1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪቃ፤ የSADC ጉባኤ፣ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በሳሕል አካባቢ ሐገራት

ቅዳሜ፣ ኅዳር 7 2017

ሞዛምቢክ ላይ የሚንተከተከዉ ቀዉስ ያሠጋት ደቡብ አፍሪቃ ከሞዛምቢክ ጋር የሚያዋስናትን አብዛኛ ድንበሯን ዘግታለች።የደቡብ አፍሪቃ የከባድ ጭነትና የባቡር ሠራተኞች ማሕበር እንዳስታወቀዉ ድንበሮቹ በመዘጋታቸዉ ደቡብ አፍሪቃ በቀን 550 ሺሕ ዶላር ገቢ እያጣች ነዉ

መሪዎቹ ከዛሬ ጀምሮ ለ4 ቀን የሚያደርጉት ያሁኑ ልዩ ጉባኤ የተጠራዉ በኮንጎ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ነበር።ይሁንና የሞዛምቢክ ቀዉስ ቀዳሚዉን ትኩረት ወስዷል
የደቡባዊ አፍሪቃ የልማት ማሕበረሰብ (SADC) አባል ሐገራት መሪዎች ባለፈዉ መስከረም ሐራሬ ዚምባቡዌ ዉስጥ ተሰብስበዉ ነበር።ምስል Tafara Mugwara/Xinhua/IMAGO

ትኩረት በአፍሪቃ፤ የSADC ጉባኤ፣ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በሳሕል አካባቢ ሐገራት

This browser does not support the audio element.

 

የደቡባዊ አፍሪቃ  የልማት ማሕበረሰብ (SADC) አባል ሐገራት መሪዎችና ተወካዮች ዛሬ ሐራሬ-ዚምባቡዌ ዉስጥ ለልዩ ጉባኤ ተሰብስበዋል።የSADC የወቅቱ ሊቀመንበር የዚምባቡዌ ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት ጉባኤተኞች ሞዛምቢክ ዉስጥ በቅርቡ ከተደረገዉ ምርጫ በኋላ ለተቀሰቀሰዉ ፖለቲካዊ ቀዉስ መፍትሔ መፍትሔ ያፈላልጋሉ።የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጦርነትና አለመረጋጋትም የጉባኤተኞቹ ሁለተኛ ትልቅ ርዕሥ ነዉ።የሳሕል አካባቢ ሐገራት ደግሞ በዓለም ኃያል ሐገራት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎች ተጥለቅልቀዋል።ሁለት ርዕሶች በየተራ እንቃኛለን።

SADC በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የደቡባዊ አፍሪቃ የልማት ማሕበረሰብ ያሁኑ ጉባኤ ዋና ትኩረት የሆኑትን ሞዛምቢክና ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክን ጨምሮ ከደቡባ አፍሪቃ እስከ ሲሼልስ የሚገኙ 16 አባል ሐገራትን ያስተናብራል።ማሕበሩ ምጣኔ ሐብታዊ ቢሆንም በየአባል ሐገራቱ በየጊዜዉ የሚፈጠረዉን ፖለቲካዊ ቀዉስና ግጭት ለማቃላል ሲባትል ዓመታት አስቆጥሯል።

መንበሩን ፕሪቶሪያ ያደረገዉ የፀጥታ ጥናት ተቋም (ISS) የፖለቲካ ተንታኝ ፒርስ ፒጉዉ እንደሚሉት ያሁኑ ልዩ ጉባኤ መጀመሪያ የተጠራዉ፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክን የሚያመሰቃቅለዉን ጦርነት ለማስቆም ማሕበሩ የወሰዳቸዉን ርምጃዎች ለመገምገም ነበር።

«የSADC ጉባኤ መጀመሪያ ላይ የተቃደዉ ሥለ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ለመነጋገር ነበር።»

የSADC አባል ሐገራት ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዉስጥ በሺ የሚቆጠር ጦር ኃይል አስፍረዋል።ጦሩ ከኮንጎ ጦር ኃይል ጋር በመሆን በሩዋንዳ የሚደገፈዉን M23 ተብሎ የሚጠራዉን ቡድንና ሌሎች አማፂ ኃይላትን ይወጋል።ይሁንና ባለፈዉ ጥቅምት ሞዛምቢክ ዉስጥ ከተደረገዉ ምርጫ ወዲሕ የተቀሰቀሰዉ ግጭትና ቀዉስ ጉባኤተኞች የመጀመሪያ ርዕሳቸዉን ሁለተኛ-በፊት ያልታሰበዉን አንደኛ አደረጉት-ፒጉዉ እንደሚሉት።

               

«ይሁንና ሞዛምቢክ ዉስጥ ባለፈዉ ወር ከተደረገዉ ምርጫ ወዲሕ በተፈጠረዉ ቀዉስ ምክንያት ጉባኤተኞች ለሞዛምቢክ ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተዋል።ሳዴክ ጉዳዩን ያጤናል።ወይም ቢያንስ የሞዛምቢክ ፕሬዝደንት የሚሰጡት ማብራሪያ አድምጦ ሥለሚወስዱት ርምጃ ይነጋገራል።»

ሞዛምቢክ ዉስጥ በተደረገዉ ምርጫ ዉጤት ያስከተለዉ ዉዝግብና ግጭት በሰዉ ሕይወትና አካል ላይ ካደረሰዉ ጉዳት በተጨማሪ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት አዉድሟልምስል Alfredo Zuniga/AFP

የሞዛምቢክ ቀዉስና የደቡብ አፍሪቃ ሥጋት

ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ሑዩማን ራይትስ ዋች እንዳስታወቀዉ ሞዛምቢክ ዉስጥ ባለፈዉ ጥቅምት የተደረገዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ዉጤት ባስከተለዉ ዉዝግብና ግጭት 30 ሰዎች  ተገድለዋል።የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎችን የአደባባይ ሰልፍ ለመበተን መንግሥት በየከተማዉ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር የፖሊስና የጦር ሠራዊት ባልደረቦችን አስፍሯልም።

ይሁንና በምርጫዉ በሥልጣን ላይ ባለዉ የፍሬሊሞ ፓርቲ ዕጩ በዳንኤል ቻፖ ተበልጠዋል የተባሉት  ለሞዛምቢክ ልማት የተስፈኞች ፓርቲ (በፖርቹጋልኛ ምሕፃሩ PODEMOS) ዕጩ ቬናንሲዮ ሞንድላኔ ደጋፊዎቻቸዉ ተጨማሪ ሰልፍና አድማ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።የገዢዉን ፓርቲ ርምጃ ለመቀልበስ «የሐገሪቱን ሁለንታናዊ እንቅስቃሴ እናሽመደምዳዋለን» በማለትም ዝተዋልም ዝተዋል።

ሞዛምቢክ ላይ የሚንተከተከዉ ቀዉስ ያሠጋት ደቡብ አፍሪቃ ከሞዛምቢክ ጋር የሚያዋስናትን አብዛኛ ድንበሯን ዘግታለች።የደቡብ አፍሪቃ የከባድ ጭነትና የባቡር ሠራተኞች ማሕበር እንዳስታወቀዉ ድንበሮቹ በመዘጋታቸዉ ደቡብ አፍሪቃ በቀን 550 ሺሕ ዶላር ገቢ እያጣች ነዉ።

በSADC እና በታዛቢዎቹ ላይ የሚሰነዘረዉ ትችት አይሏል

የዚምባቡዌ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሊንዳ ማሳሪራ ለሞዛምቢክም ሆነ በሌሎች አባል ሐገራት በምርጫ ዉጤት ሰበብ ለሚነሱ ዉዝግቦች መፍትሔ አይሰጥም በማለት SADCን ይወቅሳሉ።በግሪጎሪያኑ አምና 2023 ዚምባቡዌ ዉስጥ በተደረገዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ተቃዋሚዉን ፓርቲ ወክለዉ የተወዳደሩት ወይዘሮ ማሳሪራ እንደሚሉት የምርጫ ዉዝግቦች በተነሱ ቁጥር SADC ሐላፊነቱን ባግባቡ አይወጣም።

«ሳዴክ ሐላፊነቱን ባግባቡ አይወጣም።የምርጫ ዉዝግብ በተነሳ ቁጥር ሳዴክ ሁልጊዜ እንዳለመጠ ነዉ።የምርጫ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር የሳዴክ አቋም እንዳጠያየቀ ነዉ።»

የሞዛምቢክን ምርጫ የተከታተለዉ የSADC የታዛቢዎች ቡድን (SEOM) የምርጫዉን ሒደት አወድሶታል።የአዉሮጳ ሕብረትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ግን ምርጫዉ ከፍተኛ መዛባት እንደነበረበት አስታዉቀዋል።የSADC ታዛቢ ቡድን የምርጫዉን ሒደት ማወደሱን የሞዛምቢክ ተቃዋሚዉ ፓርቲ አጥብቆ ነቅፎታል።

በሞዛምቢኩ ምርጫ ማሸነፋቸዉ የተነገረዉን የገዢዉ ፓርቲ ዕጩ ዳንኤል ቻፖን ቀድመዉ እንኳን ደስ አለዎት ካሉ መሪዎች የወቅቱ የSADC ሊቀመንር፣ያሁኑ ጉባኤ መሪና የዚምባቡዌ ፕሬዝደንት ኤምርሰን ምናንጋግዋ አንዱ ናቸዉ።የምናንጋግዋ «የእንኳን ደስ ያለዎ» መልዕክት ማፑቶ የደረሰዉ የሞዛምቢክ የምርጫ ኮሚሽን የምርጫዉን ዉጤት በይፋ ከማሳወቁ በፊት ነዉ።

ምናንጋግዋ ተሽቀዳድመዉ የገዢዉን ፓርቲ ዕጩ ድል ማወደሳቸዉን ተቃዋሚዉ ፓርቲ አጣጥሎ ነቅፎታል።ነገሩን ይበልጥ ያወሳሰበዉ ደግሞ የየሞዛምቢክ ተቃዋሚ ፓርቲ ያቀረበዉን አቤቱታ የሐገሪቱ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት መርምሮ ዉሳኔ ከመስጠቱ በፊት ምናንጋግዋና ሌሎች የ SADC አባል ሐገራት መሪዎች ለ«እንኳን ደስ አለዎት» መልዕክት መሽቀዳደማቸዉ ነዉ።

ማፑቱ-ሞዛምቢክ ርዕሰ ከተማ ዉስጥ የተቃዋሚዉ ፓርቲ ደጋፊዎች የምርጫዉን ዉጤት በመቃወም ያደረጉት ተቃዉሞምስል Siphiwe Sibeko/REUTERS

የSADC አባል ሐገራት ልዩነት

                       

ለምርጫዉ ዉጤት እስካሁን እዉቅና ያልሰጡ የሳዴክ አባል መንግሥታት ብዙ ናቸዉ።የፖለቲካ ተንታኝ ፒርስ ፒጉዉ እንደሚሉት ከዛሬዉ ጉባኤ ተካፋዮች መካከል «የአንጎላ፣የታንዛኒያ፣ የደቡብ አፍሪቃና የዚምባቡዌ መሪዎች የፍሪሊሞ ፓርቲና የዕጩዉን ድል ተቀብለዉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።ሌሎቹ ግን ሒደቱ እስኪያበቃ ድረስ ዝምታን የመረጡ መስለዋል።»

ታዛቢዎች እንደሚሉት ጉባኤተኞች ልዩነታቸዉን ለማጥበብ ብዙ መድከም አለባቸዉ።ይሁንና ጉባኤተኖች በሞዛምቢክ ምርጫ ዉጤት ላይ የተለያየ አቋም መያዛቸዉና ጉዳዩን ዋና ርዕሳቸዉ ማድረጋቸዉ ለተቃዋሚዎቹ የPODEMOSና የሬናሞ ፓርቲዎች የሩቅም ቢሆን ጥሩ ተስፋ ነዉ።ግን ተቃዋሚዎቹ ካወቁበት ይላሉ የፖለቲካ ተንታኝ ፒርስ ፒጉዉ

«(በጉባኤዉ) ጠንካራ የተቃዉሞ ድምፆች የመሰማት ዕድል አላቸዉ።የሞዛምቢክ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች  አጋጣሚዉን ተጠቅመዉ በዚሕ ልዩ ጉባኤ ለሚካፈሉት ተፅዕኖ ፈጣሪ የሳዴክ አባላት፣ድምፃቸዉን ማሰማት መቻል-አለመቻላቸዉ ግን ሲሆን ይታያል።»

የዚምባቡዌ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሊንዳ ማሳሪራ የሞዛምቢክ ሰላም መታወክ ብዙዎቹን የአካባቢዉን ሐገራት ለችግር ይዳርጋል ይላሉ።አላበሉም።ወደብ አልባዎቹ የሳዴክ አባል ሐገራት ዜምባቡዌ፣ ዛምቢያ፣ ማላዊና ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የሞዛምቢክ ወደቦች ተጠቃሚዎች ናቸዉ።

 

የሳሕል አካባቢ ሐገራት የመገናኛ ዘዴ ዘመቻ

የደቡባዊ አፍሪቃ ሐገራት የሞዛምቢክ ምርጫ ዉዝግብና የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጦርነት መትሔ የሚያገኙበትን መንገድ ለማፈላለግ ሲጥሩ የምዕራብ አፍሪቃ በጣሙን የሳሕል አካባቢ ሐገራት ደግሞ በመገናኛ ዘዴዎች ፕሮፓጋዳ መጥለቅለቃቸዉ እያነጋገረ ነዉ።የአፍሪቃ ሥልታዊ ጥናት ማዕከል፣ አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ድንበር የለሽ ዘጋቢዎችና ለ ኤቬንሜ የተባሉ ዓለም አቀፍ፣ አሐጉራዊና ብሔራዊ ተቋማት እንደሚሉት በሳሕል አካባቢ ሐገራት የሚነዛዉ ፕሮፓጋንዳ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ ነዉ።

ተቋማቱ አንዳዴ በጋራ ብዙ ጊዜ በየፊናቸዉ አደረግን ያሉት ጥናት እንደሚያመለክተዉ በተለይ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከ2020 ጀምሮ መፈንቅለ መንግስት በተደረገባቸዉ ሐገራት በአብዛኛዉ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጨዉ የሐሰት፣ የተጋነነና ሆን ተብሎ የተዛባ መረጃ በየሐገራቱና በተቀረዉ ዓለም ያለዉን እዉነታ እየቀበረዉ ነዉ።

አብዛኞቹ የተሳሳቱ መረጃዎች የሚመነጩት ከሩሲያ ነዉ

ለስትራቴጂ ጥናት  የአፍሪቃ ማዕከል እንደሚለዉ አብዛኛዉ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ወይም ለዘመቻዉ የሚዉለዉ የሐሰት መረጃ ምንጭ የዉጪ ኃይላት ናቸዉ።ከዉጪ ከሚደረገዉ ዘመቻ 60 በመቶዉ ደግሞ የሩሲያ ነዉ።የአፍሪቃ ማዕከል ለሥትራቴጂ ጥናት እንደሚለዉ ፕሮፓጋንዳዉ ምዕራባዊ መንግስታትን በማራከስ፣ ሩሲያን በመደገፍ ላይ ያነጣጠረ ነዉ።

በአጥኚዉ ተቋም መረጃ መሠረት ሩሲያ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከ2018 ወዲሕ በሳሕል አካባቢ ሐገራት በተለይም ማሊ፣ ቡርኪናፋሶና ኒዠር ዉስጥ 19ኝ ዘመቻዎች አድርጋለች።በነዚሕ ሐገራት በተከታታይ ሥልጣን የያዙት ወታደራዊ ሁንታዎች የምዕራባዊ ሐገራት ኃይላትን ከየሐገራቸዉ ካበረሩ ወዲሕ ሩሲያ በየሐገራቱ ዉስጥ ያላትን ተፅዕኖ ማጠናከር ትፈልጋለች።

የአፍሪቃ የአጣሪዎች ሕብረት የተባለዉ ተቋም ባልደረባ ቢላል ታይሩ እንደሚሉት ሩሲያ ምዕራባዉያኑን መንግስታት ለማሳጣት አጋጣሚዉን እየተጠቀመች ነዉ።

«እናዉቃለን።የሩሲያ አቋም ምዕራባዉያኑን የሚፃረር ነዉ።ይሕ የፀረ-ምዕራባዉያን አስተሳሰብ ማዕበል መሆኑንም እናዉቃለን።ሥለዚሕ ሩሲያ በርካታ የተሳሳተ መረጃዎች ዘመቻዎችን እያቀለጣጠፈች ነዉ።»

በ2020 በሩሲያ መንግሥት ይደገፋል የሚባለዉ የጦር ኃይል ኩባንያ ቫግነር ወታደሮቹን ማሊ ዉስጥ ማስፈሩ ከመረጋገጡ ከጥቂት ወራት በፊት ምዕራባዉያንን የሚጣጥለዉ ቅስቀሳ ተባብሶ ነበር።የአሜሪካዉ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ መድረክ ፌስ ቡክ እስካሁን ድረስ 3 አምደ መረቦችን ዘግቷል።ከሶስቱ ሁለቱ ከሩሲያ ጋር ግንኙነት ያላቸዉ ናቸዉ ተብሏል።

ዲሚትሪ ዙፌሪይ «ሁሉም ዓይኖች በቫግነር ላይ» የተሰኘዉ ስብስብ አባል፣ ጋዜጠኛም ነዉ።የሩሲያና የደጋፊዎችዋን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻን «አዲዮስ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ እንኳን ደሕና መጣሽ» ከሚለዉ መፈክር መሰል መልዕክት ጀምሮ እናዉቀዋለን ይላል።መልዕክቶቹ በፈረንሳይና በተባባሪዎችዋ  ምዕራባዉያን መንግሥታት መርሕና ርምጃ ቅሬታ የገባዉ ሕዝብ ድጋፉን ለሩሲያ እንዲሰጥ አድርጎታል-እንደ ዲሚትሪ  ዙፌሪይ

«እንዲያዉ በቀላሉ መመዘኛ ሩሲያ ለምሳሌ እንደ ማሊና ቡርኪናፋሶ ባሉ ሐገራት የሕዝብ አስተያየትን መቀየሩ ተሳክቶላታል።»

በሕዝብ አስተሳሰብ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚደረገዉ ጥረት

መፈንቅለ መንግሥት በተደረገባቸዉ ሐገራት የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሚደረገዉ ዘመቻ ሌሎች መንግስታትም ተሳታፊዎች ናቸዉ።አጥኚዎቹ እንደሚሉት ከሩሲያ በተጨማሪ የቻይናና የቀጠር መንግሥታትም የየራሳቸዉን ተፅዕኖ ለማሳረፍ እየታገሉ ነዉ።

መፈንቅለ መንግሥት በተደረጋባቸዉ የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢ ሐገራት ማሊ፣ቡርኪና ፋሶና ኒዠር አብዛኞቹ የፈረንሳይ መገናኛ ዘዴዎች ተዘግተዋል።ምስል Olympia De Maismont/AFP

ጋዜጠኛና የመረጃ ጉዳይ ተንታኝ ሐሮና ሲምቦ እንደሚለዉ ሩሲያ፣ ቻይናና ቀጠርን የመሳሰሉት አዳዲስ ኃይላት በከፈቱት ዘመቻ ባንድ በኩል አንዳቸዉ ከሌላቸዉ በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም ከነባሮቹ  ተፅዕኖ ፈዛጣሪዎች ከምዕራባዉያን ጋር እየተሻኮቱ ነዉ።ጎልቶ የሚታየዉ ግን በነባሮቹና በአዳዲሶቹ ኃይላት መካከል የደራዉ ፉክክር ነዉ።

«በተቀናቃኝ ተዋኞቹ መካከል ጠንካራ ፍትጊያ እየተደረገ ነዉ።ተፅዕኖቸዉን መቀጠል በሚፈልጉት ነባሮቹና በአዳዲሲቹ ዓለም አቀፍ ኃይላት መካከል ፉክክሩ ቀጥሏል።»

ፉክክሩ እየጠናከረ መቀጠሉ ለየሐገሩ ጋዜጠኞች በተለይም ገለልተኛና ሚዛናዊ ዘገባዎችን ለማሰራጨት በሚፈልጉት ጋዜጠኞች ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና እያደረሰ ነዉ።ወትሮም ቢሆን የማሊ፣የቡርኪና ፋሶና የኒዤር ወታደራዊ ገዢዎች ሥርአታቸዉን ለሚተቹ ጋዜጠኞች ምሕረት የላቸዉም።ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች እንደሚለዉ በሶስቱ ሐገራት በመቶ የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች «ሐገራቸዉን የሚጠሉ» ወይም «ከሐዲዎች» እየተባሉ ተወግዘዋል።የታገቱ እንዳሉም ተዘግቧልም።

ጋዜጠኛ ማሊክ ኮንናቴ መፈንቅለ መንግሥት በተደረገባቸዉ ሐገራት ያሉ ጋዜጠኞች ባሁኑ ወቅት ያላቸዉ ምርጫ ሶስት ነዉ ይላል። ከወታደራዊዉ ሁንታ ጋር ሰልፋቸዉን ማሳማር-አንድ፣ ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርገዉ መተዉ-ሁለት ወይም መሰደድ-ልክ እንደኔ ይላል ማሊክ ሶስተኛዉን አማራጭ።

«ጋዜጠኞች ዝም ለማለት፣ ወይም መስመሩን ለመከተል አለያም እኔ እንዳደረግሁት ከሐገር ለመሰድድ መወሰን አለባቸዉ።(ገለልተኛና ሚዛናዊ) መረጃ ለማቅረብ የሚሞክሩ ሁሉ ሐገሪቱን እንደሚያዉክ ጠላት ይቆጠራሉ።»

የጆኦ ፖለቲካ ፉክክር ሰለባ

በሳሕል አካባቢ ሐገራት የሚታየዉ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ የገለልተኛ መገናኛ ዘዴዎችንና የጋዜጠኞችን ሕልዉና ለአደጋ አጋልጦታል።በሕብረተሰቡም ዘንድ ዉዥንብርና ግራ መጋባት ማስከተሉ አልቀረም።ዳካር-ሴኔጋል የሚገኘዉ የጋዜጠኞች ኮሌጅ የበላይ ኃላፊና መምሕር ሐማዶ ቲድያኔ ስይ የገለልተኛ መገናኛ ዘዴዎችን መዳከምና በሕዝብ ዘንድ የተፈጠረዉን ግራ መጋባት ለማረቅ የሚረዳ መልዕክት የሚሰራጭበት አምደ መረብ ከፍተዋል።

ስይና ባልደረቦቻቸዉ አንዳዴ ሥለ ተሳሳተ መረጃ ምክንያት፣ ደረጃዉና መዘዙ ክርክሮችን ያሰራጫሉ።ይሁንና በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሰፊዉ የሚሰራጨዉን የተቀናቃኝ ኃይላት ፕሮፓጋንዳ መቋቋም መቻላቸዉን ይጠራጠራሉ።ምክንያቱም ጉዳዩ ከጋዜጠኞችም፣ ከመገናኛ ዘዴ ነፃነት ተቆርቋሪዎችም፣ አልፎ ተርፎ «ከትናንንሽ ሐገሮቻችንም» ባላይ  የመልከዓ ምድረዊ-ፖለቲካዊ ሽኩቻ ዉጤት ነዉና-ይላሉ-መምሕሩ።

                               

«ጉዳዩ ከኛ ትናንሽ ሐገራት በላይ የሚሔድ ነዉ።ይሕ በጣም፣በጣም አሳሳቢ የመልክዓ-ምድራዊ ፖለቲካዊ ጉዳይ ነዉ።በዚሕ ጠመን የተለያዩ ኃይላት በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ አማካይነት ሰፊዉን ሕዝብ ባሻቸዉ መንገድ ማስኬድ እንደሚችሉ ሁሉም ሰዉ የሚያዉቀዉ ጉዳይ ነዉ።እንዳለመታደል ሆኖ አንዳዴ ሰፊዉ ሕዝብም ብዙም አያዉቅም።»

የጋዜጠኝነት መምሕሩ ተስፋ አልቆረጡም።ሰፊዉ ሕዝብ የሚሉት ማሕበረሰብ ሥለገለልተኛ መገናኛ ዘዴዎች ጥቅም፣ ሥለጋዜጠኞች ብቃት፣ ሥነ ምግባር ሥለተሳሳቱና ሥለተዛቡ መረጃዎች ምንነት፣ሥለሚያስከትሉት ጉዳት ግንዛቤ  እንዲኖረዉ ማስተማር አለብን ይላሉ።ግን በምን አቅም?

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW