1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቱኒዚያ ዘረኝነት፣ የጀርመን ሴት ተኮር መርሕ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 2 2015

ባለፈዉ የካቲት 14 ያደረጉት ንግግር ከሕዝብ የገጠማቸዉን ተደጋጋሚ ተቃዉሞ «አቅጣጫ ለማሳት» ያለመ ነዉ ።በርግጥም ሰዉዬዉ ጥቁር አፍሪቃዉያን የቱኒዚያን ሕዝብ ማንነት ይቀይራሉ፣ የሐገሪቱን ምጣኔ ሐብትም ያራቁታሉ፣ ወንጀለኝነት አስፋፋትዋል እያሉ የነዙት መርዝ ላጭር ጊዜም ቢሆን የበርካታ ቱኒዚያዊያንን ድጋፍ አግኝቷል።

Tunesien | Migranten kommen am internationalen Flughafen von Tunis-Carthage an
ምስል FETHI BELAID/AFP/Getty Images

የቱኒዚያ መንጠራራት፣የጀርመን ሴት ባለስልጣናት ሴት ተኮር መርሕ

This browser does not support the audio element.

ቱኒዚያ ዘረኝነት የወጠራት ትንሽ ሐገር

የቱኒዚያዉ ፈላጭ ቆራጭ ገዢ ካይስ ሰዒድ ባለፈዉ የካቲት አጋማሽ  በሐገራቸዉ የሚኖሩ ጥቁር አፍሪቃዉያንን የሚያናንቅ ንግግር ካደረጉ ወዲሕ የትንሺቱ ሰሜን አፍሪቃዊት አረባዊት ሐገር ፀጥታ አስከባሪዎች፣ወጣቶችና አክራሪ ዘረኞች በጥቁር የአፍሪቃ ስደተኞች ላይ ዘምተዋል።ወደየሐገራቸዉ የተመለሱና ከየቤታቸዉ ተባረርረዉ የአዉራ መንገድ ላይ የፈሰሱ አፍሪቃዉያን እንደሚሉት ተደብድበዋል፣ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ሐብት ንብረታቸዉ ተዘርፏልም።

የዶቸ ቬለዋ ማርቲና ሽቪኮቭስኪ እንዳለችዉ የጊኒዉ ተወላጅ ኢብራሒም ድያሎ ኮናክሪ በመድረሱ ተደስቷል።ቱኒዚያን ከመልቀቁ በፊት በሕይወት መትረፉን ሲበዛ ተጠራጥሮ ነበር።

«ፕሬዝደንቱ ያን የዘረኛና የጥላቻ ንግግር ካደረጉ ወዲሕ በጥቁር አፍሪቃዉያን ላይ ሁሉም ዘመተምን» አለ ኢብራሒም ለዶቸ ቬለ ባልደረቦች።«እንዲያዉ እንደ አሸባሪ ነዉ የሚያዩሕ።ሐገራቸዉን ለመዉሰድ የመጣሕባቸዉ አድርገዉ ነዉ የሚቆጥሩሕ»

ጊኒ፣ ቱኒዚያ የነበሩ ዜጎችዋን የሚያስወጣ ልዩ አዉሮፕላን የላከች የመጀመሪያቱ ሐገር ናት።የመጀመሪያዎቹ 40 ከስደት ተመላሾች ኮናክሪ ሲገቡ የሐገሪቱ ወታደራዊ መሪ ማማዴይ ዶዩምቦይና የዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉ ኮናክሪ አዉሮፕላን ማረፊያ ተገኝተዉ ተቀብለዋቸዋል።

ዶዩምቦይ የቱኒያዚያ መንግስትና ተባባሪዎቹ በጥቁር አፍሪቃዉያን ላይ ያደረሱትን  ጥቃት «ጨርሶ ተቀባይነት የሌለዉ»ና «ተገቢ ያልሆነ» በማለት አዉግዘዉታል።«ሁላችንም አፍሪቃዉያን ነን፣የቆምነዉ ለአፍሪቃ አንድነት ነዉ።መከፋፈልን ምን አመጣዉ?» ጠየቁ ኮሎኔሉ።

ጊኒን ተከትላ ሌለኛዋ ምዕራብ አፍሪቃዊት ሐገር ማሊም ለጥቃት የተጋለጡ ዜጎችዋን ከቱኒዚያ አስወጥታለች።ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ባማኮ ከደረሱ 145 የማሊ ስደተኞች አንዷ ኮሮቶሚ ድያኪቴ እንደምትለዉ «ሁሉም ነዉ የዘመተባቸዉ»

                                            

ምስል Fethi Belaid/AFP/Getty Images

«ሁሉም ነዉ የዘመተብን።ፖሊሱ፣ሕዝቡ፣ ተማሪዎች ሁሉም ያለምንም ምክንያት ደበደቡን።ስደተኛ ሁን ቋሚ ነዋሪ ምንም ምርጫ የለም።ጥቁር ከሆንክ ያዉ ጥቁር ነሕ።ፖሊስም ብዙ ሰዎች አስሯል።ጥቁር በመሆናችን ብቻ ታሰርን።»የቱኒዚያን ካቢኔ፣ የፀጥታ ተቋም፣ ቢሮክራሲዉን፣ በሕዝብ የተመረጠዉን ምክር ቤት ጭምር በትነዉ የሐገሪቱን መንግስታዊ ስልጣን ጨምድደዉ የያዙት ፕሬዝደንት ካይስ ሰዒድ ያቺን የአረብ ሕዝባዊ አመፅ አብነነትን ሐገር ወደ ፍፁም አምገነናዊ አገዛዝ እየጋለቧት ነዉ።

ፕሬዝደንቱን የሚቃወሙ ፖለቲከኞች፣የሕግ ባለሙያዎች፣ የመብት ተሟጋቾችና ለተቃዉሞ የተሰለፉ በርካታ ሰዎች ታስረዋል።

ባለፈዉ የካቲት 14 ያደረጉት ንግግር ከሕዝብ የገጠማቸዉን ተደጋጋሚ ተቃዉሞ «አቅጣጫ ለማሳት» ያለመ ነዉ ።በርግጥም ሰዉዬዉ ጥቁር አፍሪቃዉያን የቱኒዚያን ሕዝብ ማንነት ይቀይራሉ፣ የሐገሪቱን ምጣኔ ሐብትም ያራቁታሉ፣ ወንጀለኝነት አስፋፋትዋል እያሉ የነዙት መርዝ ላጭር ጊዜም ቢሆን የበርካታ ቱኒዚያዊያንን ድጋፍ አግኝቷል።

ዘረኝነትን የሚቃወመዉ ምኔምቲ የተባለዉ የቱኒዚያ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሳዓዲያ ሞስባሕድ እንደሚሉት የዘረኝነት ስሜት ድሮም ነበር።የፕሬዝደንቱ ንግግር አቀጣጠለዉ።

«አዲስ አይደለም።ድሮም እንዲሕ ዓይነት የዘረኝነት አስተሳሰብ ያላቸዉ ነበሩ።የሪፐብሊኪቱ ፕሬዝደንት ለነዚያ ዘረኞች አረንጓዴ ሲያበሩላቸዉ ግን የረጋዉን ማዕበል ነወጡት።»

የፕሬዝደንቱን ንግግር የአፍሪቃ ሕብረት አዉግዞታል።ድንበር የለሽ ጠበቆች (RSF) የተሰኘዉን ድርጅት ጨምሮ የተለያዩ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች አጥብቀዉ ተቃዉመዉታል።

ይሁንና የፕሬዝደንቱ  መርዛማ ዲስኩር የነሸጠዉ፣ ለዘረፋ የቋመጠዉ፣ ሌሎች ያደረጉትን ማድረግ የሚሻዉ፣ የሚፈራዉ ሁሉም አፍሪቃዉያኑን ያሳድድ ገባ።ቤት አከራያችን ሳይቀር «አባረረን» ትላለች የአይቮሪኮስትዋ ስደተኛ

                              

ምስል Hasan Mrad/Zuma/picture alliance

«አከራያችን፣ የቱኒዚያ መንግስት ጥቁር አፍሪቃዉያን ከቱኒዚያዊ ጋር እንዳይኖሩ ከልክሏል በማለት ቤቱን ለቅቀን እንድወጣ ነገረን።ፖሊስ ይይዘኛል ብሎ ስለፈራ አባረረን።»

የዚያኑ ያክል በርካታ ቱኒዚያዉያን የፕሬዝደንቱን ንግግር ተቃዉመዋል።ጥቁር ስደተኞችን የሚረዱም ብዙዎች ናቸዉ።ቱኒዚያ ዉስጥ ከ21 ሺሕ የሚበልጡ ጥቁር አፍሪቃዉን ስደተኞች በይፋ ተመዝግበዉ ይኖራሉ።የመብት ተሟጋቾች ግን የስደተኛና ወደ አዉሮጳ ለመሰደድ ቱኒዚያ የገባዉ ጥቁር አፍሪቃዊ ቁጥር በይፋ ከተመዘገበዉ በእጥፍ ይበልጣል ባዮች ናቸዉ።

አብዛኛዉ ስደተኛ የአይቮሪኮስት፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣የጊኒና የማሊ ዜጋ ነዉ።

 

የጀርመን የእንስታዊነት የዉጪ መርሕና አፍሪቃ

የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ወይዘሮ አናሌና ቤርቦክ በቅርቡ ያዘጋጁትን የዉጪ መርሕ ሰነድ «ሴቶች አስተማማኝ ኑሮ እስካልኖሩ ድረስ ማንም አስተማማኝ ኑሮ አይኖርም» በሚል ጥቅስ ጀመሩት።

«ሩሲያ ዩክሬንን ከመዉረሯ በፊት አንዲት ዩክሬናዊት እናት ሲሉት ነዉ የሰማሁት» ይላሉ ጥቅሱን።ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በየደረሱበት ይጠቅሱታል።በቅርቡ ናጄሪያን በጎበኙበት ወቅት ቦኮሐራም ከቤት ንብረታቸዉ ያፈናቀላቸዉን ሴቶች ሲያነጋግሩም ብለዉታል።

የአረንጓዴዉ ፓርቲ ትልቅ ዲፕሎማት በየደረሱበት ሐገር ሴቶችን ሳያነግሩ አይመለሱም።ባለፈዉ መፀዉ ኡዝቤክስታንን ሲጎበኙ እንደለመዱት መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ሴቶችን ማነጋገር እንደሚፈልጉ ለኡዝቤኩ አቻቸዉ ይናገሩ።

ጥያቄዉ በይፋ የጉብኝት ዝርዝር ዉስጥ ያልተካተተ በመሆኑ ለዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቭላድሚር ኖሮቭ  አስገራሚና ያልተጠበቀ ቢሆንባቸዉም ጀርመናዊቱ እንግዳቸዉን በቅርብ ከሚገኘዉ የሴቶች ቤት ይዘዋቸዉ ሔዱ።

ምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

እዚያ ሲደርሱ ግን ጀርመናዊቱ እንግዳ ሌላ ጥያቄ አቀረቡ።«ብቻዬን ነዉ»ማነጋገር የምፈልገዉ» አሏቸዉ።ሌላ ግርምት፣ ሌላ መደመም ግን የኡዝቤኩ ዲፕሎማት «ለምን» ብለዉ ጠየቁ።

«እ---ብዙ ጊዜ ሴቶች ወንድ ባለስልጣን ባለበት የልባቸዉን ማዉራት ስለማይሹ ነዉ።» መለሱ ቤርቦክ ከፈገግታ ጋር።ሰዉዬዉ ዉጪ ከመጠበቅ ሌላ ምርጫ አልነበራቸዉም።

ቤርቤክ ከኡዝቤክስታን ሴቶች ጋር ሲያወሩ ያቺን የሚወዷትን ጥቅስ ማዉሳታቸዉን ኋላ ላስተናጋጃቸዉ  ነገሯቸዉ።አሁን ደግሞ የዉጪ መርሐቸዉ መክፈቻ አደረጉት።

«የእንስታዊነት (ፌሚንስት) የዉጪ መርሕ በመላዉ ዓለም የሚገኙ ሴቶች ኑሮና ሁኔታ እንዲሻሻል የሚረዳ ነዉ።» ይላሉ ቤርቦኮ።ሴቶች ብቻ ዓይደሉም በ21ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ሁሉ ሰዉ የፆታ፣የእምነት፣የቀለም፣የትዉልድ ወዘተ አድልዎ እንዳይደረግበት እኩል መብት፣ነፃነትና ዕድል ሊኖረዉ ይገባል» አከሉ ሴትዮዋ የመርሐቸዉ ዓላማና ግብ ሲያስረዱ።

ባልደረባቸዉ የጀርመን የጋራ ልማት ተራድኦ ሚንስትር ወይዘሮ ስፌንያ ሹልሰም ተመሳሳይ ሴቶች ተኮር መመሪያ አዘጋጅተዋል።«ረሐብን፣ድሕነትን፣የኑሮ ተባለጥን ለመዋጋት በምናደርገዉ ትግል ለማሕበረሰቡ ግማሽ አካል (ለሴቶች) ትኩረት መስጠት አለብን» ባይ ናቸዉ ሹልሰ።

ሁለቱም ስልት በጀርመንኛዉ «3 R» በሚባሉት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ነዉ።Gleiche Rechte, Ressourcen und Repräsentanz. ለሴቶች እኩል መብት፣ሐብት፣እና ዉክልና-እንደማለት።

በዕቅዱ መሰረት እስከ 2025 (እግአ)ድረስ የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር በሌሎች ሐገራት ከሚደግፋቸዉ ፕሮጄክቶች የ85 ከመቶዉ ወጪ፣ የልማት ተራድኦ ትብብር ከሚያደርጋቸዉ ድጋፎች 90 በመቶዉ ዉጪ የሚሸፈነዉ ለሴቶችና እንደ LGBTQ+ ለመሳሰሉ ወገኖች ትኩረት የሚሰጥ ነዉ።

የጀርመን የዲፕሎማሲና የልማት ተራድኦ በነዚሕ ሶስት ጉዳዮች ላይ ማነጣጠሩ ISS በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የስልታዊ ጥናት ተቋም ባልደረባ ኦቲሊያ አና ማዉንጋኒደዜ እንደሚሉት ለአፍሪቃ ጠቃሚ ነዉ።

«በአፍሪቃ ተጨባጭ ሁኔታ በሴቶች ላይ ያተኮረ መርሕ በጣም ጠቃሚ ነዉ።እንደማንኛዉ ዓለም አፍሪቃ ዉስጥ ከፍተኛዉን ቁጥር የሚይዙት ሴቶችና ልጃገረዶች ናቸዉ።በወግ አጥባቂዉ ሥርዓት ይሁን ወይም በሌሎች ምክንያቶች ለጉዳት የተጋለጡ ናቸዉ።የነሱን ፍላጎት የሚያሟላ መርሕና ስልት ያስፈልጋል።»

እንደ ደቡብ አፍሪቃና ኬንያን የመሳሰሉ የአፍሪቃ ሐገራትም የሴቶችን እኩልነትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሕጎችን በቅርቡ አፅድቋል።ኬፕቬርዴ ዉስጥ ደግሞ  38 ከመቶ የሚሆኑት የምክር ቤት እንደራሴዎች ሴቶች ናቸዉ።የአፍሪቃ ሕብረትም  በቅርቡ የሴቶችን እኩልነትና ዉክልና የሚያጠናክር ደንብ አፅድቋል።

ምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

ይሁንና በርሊን የሚገኘዉ የአፍሪቃ ጉዳይ ጥናት ተቋም ባልደረባ ግሬስ ምቡንጉ እንደሚሉት አዲሱን መርሕ አፍሪቃ ዉስጥ ሥራ ላይ ለማዋል ጥንቃቄ መደረግ አለበት።

 «ያለፈዉ የቅኝ አገዛዝ ዘመንን እዉነታ፣የዘር ልዩነትና የጀርመንንና የሌሎችንም ሐገራት ተፅዕኖ የማሳደር ሁኔታን ከግምት ስናስገባ ይሕ መርሕ ዓላማዉ ጥሩ ቢሆንም ካንዳድ ወገኖች ብዙ ፈተና ምናልባትም ተቃዉሞ ሊገጥመዉ ይችላል።»

ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አናሌና ቤርቦክም መስሪያ ቤታቸዉ ብዙ ጥረት እንደሚጠብቀዉ ያወቁት መስለዋል።መርሕ ቤርቦክ በቅርቡ እንዳሉት ገቢር እንዲሆን የሚታገሉለት እንጂ እንደ በራሪ ወረቀት ተፅፎ የሚበተን አይደም።

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW