት በአካባቢዉ የሚያደርሰዉ ብከለትና በነዋሪዉ ላይ ያስከተለዉ ችግር «መወገድ አለበት ባይም» ናት አሱኮ።
የሴኔጋል የአሳ አጥማጆች ፈተና
ኢብራሒም ታይምሴናጋላዊ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ተሟጋች ነዉ።የአየር ንብረት ለዉጥ በሴኔጋል ባሕርና ባሕር ጠረፍ ላይ ያደረሰዉን ጉዳት ለማሳወቅ እንደ ጥሩ ማስረጃ የወሰደዉ የተጎዱ አካባቢዎችን የሚያሳዩ የፎቶ ግራፎች ትርዒት ማቅረብን ነዉ።«ሴኔጋል የአሳ ጥገኛናት» ይላል ኢብራሒም።ይሁንና ብዙ አሳ አስጋሪዎች እንድም ተሰድደዋል ወይም ሥራ እያጡ ነዉ» ይላል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በCOP ጉባኤ ላይ የተሳተፈዉ ሸርም አል ሼኽ-ግብፅ ባስተናገደችዉ ጉባኤ ነበር።«ሰማያዊ ቀጠና በሚባለዉ የጉባኤዉ ክፍል ባንኮች ተደርድረዉ ሳይ ገረመኝ፣ አናደደኝም።» አለ ኢብራሒ ለዶቸ ቬለ።«ባንኮች ደግሞ እዚሕ ምንያደርጋሉ ብዬ?» ።ብራዚል ዉስጥ በተለይ «የሕዝብ ጉባኤ» በተባለዉ ሁሉን አቀፍ ዘመቻ ላይ በመካፈሉና በሐገሩ ባሕር፣ ጠረፍና አሳ አስጋሪዎች ላይ የደረሰዉን ጉዳት ማስረዳት በመቻሉ ደስተኛ ነዉ።«ከሚረዱኝ ሰዎች ጋር እንዳለሁ ይሰማኛል» አለ።
ኩባንዮች ግብር ይክፈሉ
የደቡብ አፍሪቃ የአማራጭ መረጃና የልማት ማዕከል ባልደረባ ጄኮብ ኦሎፍሴን እንደሚለዉ በተለያዩ የአፍሪቃ ሐገራት የሚታየዉን አብዛኛዉን የአየር ንብረት መዛባት የሚያደርሱት ማዕድን አዉጪ ኩባንዮች ናቸዉ።ናይሮቢ ላይ ተሰይሞ የነበረዉ የተፈጥሮ ጉዳይ ጉባኤ በተለይ ማዕድን የሚያወጡ ኩባንዮች ለሚያደርሱት የአየር ብክለት ግብር መክፈል ወይም የሚደ,ረግላቸዉ ምሕረት መቀነስ አለበት የሚል ሐሳብ ተነስቶ ነበር።ጄኮብ ኦሎፍሴን እንደሚለዉ እሱና የባልደረቦቹ ጥረት የCOP30 ጉባኤ ዉሳኔን ከናይሮቢዉ ሐሳብ ጋር ማጣጣም ነዉ።
«በትክክል ማድረግ የፈለግነዉ ቤለም COP30 ጉባኤ ላይ በመደረግ ላይ ያለዉን ናይሮቢ ከሚደረገዉ ጋር ማገናኘት ነዉ።ታክስ መጣል የሚያስችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደንብ እንዲኖረዉ በሚደረገዉ ድርድር መግባባት እንዲኖር ነዉ።በግብርና በ,አየር ንብረት ለዉጥ መካከል ሥላለዉ ግንኙነት መናገር እንፈልጋለን።ማዕድን ለሚያወጡና ጋስ ለሚያምርቱ ኩባንዮች የሚደረገዉ የግብር ቅናሽ፣ የሚያጭበ,ረብሩት ግብርና የገንዘብ ልዉዉጡ፣ልማትና የአየር ንብረት ለዉጥ ሁነኛ ዉል ሊደረግባቸዉ ይገባል።»
የጊኒ ቢሳዉ ምሑር መልዕክት
ከጊኒ ቢሳዉ የተወከሉት የሥነ-ሕዝብ ምሁርና የተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋች ሚጉኤል ዴ ባሮስ በተለይ «የሕዝብ» የተባለዉ ትዩዩ ጉባኤ የአየር ንብረት ለዉጥን ለመቀነስ በሚደረገዉ ትግል ልዩ ሥፍራ ይኖረዋል የሚል ተስፋ አላቸዉ።ሐገራቸዉ ጎርፍ፣የበረሐ መስፋፋት፣ የአፈር መታጠብ እየተደጋገሙባት ለችግርም እያጋለጧት እንደሆነ ባሮስ አስታዉቀዋል።
በሕዝብ ጉባኤዉ የተካፈሉት ወገኖች በሚያደርጉት ጫና የሲቢል ማሕበራት የሚመሩት የተፈጥሮ ጥበቃ ፖሊሲ ለመንደፍ ከቻለና የሚገኘዉ ገንዘብ ዕዉቀትን ለማስረፅ ከዋለ ባሮስ እንደሚያምኑት የተፈጥሮ መዛባት የሚያደርሰዉ ጉዳት ይቀንሳል።
የናጄሪያ፣ የደቡብ አፍሪቃ፣ የሴኔጋል፣ የጊኒ ቢሳዉ፣ የቶጎና የሌሎቹም የአፍሪቃ ሐገራት የተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋቾች፣ ባለሙያዎችና ምሑራን ባንድ ነገር አንድ ናቸዉ።ከዚሕ ቀደም ከተደረጉ ጉባኤዎች ሁሉ በዘንድሮዉ ጉባኤ የአፍሪቃን ችግር ለተቀረዉ ዓለም ለማሳወቅ የተሻለ እድል አግኝተዉበታል-በሕዝብ ጉባኤ።
የኤል ፋሻር እልቂት፣ ዉገዝ፣ ምርመራና ማዕቀብ
ጥቅምት 23፣ 2025 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) የሰሜን ምዕራብ ሱዳንን ሥልታዊ ትልቅ ከተማ ኤል ፋሸርን የሚቆጣጠረዉ የሱዳን መከላከያ 6ኛ እግረኛ ክፍለ ጦር የፈጥኖ ደራሽ ጠላቱ የሰነዘረዉን ጥቃት ማክሸፉን አሳወቀ።የሥልታዊቱን ከተማ መዉጪ መግቢያ ለ500 ቀናት የዘጋዉ የፈጥኖ ደራሽ ጦር የጠላቱን መግለጫ አላመነም፣ አላስተባበለምም።ፈጥኖ ደራሹ ጦር ለሁለት ቀናት ድምፁን አጥፍቶ ወይም በወታደሮቹ ቋንቋ ሥልቱን ለዉጦ ሌላ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፈተ።
የአብዱረሒም ሐምዳን ዳጋሎ ድል-የአልፋሸሮች እልቂት
ጥቅምት 26 የፈጥኖ ደራሹ ጦር ተወርዋሪ ጓድ የጠላቱን ዋና ማዘዢያ ጣቢያ በጠበጠዉ።አናቱ የተፈረከሰበት መከላከያ ጦር ተናደ። ድል ለፈጥኖ ደራሽ ጦር።ከተማይቱን የተቆጣጠረዉን ጦር ያዘዙት የፈጥኖ ደራሹ ጦር ምክትል አዛዥ አብዱልረሒም ሐምዳን ዳጋሎ ናቸዉ።
«የ6ኛዉ እግረኛ ክፍለ ጦር ዋና ዕዝ አሁን በታሲስ መንግሥት እጅ ነዉ።»
«የታሲስ መንግሥት» የሚሉት የፈጥኖ ደራሹ ጦር ከሌሎች ተባባሪዎቹ ጋር ሆኖ ናይሮቢ-ኬንያ ላይ የመሠረቱት ትዩዩ መንግሥት ነዉ።አብዱረሒም ሐምዳን ዳግሎ ደግሞ የፈጥኖ ደራሹ ጦር ዋና አዛዥ የጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሐሚቲ) ወንድም ናቸዉ።
«የሱዳን ሕዝብ ኤል ፋሸር ላይ ላገኘዉ ድል እንኳን ደስ ያለሕ እንላለን።በኤል ፋሸር ነፃ መዉጣት።ሱዳንን እስከ ፖርት ሱዳን ድረስ ነፃ እናወጣለን።»
የኤል ፋሻር መያዝ ለፈጥኖ ደራሹ ጦር ድል፣ ለመከላከያዉ ጦር ሽንፈት ሊሆን ይችላል።ለሱዳን ሕዝብ በጣሙን ለከተማይቱ ነዋሪ የተጨማሪ ዕልቂት፣ ግፍ፣ ሥደት እንጂ በርግጥ ደስታ ሊሆን አይችልም። የሱዳን ሕዝብ ከኤል ፋሻረም በፊት ከ150 ሺሕ በላይ ወገኖቹ አልቀዉበታል። የፈጥኖ ደራሽ ጦር ኤል ፋሸርን ከተቆጣጠረ ወዲሕ ደግሞ የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ታጣቂዎቹ፣ ሕፃን ካዋቂ፣ በሽተኛ ካስታማሚ ሳይለዩ ይገድላሉ።ሴቶቹን ይደፍራል።ዓለምም ሟች-ስደተኛ ይቆጥራል።
የሟች፣ ረሐብተኛ ሥደተኛዉ ቁጥር እየጨመረ ነዉ
የርዳታ አቀባዮችና የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉትየፈጥኖ ደራሹ ጦር ኤል ፋሸር ከተቆጣጠረ ወዲሕ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል ወይም ደብዛቸዉ ጠፍቷል። በርካታ ሴቶችና ልጃገረዶች ተደፍረዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች ትናንት እንዳሉት ፈጥኖ ደራሹ ጦር ኤል ፋሸርን ከተቆጣጠረ ወዲሕ ከከተማይቱ የተሰደደዉ ሕዝብ ቁጥር ከ100 ሺሕ በልጧል።
«የሱዳንና ሰሜን ዳርፉር ዉስጥ የሚደርሰዉን አሰቃቂ ሁኔታ ሥንመለከት፣ የሰብአዊ ጉዳይ ባልደረቦቻችን እንደነገሩን የፈጥኖ ደራሹ ጦር ኤል ፋሸር ከተቆጣጠረ ከጥቅምት ማብቂያ ወዲሕ ብቻ ከከተማይቱና ካካባቢዋ የተ,ሰደዱት ሰዎች ቁጥር ከ100 ሺሕ በልጧል። ብዙ ሰዎች ግን ያሉበት አይታወቅም።ከኤል ፋሻር ማምለጥ የቻሉት ሰዎች የሰፈሩበት አካባቢ ለመኖር ምን ያሕል አስከፊ እንደሆነ መገመት ትችላላችሁ።እኛና የሰብአዊ ርዳታ አቀባይ ባልደረቦቻችን ንፁሕ ዉኃ፣ ምግብ የጤና አገልግሎት ለማዳረስ እጣርን ነዉ።»
ዉግዘትና ምርመራና ማዕቀብ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት፣ የድርጅቱ የሰብአዊ መብት ምክር ቤት፣ የተለያዩ መንግሥታትና ድርጅቶች ኤል ፋሻር ዉስጥ የሚፈፀመዉን ግፍ አዉግዘዋል። ባለፈዉ ሳምንት የተሰበሰበዉ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ኤል ፋሻር ዉስጥ የተፈፀመዉ ግፍ በገለልተኛ መርማሪዎች እንዲጣራ ወስኗል። የአዉራጳ ሕብረትም ኤል ፋሸር ዉስጥ የሚፈፀመዉን ግፍ አዉግዞ በፈጥኖ ደራሹ ጦር ምክትል አዛዥ በ,አብዱረሒም ሐምዳን ዳግሎ ላይ ማዕቀብ ጥሏል።
የሕብረቱ ኮሚንሽን ቃል አቀባይ አኖዋር ኤል አኖኒ ትናንት እንዳስታወቁት ማዕቀቡ፣ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ወንጀል የሚፈፅሙ ኃይላትን በቸልታ እንደማያልፍ ግልፅ መልዕክት ያስተላልፋል።
«የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር የፈፀና የሚፈፅመዉን ግፍ የአዉሮጳ ሕብረት አጥብቆ ያወግዛል።ለእነዚሕ ወንጀሎች አፀፋ ለመስጠትም፣ በፈጥኖ ደራሹ ጦር ምክትል አዛዥ በአብዱረሒም ሐምዳን ዳጋሎ ላይ ማዕቀብ ጥሏል። ይሕ ርምጃ ወንጀል የሚፈፀሙ ተጠያቂዎችን ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በችልታ እንደማያልፋቸዉ ግልፅ መልዕክት ያስተላልፋል።»
የአዉሮጳ ሕብረት በስም ያልጠቀሳቸዉ ግን «የዉጪ ተዋንያን» ያላቸዉ ወገኖች ለፈጥኖ ደራሹ ጦር የጦር መሣሪያና ሌሎች ድጋፎችን ማድረጋቸዉን እንዲያቆሙ አሳስቧል።የፈጥኖ ደራሹን ጦር፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ቻድ፣ የሊቢያዉ የጦር አበጋዝ ኸሊፋ አፍጣር የሚመሩት ቡድንና ሌሎች ያካባቢዉ መንግስታት ይደግፉታል ይባላል።
የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የጆ ባይደን መስተዳድር በሱዳን መከላከያ ጦርም በፈጥኖ ደራሹ ጦርም አዛዦች ላይ ማዕቀብ ጥሏል። የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ደግሞ የፈጥኖ ደራሹ ጦር የዘመቻ መምሪያ አዛዥንና በምዕራብ ዳርፉር የፈጥኖ ደራሽ ጦር አዛዥን በማዕቀብ ቀጥሏል። ዉግዘት፣ ምርመራ፣ ዛቻ ማዕቀቡ ግን መቶ ሺዎችን የሚፈጀዉን ጦርነት ለማስቆም የተከረዉ ነገር የለም።
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ