1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ትኩረት በአፍሪቃ፤ የናይጄሪያ የምርጫ ዝግጅት፤ የሩዋንዳና የኮንጎ ስምምነት

ቅዳሜ፣ ሰኔ 28 2017

ይህ በታጣቂዎች ላይ ቅሬታን ፈጥሯል ያሉት የፖለቲካ ተንታኙ ይህም የስምምነቱን ተፈጻሚነት አደጋ ላይ እንደሚጥለው ተናግሯል። የኮንጎ መንግሥት በበኩሉ እነዚህ የ ኤም አይ 23 ሚሊሺያዎች ድርጊት በማውገዝ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አጥብቆ አሳስቧል።

የሩዋንዳና የኮንጎ የሰላም ስምምነት
የሩዋንዳና የኮንጎ የሰላም ስምምነት በሲቪሎች ላይ የተፈፀሙ አረመኔያዊ ጥቃትን ዘንግቷልምስል፦ Joe Raedle/Getty Images

ትኩረት በአፍሪቃ፤ የናይጄሪያ የምርጫ ዝግጅት፤ የሩዋንዳና የኮንጎ ስምምነት

This browser does not support the audio element.

ናይጄሪያ ፦ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግንባር ፈጥረው ቲኑቡን በ2027 ለመገዳደር ይሞክራሉ
በተቃዋሚዎች ግምት አዲሱ የመላው ዲሞክራቲክ አሊያንስ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ (ADA)  እ.ጎ.አ በ2027 በናይጀሪያ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የፕሬዚዳንት ቦላ ቲኑቡን መንግሥትን ለማሸነፍ ጥምረቱ ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት ይለወጣል። 
የጥምረቱ ደጋፊዎች በቲኑቡ አስተዳደር ስር ያለው የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን በመግለፅ አንድነታቸውን ጠብቀው ገዢውን ፓርቲ ለመገዳደር አቅደዋል።  
በጥምረቱ ውስጥ ቁልፍ ከሆኑት ሰዎች መካከል የናይጄሪያ የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት አቲኩ አቡበከር ፣ የቀድሞው የካዱና ግዛት አገረ ገዥ ናስር ኤል ሩፋይ ፣ የቀድሞው የትራንስፖርት ሚኒስትር ሮቲሚ አማኤቺ እና የሰራተኛው ፓርቲ ፒተር ኦቢ «የናይጄሪያውያንን መከራና ስቃይ  የሚያስቀር» ያሉት  የፓርቲዎቹ ጥምረት ላይ ብቻ ትኩረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል ። የአዲሱ ግንባር አስተባባሪ ዩኑሳ ታንኮ ለዶይቸቨለ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተከታዩን ብለዋል።
«ለሀገሪቱ ህልውና  እየታገልን  ነው ፣ የጥምረቱ አጠቃላይ መንፈስ ይህ ነው። በናይጀሪያ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ይስተዋላሉ። ከነዚህም አንዱ የጸጥታ ችግር ነው።ሌላው የዴሞክራሲ ጉዳይ ነው። እኛ የምንታገለው በሐገሪቱ ዴሞክራሲን ለማስፈን ነው፤ ዴሞክራሲ ከገባበት አዘቅት መከላከል ነው።»
  
«የናይጄሪያ ሥርዓት በመጥፎ ሁኔታ ላይ ነው፤ በሐገሪቱ ላይ ረሃብ ፣ በራስ ያለመተማመን ስሜት እየጨመረና ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች ግልጽ የሆነ ንቀት አለ» ያሉት ታንኮ «ብዙ እውነተኛ ዴሞክራቶች ሥርዓቱ እንደገና መታደስ እንዳለበት ያምናሉ በማለት ያክላሉ። ይህ ጥምር ኃይል የተመሰረተው  ለናይጄሪያ ህልውና ለመታገልና የዲሞክራሲን መሠረት ለማስከበር በጋራ ጥረት ለማድረግ ነው።  በስልጣን ላይ ያለው መንግስት  የተትረፈረፈ የምግብ ምርት ባለባት ሐገር ሕዝቡን በረሃብ እንዳያጠፋው ማድረግ  ሌላኛው ዓላማችን ነው»ብለዋል ።
ናይጄሪያ በምርጫ ማጭበርበር፣ በፖለቲካ አመፅና በሙስና ወንጀል ብትከሰስም  ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ  ሰላማዊ ምርጫዎችን አካሂዳለች።

ናይጄሪያ በምርጫ ማጭበርበር፣ በፖለቲካ አመፅና በሙስና ወንጀል ብትከሰስም  ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ  ሰላማዊ ምርጫዎችን አካሂዳለች።ምስል፦ Pius Utomi Ekpei/AFP

የፕሬዝዳንት ቲኑቡ አጋሮች የሰጡት ምላሽ
የኅብረቱ ደጋፊዎች በ2027 ምርጫ ድል ለመቀዳጀት  ብሩህ ተስፋ ቢኖራቸውም ሁሉም ሰው ግን ይህ ተስፋ ዕውን ይሆናል ብሎ እርግጠኛ አይደለም። የፕረዚደንት ቲኑቡ ደጋፊና የቀድሞ የምክርቤት አባል ቢንታ ጋርባ ማሲ ቅንጅቱ የዴሞክራሲ መልካም ገፅታ ቢሆንምፕሬዚዳንቱን ከምርጫ በፊት ከስልጣን የማንሳት ጉዳይ ግን ከዚህ የተለየ ጉዳይ ነው ሲሉ ለዶይቸቨለ ተናግረዋል።
«በዴሞክራሲ ማዕቀፍ ተቀናጅቶ መታገል ይህ ለእኔ ጤናማ ነው። ይሁንና  ያልተሰናበተውን ፕሬዚዳንት ከስልጣን ለማውረድ የመሞከሩ ሂደት ሌላው ጉዳይ ነው። ፕሬዝዳንት ቲኑቡን ለመጣል ለሚፈልግ ሰው ሁሉ ትልቅ ኮረብታን እንደመግፋት ነው። ጥምረቱ ከምርጫ በፊት ፕረዚደንቱን ለማውረድ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ዴሞክራሲን የሚያቀጭጭ ነው። ይህ በሐገሪቱ አሳዛኝ ክስተት ሊፈጥር ይችላል።»

«አሁን ግን... ሙሉ በሙሉ የተለየ ኳስ ጨዋታ ይመስለኛል ።» የፖለቲካ ተንታኙ ማላም ባባ ዩሱፍ
ቅንጅት በናይጄሪያ ፖለቲካ አዲስ አይደለም ። ተቃዋሚዎች ከዚህ በፊት ይህን ሞክረዋል ። በ2015 በእንግሊዝኛ ምህጻሩ ኤፒሲ የተባለው ጥምረት በወቅቱ የነበሩትን ፕረዚደንት  ጉድላክ ጆናታንን ድል ለማድረግ የተፈጠረ ግንባር ተፈጥሮ ነበር።  ያ ቅንጅት በወቅቱ የተቃዋሚ  ዕጩ የነበሩት ማማዱ ቡሐሪ እንዲመረጡ ምክንያት ሆኗል። የፖለቲካ ተንታኙ ማላም ባባ ዩሱፍ ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ያሉት ተለዋዋጭ ሁኔታዎች በጣም የተለዩ እንደሆኑ ይገልጻሉ ።
«እኔ እንደማስበው የተቃዋሚ ጥምር ኃይል ምንም ዓይነት ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ ለማለት ጊዜው ገና ይመስለኛል። በናይጄሪያ ያለውን ወቅታዊ የፖለቲካ ድባብ ብንመረምር፤ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ፕረዚደንት ቲኑቡ ምርጫ በሚወዳደሩበት ጊዜ በናይጄሪያ የነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ አሁን ካለው የፖለቲካ ድባብ ፈፅሞ የተለየ ነበር። አሁን ያሉት ተቃዋሚ መሪዎች በከፍተኛ ደረጃ ስልታቸውን ካልቀየሩ በስተቀር ብዙም ሲቀራረቡ አልመለከትም።»

«በዴሞክራሲ ማዕቀፍ ተቀናጅቶ መታገል ይህ ለእኔ ጤናማ ነው። ይሁንና  ያልተሰናበተውን ፕሬዚዳንት ከስልጣን ለማውረድ የመሞከሩ ሂደት ሌላው ጉዳይ ነው።» የፖለቲካ ተንታኝምስል፦ Sunday Alamba/AP Photo/picture alliance

የኢኮኖሚ ፈታኝ ሁኔታዎች እየሰፉ መሄዳቸውን
የፕሬዝዳንት ቲኑቡ መንግሥት ከግንቦት 2023 ዓ.ም ጀምሮ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የሕዝብን ገንዘብ መልሶ ለማቋቋም እንዲቻል የነዳጅ ድጎማዎችን በማቆምና የናይጄሪያ ገንዘብ «ናይራ»ን ከውጭ ምንዛሪ ጋር ያለውን ትይዩ የምንዛሪ ዋጋን በማዳከም በኩል ድፍረት የተሞላበት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ አድርጓል ተብሎ ይመሰገናል። በቅርቡ የዓለም ባንክ እንደገለጸው የናይጄሪያ ኢኮኖሚ ባለፉት አሥር ዓመታት ከፍተኛ እድገት አስመዝግቧል ብሏል።
ይሁን እንጂ ናይጄሪያውያን የጥድፊያ ለውጡ ኑሮአቸውን እንደቆነጠጣቸው ይሰማቸዋል። የኑሮ ውድነቱ በእጅጉ ጨምሯል ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የምግብ፣ መኖሪያና መጓጓዣን ጨምሮ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት እየታገሉ ነው ።
ብዙዎች የዋጋ ግሽበትን ፣ ሥራ አጥነትን እንዲሁም የደህንነት ስጋት ባለበት ሁኔታ ጥምረቱ አዲስ የፖለቲካ ምህዳር እንደሚያመጣ ቃል ቢገባም ሐሳቡ በመራጮች ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት  ዕድሉ አጠራጣሪ ነው ።
ይሁን እንጂ ቢንታ ጋርባ ማሲ አሁን «በስልጣን ላይ ያለው ኤፒሲ የተባለው ፓርቲ ፤አሁንም ጠንካራና እየጠነከረ እንደሚሄድ እርግጠኛ ነኝ ።» ይላሉ። ማሲ እ.ግ.አ. በ2027 በናይጄሪያ በሚካሄድ ምርጫ በፈጣሪ እርዳታ እንደሚያሸንፍ» ተስፋ አድርገዋል።

የሩዋንዳና የኮንጎ የሰላም ስምምነት በሲቪሎች ላይ የተፈፀሙ አረመኔያዊ ጥቃትን ዘንግቷል
በቅርቡ በዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ  እና በሩዋንዳ መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት በምሥራቅ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ  ለዓመታት የዘለቀ የጋራ ግጭት እና የእርስ በእርስ መወነጃጀል ካስከተለ በኋላ በሁለቱ መንግሥታት  ታሪካዊ ምዕራፍ ተብሎለታል።
በአሜሪካ እና ቀጠር አሸማጋይነት በዋሽንግተን ዲሲ  የተፈረመው የሰላም ስምምነት  ጦርነቱን ለማቆም፣  የሩዋንዳ ነፃ አውጭ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች (FDLR) ን ጨምሮ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖችን ትጥቅ ለማስፈታት፣  የኢኮኖሚ ትብብርን ለመመስረት እንደሚያስችል ይደነግጋል።የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ  ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ሴሺሴኬዲ ስምምነቱን «አዲስ የመረጋጋት፣የትብብርና ብልፅግና ዘመን» ሲሉ ገልጸውታል።  የአሜሪካ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ስምምነቱ «በአካባቢዉ የማዕድን ሀብት እንደገና ለማንቀሳቀስ ጥሩ እርምጃ ነው» ብለውታል ።
ዳሩ ግን የፖለቲካ ተንታኞችና በድንበሩ ግራና ቀኝ ያሉ ታዛቢዎች የስምምነቱ አፈፃፀም፣ ለአካታችነት እና ለተጠያቂነት አሠራር ትልቅ መሰናክል እንደሆነ ያስጠነቅቃሉ ።
በተጨማሪም መሬት ላይ ያለው እውነታ እና እንደ M23 ያሉ ታጣቂ ቡድኖች የሚሰጡት ምላሽ፤ ፍጹም የሚመስለውን ምስል ውስብስብ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የሩዋንዳና የኮንጎ የሰላም ስምምነት በሲቪሎች ላይ የተፈፀሙ አረመኔያዊ ጥቃትን ዘንግቷልምስል፦ Mandel Ngan/AFP/Getty Images

አፈጻጸምና ተደራሽነት
የኪጋሊ-ፖለቲካ ተንታኝ ጎንዛ ሙጊ ለዶይቸቨለ ሲናገሩ ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረግ ፈታኝ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
«ዋናው ነጥብ እንዲህ ያለውን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጽንሰ ሐሳብ በ90 ቀናት ውስጥ በሥራ ላይ ማዋል ይቻል እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን ነው፤ ይህም በውሉ ላይ በተገባው ቃልና ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ላይ የተመሰረተ  ነው ።"
ቀደም ሲል የነበረውየሰላም ጥረትሊሳካ ያልቻለው ሁሉን አቀፍ የሆነ ውይይት ባለመደረጉና አንዳንድ የፖለቲካና የሲቪል ማህበረሰብ ተዋንያን በመገለላቸው እንደሆነ የገለጹት የፖለቲካ ተንታኙ በምስራቃዊ የሐገሪቱ ክፍል የተከሰተውን ግጭት ኪንሻሳ ውስጥ አዲስ የፖለቲካ ሥርአት እንዲመጣ ለመደራደር እንደ መልካም አጋጣሚ የተመለከቱት ሃይሎች እንዳሉ አልሸሸጉም።
« በቀጣናው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ከተፈለገ የዶሃው የሰላም ሂደት በጣም አካታች እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ከዚህ በፊት እንደነበረው የፖለቲካ ተዋናዮቹ መገለል የለባቸውም።»

የአገር ውስጥ ወይስ ዓለም አቀፍ ፍትሕ?
ኮንጋዊው የሕግ ባለሙያና የፖለቲካ ተንታኝ ዣን ባፕቲስት ጋሶሚናሪ ተጠያቂነት እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ። ፍትሕ በዋነኝነት የሚገኘው በኮንጎ  ሉዓላዊ ግዛት  ውስጥ እንደሆነም ተናግረዋል ።
«ፍትሕ የመንግሥት ሉዓላዊነት ጉዳይ ነው፤  የኮንጎ ዴሞክራቲክ መንግሥት የፍርድ ሂደቱን  በብሔራዊ ፍርድ ቤቶች በኩል ወይም ሐገሪቱ አባል በሆነችበት የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ጣልቃ እንዲገባ በመሻት ፍትህ ሊረጋገጥ ይገባል።»

የኤም 23 ታጣቂዎች አደናቃፊዎች ወይም ባለድርሻዎች ናቸውን?
ጎማንና ቡካቩን ጨምሮ የኮንጎን ስትራቴጂካዊ ከተሞችን የያዘውየM23 አማፂያን ቡድን የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎንና የሩዋንዳን ስምምነት ውድቅ አድርጓል ። አማጺያኑ በመንግስት በኩልም ጥቃት እየተፈጸመባቸው ይገኛል። ይህ በታጣቂዎች ላይ ቅሬታን ፈጥሯል ያሉት የፖለቲካ ተንታኙ ይህም የስምምነቱን ተፈጻሚነት አደጋ ላይ እንደሚጥለው ተናግሯል። የኮንጎ መንግሥትበበኩሉ እነዚህ የ ኤም አይ ሚሊሺያዎች ድርጊት በማውገዝ  ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አጥብቆ አሳስቧል።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ነጋሽ መሐመድ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW