1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ትኩረት በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 19 2015

ተቃዉሞ ሰልፈኛዉ ግን ዓላማዉ ግቡን ሳይመታ ወደየቤቱ ለመግባት የፈለገ አይመስልም።ከሰልፉ አስተባባሪዎች አንዷ ራኒያ አብዱል አዚዝ ህዝቡ ድፍን አንድ ዓመት እንደ ሐገር ባንድነት በመቆሙ ትኮራለች።

Sudan | Proteste in Khartum
ምስል፦ Ashraf Shazly/AFP/Getty Images

የሱዳን መፈንቅለ መንግስት አንደኛ ዓመት፣ የኦሚክሮን አግኚዎች ሽልማት

This browser does not support the audio element.

ሱዳን ዉስጥ መንግስትን ለመቃወም፣ መሪን ለማዉገዝ፣ ወይም ዳቦና ፉል ጥየቃ መሰለፍ እንግዳ አይደለም።በ2018 ማብቂያ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የተጀመረዉ የተቃዉሞ ሰልፍ ግን ካፍታ እፎይታ በስተቀር አላባራም።የዳቦና ባቄላ መወደድን፣ የፕሬዝደንት ዑመር አል በሽርን አስተዳደርን፣ አልበሽርን ከስልጣን ያስወገዱ ጄኔራሎችን በመቃወም፣ ሉአላዊ ምክር ቤትን በመደገፍ ሲደረግ የነበረዉ  ሰልፍ አምና ጥቅምት በሌላ ተተካ

ጥቅምት 25 2021 የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን በጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ የሚመራዉን የሲቢል የሽግግር መንግስት አስወገዱ።ጠቅላይ ሚንስትሩንና ሌሎች ባለስልጣናትን አሰሩ።የተቃዉሞ ሰልፉም ባዲስ ቁጣ ናረ።

                                    

በየከተማዉ አደባባይ የሚወጣዉ ሕዝብ «ዴሞክራሲ ለሱዳን»፣ «ከጦሩ ጋር ስልጣን መጋራት አያስፈልግም» ጦሩ ወደ ምሽጉ ይመለስ» እያለ ይጮኽ ገባ።ገዢዎቹ አልሰሙትም-ሕዝቡም ገዚዎቹን አልሰማም።የፀጥታ አስከባሪዎችን ግድያ፣አፈሳ፣ እስራት እየተጋፈጠ የአደባባይ ጩኸት ትግሉን ቀጠለ።ባለፈዉ  ሮብ ዓመት ደፈነ።

የሱዳን ዶክተሮች የተባለዉ ማሕበር እንዳስታወቀዉ ባለፈዉ አንድ ዓመት መፈንቅለ መንግስቱን ለመቃወም አደባባይ በወጣዉ ሕዝብ ላይ ፀጥታ አስከባሪዎች በወሰዱት ርምጃ በትንሽ ግምት 118 ሰዎች ተገድለዋል።ከ7 ሺሕ በላይ ቆስለዋል።በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ሰልፈኞች እየታሰሩ ተፈተዋል።ሰልፉ ግን አላባራም።እንዲያዉም በካርቱም የጀርመኑ የፍሪድሪሽ ኤበርት ጥናት ተቋም የበላይ ክርስቲነ ረህርስ እንደሚሉት የአደባባይ ተቃዉሞ ሰልፍ እንደ መደበኛ ስራ በፈረቃ እየተደረገ ነዉ።

የሱዳን ወታደራዊ መሪ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐንምስል፦ SDSTS/EBU

                                           

«ባለፈዉ ዓመት ጥቅምት 25 መፈንቅለ መንግስት ከተደረገ ወዲሕ በሲቢል ማሕበረሰቡ የሚዘጋጅ በተለይም ወጣቶች የሚበዙበት የተቃዉሞ ሰልፍ በየሳምንቱ  ብዙ ቀናት ይደረጋል።በየወሩ የተቃዉሞ ሰልፍ የሚደረግባቸዉ ቀናትን የሚጠቁም ቀን መቁጠሪያ ይደርሰናል።ይሕ ማለት ሰዉ ሰልፍ እንዲወጣ ብቻ ሳይሆን ወደ ስራ የምንሔድ ሰዎች መንገድ ከመዘጋቱ በፊት ወደምንፈልግበት እንድንሔድም ጭምር ነዉ።»

ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን ሥልጣናቸዉን በሕዝብ ለሚመረጥ መንግስት ለማስከረከብ ቃል ከገቡ ሶስት ወር አለፋቸዉ።የሱዳን የፖለቲካ አጥኚዎች እንደሚሉት አል ቡርሐን የሚሹት ሕዝቡ በነፃነት የሚመርጠዉ መሪ ወይም ምክር ቤት ሳይሆን ጦር ኃይሉን የሚደግፍና በጦር ኃይሉ የሚደገፍ መንግስት ነዉ።የሱዳን መፈንቅለ መንግስትና የስቪሎች ምላሽ

አል ቡርሐን በሚመሩት ወታደራዊ ቡድን እና  በሲቢል  የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በተደጋጋሚ የተደረገዉ ድርድርም  ያመጣዉ ዉጤት የለም።መንበሩን ለንደን ብሪታንያ ያደረገዉ ኢንተርናሽናል ኢንተረስት የተሰኘዉ አጥኚ ተቋም ባልደረባ ሳሚ ሐምዲ እንደሚሉት የሱዳን ፖለቲከኞች ለምርጫ ሊዘጋጁ ቀርቶ የሽግግር ጊዜዉ በሚራዘምበት ጉዳይ ላይ እንኳን መግባባት አልቻሉም።

                                          

«ልክ በፊት እንደነበሩት ሁሉ አሁንም ከዴሞክራሲያዊ ሒደት በጣም ሩቅ ናቸዉ።ባሁኑ ወቅት ምናልባትም ባለፉት 12 ወራት ዉስጥ  ሱዳኖችን የሚያነጋግረዉ በጦር ኃይሉና በሲቢል ፓርቲዎች መካከል ምርጫ ለማድረግ ሳይሆን የሽግግር ጊዜዉን ለማረዘም እንኳ ድርድር ወይም ምክክር እንዴት ይደረጋል የሚለዉ ነዉ።»

የጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን ወታደራዊ ሁንታ በየጊዜዉ የሚደረገዉን ያደባባይ ሰልፍ ሲቻለዉ በኃይል፣ ሲሳነዉ ሰበብ በመፍጠር፣ ብዙ ጊዜ ኢንተርኔትን የመሳሰሉ መገናኛ ዘዴዎችን በመዝጋት ለማፈን ብዙ መጣጣሩ አልቀረም።ሕዝቡ በየጊዜዉ ሥራና ሌላ እንቅስቃሴዉን እያቆመ ለሰልፍ መታደሙ ወትሮም የላሸቀዉን የሐገሪቱን ምጣኔ ሐብት ማሽመድመዱ፣የየሰዉን ኑሮ ማጎሉም በግልፅ ይታያል።

ሱዳን ረሐቡም እየከፋ ነዉምስል፦ Sam Mednick/AP Photo/picture alliance

ተቃዉሞ ሰልፈኛዉ ግን ዓላማዉ ግቡን ሳይመታ ወደየቤቱ ለመግባት የፈለገ አይመስልም።ከሰልፉ አስተባባሪዎች አንዷ ራኒያ አብዱል አዚዝ ህዝቡ ድፍን አንድ ዓመት እንደ ሐገር ባንድነት በመቆሙ ትኮራለች።እውን የሱዳን ጦር ከሲቪሉ ጋር ቀጥተኛ ውይይት?

                                        

«እኔ በግሌ በጣም የሚማርከኝ ባለፈዉ አንድ ዓመት እንደሐገር ባንድነት መነሳታችን ነዉ።መሰባሰባችን፣ በጋራ መቆማችንና ፅናታችን የሚያስደንቅ ነዉ።ለማቋረጥ የወሰንኩባቸዉ፣ የተሰላቸሁባቸዉና «በቃኝ» ያልኩባቸዉ ብዙ ጊዜዎች ነበሩ።ይሁንና ወጣ ብለሕ የሚሆነዉን ስታይ ብቻሕን እንዳልሆንክ ትረዳለሕ።ረጅም ሒደት መሆኑን ትገነዘባለሕ እና በትግሉ ለመቀጠል ትቆርጣለሕ።»

ሱዳን በርግጥም ቆርጧል።ለሁለተኛ ዓመት ሊl,ፍ ተዘጋጅቷልም።

 

////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////////

               የጀርመን የአፍሪቃ ሽልማት

የተሕዋሲ አጥኚ (ቫይሮሎጂስት) ናቸዉ።ዶክተር ሲኹሊል ሞዮ።የጥናት ዓላማና ትኩረታቸዉ  የኤድስ አማጩ ተሕዋሲ-HIV፣ ኃላፊነታቸዉም ሐርቫርድ-AIDS የተሰኘዉ የቦትስዋና ላቦራቶሪ የበላይ ናቸዉ።በ2019 ማብቂያ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የኮሮና ተሕዋሲ ዓለምን ሲያተራምስ ግን ባዲሱ ቀሳፊ ተሕዋሲ ላይ አነጣጠሩ።

ከዓመት ከመንፈቅ  ምርምር፣ሙከራ፣ክትትል በኋላ የእስከዚያ ጊዜዉን የዓለም ዕዉቀት፣ግንዛቤ፣አስተሳሰብን የሚለዉጥ አዲስ ተሕዋሲ አገኙ።«የሚለዋወጥበት ቅፅበትና ብዛት» አሉ ሰዉዬዉ በቀደም «አሻኢብ» ነዉ።

የ2022 የጀርመን ሽልማት ለአፍሪቃ ተሸላሚዎች ፕሮፌሰር ኦሊቬራና ዶክተር ሞዮምስል፦ sun / bhp

ዶክተር ሞዮ «ጉድ» ያሰኛቸዉን ዉጤት ደቡብ አፍሪቃ ለሚገኙት ለቀድሞ አስተማሪና አማካሪያቸዉ ለፕሮፌሰር ቱሊዮ ደ ኦሊቬራ አጋሩና ለሁለት አዲሱን መረጃ ከነባሩ ጋር ያነፃፅሩ፣ ያስተነትኑ ያዙ።በመጨረሻም የልዉጡን ተሕዋሲም ባሕሪ መረጃን  ኢንተርኔት ላይ ዘረገፉት።የዓለም ጤና ድርጅት አፍታም ሳይቆይ የሳይቲስቶቹን መረጃ አይኆ እዉቅና ሰጣቸዉ፤ተሕዋሲዉንም ኦሚክሮን ብሎ ሰየመዉ።

«አጃኢብ» ያሰኘዉ ተሕዋሲ በአፍሪቃዉያን ሳይቲስቶች አፍሪቃ ላቦራቶሪዎች ዉስጥ መሰኘቱም ብዙዎችን «አጂኢብ« የሚያሰኝ ነዉ።ግኝቱ ለዓለም አዲስ ጭንቀትን ከአዳዲስ ጥንቃቄ፣ አዲስ ሥጋትን ከአዳዲስ መከላከያ ፍለጋ ጋር ቀይጦ ብዙዉን ያራኩት ያዘ።ዶክተር ሞዮ በቀደም እንዳሉት ግኝታቸዉ ለነሱም ተስፋን ከስጋት፣ እፎይታን ከጭንቀት የቀየጠ ነበር።

                                   

«የማይታወቁ ሰዎች ይደዉሉልሐል።እረፍታችንን አበላሽሕብን ይሉሐል።ወቅቱ ሰዎች ለገና በዓል ከዘመድ ወዳጆቻቸዉ ጋር የሚገናኙበት ጊዜ ስለነበር።ያደረስክብንን ተመልከት።ይሉሐል።መንገድ ላይ ሊተናኮሉሕ የሚፈልጉም አሉ።እናንተ ሳይቲስቶች አፋችሁ ትልቅ ነዉ እያሉ ይሰድቡሐል።አስቸጋሪ ነበር።»

የሚሰደቡ፣የሚዛትባቸዉ ጋዜጠኞች ብቻ ይመስለን ነበር።ለካ ሳይቲስቶችም አይቀርላቸዉም።ብቻ  ተሰድበዉ አልቀሩም።ብዙ ሰዉ በማዳናቸዉ እረኩ።አፍሪቃዊ በመሆናቸዉ ተደሰቱ።ዓለም አቀፍ ዕዉቅና አገኙ።ዘንድሮ ደግሞ ጀርመን ለአፍሪቃ የምትሰጠዉን ታላቅ ሽልማት ተሸለሙ።«የጀርመን ለአፍሪቃ ሽልማት» አሸናፊ ኒኮላስ ኦፕዮ 

                               

«ክብር ነዉ።ባለፉት 2 ዓመታት ላከናወነዉ ሥራ ታላቅ ክብር የሚሰጥ ሽልማት ነዉ።በጣም ተደስቻለሁ።ሽልማቱ ከኛ ጀርባ ለጣሩ ብዙ ሰዎች ጭምር የተሰጠ ነዉ።የሚወክል ነዉ።የአንድ ሰዉ ድል ብቻ አይደለም።እኔ አብሬያቸዉ የሰራኋቸዉ ወጣት ሳይቲስቶች፤ የሳይቲስቶች ማሕበረሰብ ተወካይ ብቻ ነኝ።»

ይላሉ ዶክተር ሲኹሊል ሞዮ። የዚምባቡዌ ተወላጅ ናቸዉ።እዚያዉ ዜምባቡዌ፣ ቦትስዋናና ደቡብ አፍሪቃ ተማሩ።ጋቦሮኒ ሐርቫርድ ኤድስ የተባለዉ ተቋም የላቦራቶሪ ኃላፊ ሆነዉ ይሰራሉ።

በ2016 የዶክትሬት ዲግሪያቸዉን ሲሰሩ ያማካሯቸዉ የሽቴሌንቡሽ፣ ደቡብ አፍሪቃ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ቱሊዮ ደ ኦሊቬራ፣ ለማዮ አስተማሪም፣የሙያ አብነት፣ ጥብቅ አጋርም ብጤ ናቸዉ።ከብራዚላዊ አባትና ከሞዛምቢካዊት እናት ብራዚል የተወለዱት ኦሊቬራ ደቡብ አፍሪቃ የገቡት በ21 ዓመታቸዉ ነዉ።ደቡብ አፍሪቃ አደጉ፣እዚያዉ ተማሩ፣እዚያዉ ያስተምራሉ፣ ይመራመራሉም።

ምስል፦ DW

የባዮኢንፎርማቲክ ፕሮፌሰሩ በኮሮና ተሕዋሲ ላይ ምርምራቸዉን ያጠናከሩት ከሙያ ግዴታ፣ከቀድሞ ተማሪያቸዉ ግፊት በተጨማሪ በዘመነ-ኮሮና አፍሪቃ ስትገለል፣ስትገፋ በመታዘባቸዉ ጭምር ነዉ።

                                      

«በዚሕ ወረርሺኝ ወቅት ያየነዉ ፍፁም የማያስፈልግ፣ ደካማ፣የዘርና የብሔርተኝነት ሥግብግብነትን ነዉ። በመጀመሪያዎቹ ግዚያት የመመርመሪያና የመከላከያ  መሳሪያዎችን፣ አንድ ሐገር ከሚያስፈልገዉ በላይ ማከማቸት፣ ክትባቱ ሲገኝ ደግሞ አንዳድ ሐገራት ከሚያስፈልጋቸዉ ከ20 እጥፍ በላይ ሲያከማቹ፣ ዉጤት የሌላዉ የጉዞ ክልከላ ሲያደርጉም ነበር።ይሕ ለዓለም አቀፍ ችግር ዓለም የሚሰጠዉ ምልሽ ምን ያሕል አሳዛኝ እንደሆነ ያሳያል።»

እንዲሕ ሊያልፍ፣ የበለፀገዉን ዓለም ስግብግብ ባሕሪ በግልፅ ታዘቡ።ከቀድሞ ተማሪያቸዉ ጋር በሙያቸዉ ማድረግ የሚችሉትን አደረጉ።ሁለቱ ሳይቲስቶች ልዉጡን የኦሚክሮን ተሕዋሲ ማግኘታቸዉ ኦሊቬራ እንደሚሉት ብዙዎችን ያስደነቀ፣ለነሱ ምንም የማይገርም፣ ለአፍሪቃ ግን ኩራት ነዉ።

                         

«ይሕ ወረርሺኝ የሚያሳየዉ፣ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝን ለመታገል አፍሪቃ በሳይንሱ መስክ መሪ ልትሆን እንደምትችል ነዉ።ብዙ  ሐገራትን አስደንቋል።ለእኛ ግን ምንም የሚያስገርም አይደለም።ምክንያቱም ላለፉት 20 ዓመታት የምናጠናዉ፣ ለምርምርና ለመሳሪያ ብዙ ገንዘብ ያወጣንበት ጉዳይ ነዉና።»

ታይም የተሰኘዉ የዩናይትድ ስቴትስ መፅሔት ሁለቱን ሳይቲስቶች በ2022 በዓለም ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ ካላቸዉ 100 ሰዎች መካከል አስፍሯቸዋል።

ዶክተር ሞዮምስል፦ DW

የጀርመን የአፍሪቃ ጉዳይ ድርጅት የሚሰጠዉን ሽልማት የፊታችን ሕዳር አጋማሽ ይረከባሉ።ሽልማቱ አፍሪቃ ዉስጥ ለሰብአዊ መብት መከበር፣ ለሕዝብ ነፃነት፣ ደሕንነትና ጤና ለሚታገሉ ሰዎች፤ ድርጅትና ማሕበራት ከ1993 ጀምሮ ይሰጣል።ከዚሕ ቀደም ከተሸለሙት መካከል የቀድሞዉ  የቦትስዋናዉ ፕሬዝደንት ኬቱማሊ ማዚሪ፣ የጋናዉ ጠበቃ መሐመድ ኢብን ቻምባስና የሶማሊያዋ የሴቶች መብት ተሟጋች ዋሪስ ዲሬ ይገኙበታል።

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW