1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የጥር 2 ቀን 2018 ዓ.ም፤ ትኩረት በአፍሪካ

ቅዳሜ፣ ጥር 2 2018

ቻይና ለአፍሪካ ሐገራት ያለፖሊሲ ጫናና በቀላል የቢሮክራሲ ውጣውረድ በገፍ የምታቀርበውን ብድር የሐገራቱን መጻኢ ዕድል በቻይና ስር እንዲወድቅ ያደርጋል የሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡ የፖለቲካ ተንታኞችም ይደመጣሉ።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪምስል፦ TINGSHU WANG/AFP

የጥር 2 ቀን 2018 ዓ.ም፤ ትኩረት በአፍሪካ

This browser does not support the audio element.

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉብኝት አንደምታው


የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ እስከ ፊታችን ሰኞ የሚቆይ በ 4 የአፍሪካ ሐገራት  ጉብኝት እያደረጉ ነው። 
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ጋር በሁለቱም ሐገራት የጋራ ግንኙነትና ይህን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ የትስስር ገጻቸው እንደጻፉት ኢትዮጵያና ቻይና የቆየ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸውና ይህ ግንኙነት በቅርቡ በሁኔታዎች ወደማይለዋወጥ የስትራተጂክ ግኑኝነት ማደጉን ገልጸዋል። በንግድ፣ አረንጓዴ የሐይል አቅርቦት፣መሰረተ ልማት ግንባታና የዲጂታል ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ መክረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ፣ሶማሊያ፣ ታንዛንያና ሌሴቶ የሚያደርጉት ጉብኝት መደበኛ የቻይና አፍሪካ ዓመታዊ መደበኛ ጉብኝት ነው ቢባልም እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን ዕውቅና እና የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሶማሊ ላንድ ያደረጉትን ጉብኝትን ተከትሎ መካሄዱ ግን አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል።
በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1991 በሶማሊያ የተፈጠረውን ትርምስና ውድቀት ተከትሎ ሶማሊላንድ ራሷን እንደ ነጻ ሐገር ትቆጥራለች። የራሷን ገንዘብ አሳትማ፤ በየጊዜው ምርጫዎችን በማካሄድም በአንጻራዊነት የተረጋጋ መንግስትን በመመስረት እንደ ሐገር እወቁኝ የሚለው ውትወታዋን አጠናክራ እንደቀጠለች መረጃዎች ያመላክታሉ። ይሁንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል የሆኑ ሐገራት እስከአሁን ይፋዊ ዕውቅና ከመስጠት ቢቆጠቡም ከሶማሊላንድ ጋር የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሳዊ ግኑኝነቶች የሚያካሂዱ አገሮች እንዳሉ ይታወቃል። 
የኢትዮጵያ መንግስት ምንም እንኳን በቱርክአደራዳሪነት ጉዳዩን ረገብ ቢያደርግም ለሶማሊላንድ ዕውቅና የመስጠቱ ሃሳብ ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቶ እንደነበር ይታወሳል። በቅርቡ እስራኤል ሶማሊላንድን እንደ ሉአላዊ ሐገር እንደምታያት መግለጿን ተከትሎ ደግሞ ከተለያዩ ሐገራት፣ አሕጉራዊና  ዓለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ ተቃውሞና ውግዘትን አስከትሏል። የእስራኤል ለሶማላሊላንድ ዕውቅና መስጠትን ከተቃወሙት አንዷ ቻይና ናት። የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ድርጊቱን የተባበሩት መንግስታት መተዳደሪያ ደንብን የሚጥስና የሶማሊያን ግዛታዊ አንድነትን የሚንድ ነው ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል።

ለቻይና ተጨማሪ ሥጋት


ባልደረባችን ነጋሽ መሐመድ የእስራኤል ለሶማሊ ላንድ ዕውቅና መስጠት የአፍሪካ ቀንድንድ ያለውን የጂኦ ፖለቲካዊ ሥርዓትን የሚያናጋ ለቻይና ደግሞ በብዙ ምክንያቶች የሚያሰጋ ጭምር ነው ይላል።
« እስራኤል ለሶማሊላንድ የሉአላዊ ሐገርነት ዕውቅና መስጠቷ እዛ አካባቢ የነበረውን የጂኦ ፖለቲካዊ ሥርአት የሚያናጋ ነው። ለቻይና ደግሞ በብዙ ምክንያቶች የሚያሰጋ ጭምር ነው።»

የእስራኤል መንግስት ለሶማሊላንድ ዕውቅና መስጠቱን ተከትሎ ጠንከር ያለ መግለጫ ከሰጡት መካከል የየመን ሁቲ አማጽያን ይገኙባቸዋል። እነሱ እንዳሉት እስራኤል እንዳለችው ለሶማሌ ላንድ ዕውቅና ሰጥታ እንደሐገር ግንኙነት ማድረግ ከጀመረች በአካባቢው ባሉ የእስራኤል ወታደራዊና ኢኪኖሚያዊ ጥቅሞቿን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች እንደሚፈጽሙ ዝተዋል። 

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪምስል፦ picture-alliance/dpa/G. Jinfh

ለሶማሊላንድ ይዞላት ወይስ የዞባት የሚመጣው ሁኔታ


የእስራኤል እርምጃ የተለያዩ ተቃውሞና ውግዘትን ቢያስከትልም ለዓመታት የነጻነት ጥያቄ ሲያራምዱ የነበሩ የሶማሊ ላንድ ነዋሪዎችን ግን አስፈንድቋል። ይህ የእስራኤል ዕውቅና ለሶማሊላንድ ይዞላት ወይስ የዞባት የሚመጣው ሁኔታ ምንድነው? አልነው ባልደረባችን ነጋሽ መሐመድን
« ይዞባት ይመጣል የሚለው ነው ቢያንስ ቢያንስ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መነሳት ያለበት። ምክንያቱም የመን የተረጋጋ መንግስት የላትም። ሶማሊያ በጣም ደካማ መንግስት ነው ያለው። እዛው ሶማሊያ ውስጥ አልሸባብ አለ።» 
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በ4 የአፍሪካ ሐገራት የሚያደርጉት ጉብኝት ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ዴፕሎማሲያዊ ግንኙነት 70ኛ አመት መታሰቢያ እንደሆነም ተገልጿል። ይህ ግንኙነት በኢኮኖሚ፣ በባሕል፣ በቴክኖሎጂና በፖለቲካው ዘርፎች አጠናክራ ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላት ቻይና ትገልጻለች። በአንጻሩ ደግሞ ቻይና ለአፍሪካ ሐገራት ያለፖሊሲ ጫናና በቀላል የቢሮክራሲ ውጣውረድ በገፍ የምታቀርበውን ብድር የሐገራቱን መጻኢ ዕድል በቻይና ስር እንዲወድቅ ያደርጋል የሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡ የፖለቲካ ተንታኞችም ይደመጣሉ። 

የኡጋንዳው ፕረዚደንት ዩዌሪ ሙሶቬኒምስል፦ Uganda PPU

 

የኡጋንዳ ምርጫና የተደቀነባት የዕዳ ጫና


ኡጋንዳ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የዘመን ቀመር የፊታችን ጥር 15 ቀን 2026 ዓ.ም ምርጫ ልታካሂድ ነው። የሐገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን በሚካሄደው ፕሬዚደንታዊና ፓርላሜንታዊ ምርጫ 27 የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚሳተፉ ይፋ አድርጓል። ለፕሬዚደንትነት አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ዩዌሪ ሙሴቬኒን ጨምሮ 8 ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የኡጋንዳ ምክር ቤት 556 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን በአፍሪካ ከፍተኛ የምክርቤት መቀመጫ ካላቸው አገራት ተርታ እንደሚመደብ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ለምርጫው 21.6 ሚልዮን መራጮች ተመዝግበዋል።  የመራጮቹ ቁጥር በሐገሪቱ እ.አ.አ. በ2006 እና በ2021 ከተመዘገበው የሰው ብዛት  አንጻር ሲታይ በብዙ እንደቀነሰ መረጃዎች ያመላክታሉ። በኡጋንዳ የምርጫ ሕግ መሰረት ለፕሬዚደንትነት የሚወዳደር ዕጩ ከመራጩ ድምጽ 50+1 አብላጫ ድምጽ ማግኘት አለበት። ይህ ካልተሟላ ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ የምርጫ ሕጉ ያዛል። 

የዑጋንዳ የዕዳ ክምችት


በአሁኑ ወቅት የኡጋንዳ የዕዳ ክምችት 32.3 ቢልዮን ዶላር መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ «ከፍተኛ » የተባለለት መንግስት የተበደረው የዕዳ ክምችት እያንዳንዱ ኡጋንዳዊ እንዴትና መቼ የጉዳቱ ወላፈን እንደሚለበልበው ባያውቀውም ስቲቨን አሎር የተባሉ የምጣኔ ሐብት ተንታኝ ለዶይቸቨለ የእንግሊዝኛ ቋንቋ አገልግሎት በሰጡት ቃለ ምልልስ  ዕዳውን «አሳሳቢ» ሲሉ ነው የገለጹት። መንግስት እያጋጠመው ያለው የበጀት ጉድለት ሕዝቡን ከባድ ዋጋ እያስከፈለው መሆኑን በማከል።

« መንግስት ሁሌ ያለበትን ዕዳ ከአጠቃላይ የሐገሪቱ ዓመታዊ ምርት አንጻር የተረጋጋ ነው እንደሚል አውቃለሁ። ከአጠቃላይ የሐገሪቱ ዓመታዊ ምርት አንጻር የሐገሪቱ ብድር 51 በመቶ ነው። ይሁንና በኡጋንዳ እየሆነ ካለው አንጻር ስንመለከተው ይህ የተረጋጋ ኢኮኖሚን አያመጣም። የሕዝብ አስተዳደሩን ተመልከቱ! ወጪዎች እንዴት እያስተዳደርን እንደሆነ ተመልከቱ!»
የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ስቲቨን አሎር አክለውም የበጀት ጉድለቱ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታዎች የመቋረጥ፤ ትኩረት የተነፈጋቸው የጤና ተቋማትን ጨምሮ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ሊጓተቱ አልያም ሊቋረጡ እንደሚችሉ ያስጠነቅቃሉ።

«ሁሉንም ዘርፎችን በጣም እየጎዳ ነው። አዳዲስ መንገዶች እየተሰሩ አደለም፤ የተጀመሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተጠናቀቁ አደለም፤ ይህ በጤና ላይ የሚያስከትለው መዘዝ፤ በትምህርና በአጠቃላይ የሕዝቡ ኑሮ ላይ የሚያስከትለው መዘዝ ከፍተኛ ነው።»

 

ዕዳውን ለመቀነስ የተደረጉ ጥረቶች


የኡጋንዳ መንግስት ከሐገር ውስጥ የሚበደረውን የገንዘብ መጠን ለመቀነስ አቅዶ እየሰራ እንደሆነ ይገልጻል። ባለፈው ታሕሳስ ወር ይፋ ያደረገው ዕቅድ እንደሚያመላክተው መንግስት ከሐገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጮች የሚወስደውን ብድር በ21.1 % ይቀንሳል። ይህን ያደረገበት ምክንያትም የዕዳ ክምችቱ ከአገሪቱ አመታዊ አጠቃላይ ገቢ ተመጣጥኖ እንዲሄድና የብድር ክምችቱ በኢኮኖሚው ላይ ያሳደረውን ጫና ለመቀነስ እንደሆነ አመላክቷል።
የቀድሞው የካምፓላ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሐብት መምህርና አሁን በጡረታ ላይ የሚገኙት ራማን ሙድዴ « መበደር በራሱ መጥፎ አይደለም፤ ይሁንና የተበደርከው ገንዘብ የምታውልበትና የምታስተዳድርበት ሁኔታ ነው የሚወስነው» ይላሉ።

«የገንዘቡን አጠቃቀም ካወቅበት መበደር በራሱ መጥፎ አይደለም። ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየነው ያለነው ግን ገንዘቡ በጥሩ ቦታ ላይ እየዋለ እንዳልሆነ ነው። ይሁንና ብድር በአንድ በሆነ ወቅት መቆም ያለበት ነው። ምክንያቱም ሁሌም እየተበደሩ መኖር አይቻልም። ገንዘብ የሚሰጡ አበዳሪዎችም የጠየቅከውን ገንዘብ በሙሉ ላይሰጡም ይችላሉ።»

የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ራማን ሙድዴ የኡጋንዳ የምክር ቤት አባላትንም ክፉኛ ወቅሰዋል። «የእንደራሴዎች ምክርቤት አባላት የቀረበላቸውን የብድር ስምምነት ዝምብለው ያጸድቃሉ። ለምን ቢባል ከገንዘቡ በአንዱ ወይም በሌላ መልኩ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ስለሚያውቁ» በማለት ነቅፈዋል። ሂደቱ በዚህ ከቀጠለና የለውጥ ሂደት ከሌለ የምክርቤት አባላቱ ብድሮችን ማጽደቃቸውን ይቀጥላሉ፤ መንግስትም የተበደረውን አለአግባብ መጠቀሙን ይቀጥላል» በማለትም ያክላሉ።

የአሜሪካ ዶላርምስል፦ Fotolia/ia_64

 

የብድር ገንዘቡ የት ገባ?


ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2024 ባወጣው የሙስና መዘርዝር ውስጥ ኡጋንዳ 26ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል። መስናን በመዋጋት ረገድም መሻሻሎች እንዳላሳየች በማከል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ1986 ጀምሮ በዩዌሪ ሙሰቬኒ የሚመራው የኡጋንዳ መንግስት ከሐገር ውስጥና ከውጭ በብድር የሚያገኘው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋትና የሐገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ አያውለውም የሚል ትችት በፖለቲከኖችና የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ይቀርብበታል። 
በካምፓለ የሚኖረው የንግድ ጉዳዮች ዘጋቢ ሎውረንስ ኮኮ ለዶይቸቨለ የእንግሊዝኛ ቋንቋ አገልግሎት በሰጠው ቃለ ምልልስ « የኡጋንዳ መንግስ ከአሜሪካ ብቻ በትሪልዮን የኡጋንዳ ሽልንግ የሚቆጠር ገንዘብ መበደሩን በመግለጽ ገንዘቡ የት ገባ? በማለት ይጠይቃል። ለቁጥር የሚታክት ብድር ተሸክሞ መቀጠል እንደማይቻል በማከል።

የነዳጅ ማደያ በካምፓላ ከተማምስል፦ Hajarah Nalwadda/AP Photo/picture alliance

የነዳጅ ዘይት መገኘት ተስፋና ስጋት


ኡጋንዳ በቅርቡ የነዳጅ ዘይት ማምረት ጀምራለች። ይህም የሐገሪቱን ኢኮኖሚ በማነቃቃት የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ይገመታል። በዩዌሪ ሙሶቨኒ የሚመራው መንግስት ከነዳጅ ምርት የሚያገኘውን ተጨማሪ ገንዘብ እግምት ውስጥ በማስገባት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2026/ 2027 ዓ.ም አመታዊ የሐገሪቱ የዕድገት ምጣኔ 10.4 % ለማድረስ ማቀዱን አስታውቋል። 
ይሁን እንጂ በሐገሪቱ የተንሰራፋውን ሙስና መላ ካልተበጀለት ከነዳጅ ዘይት ምርት የሚመነጨውን ገንዘብ ተጠቅሞ የሐገሪቱን ቁልል ዕዳ ለማቃለል አስቸጋሪ እንደሚሆን የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አሎር ይገልጻሉ። በስነ ሐሳብ ደረጃ የነዳጅ ምርት የተሻለ ገንዘብ እንደሚያመነጭ ይሁንና በተግባር  ሙስና ማቆም ካልተቻለ ይህ እውን ሊሆን እንደማይችል በማከል።
« እርግጥ ነው በተሻሉ ፖሊሲዎችና በተሻለ አዲስ አመራር በኡጋንዳ ያለውን አሁናዊ ሁኔታ መቀየር ይቻላል። የአለፈውን ልማድ ለመቀየር ዘግይተናል ማለት አይቻልም። መንግስት በነዳጅ ምርቱ ላይ ከፍተኛ ተስፋን ጥሏል። የነዳጅ ምርት ሲመጣ እሱን ሸጠው ገንዘብ በማመንጨት ዕዳቸውን መክፈል እንደሚችሉ ያስባሉ። ይህ በሥነ ሐሳብ ደረጃ ትክክል ነው። በተግባር ግን ሙስናን ማቆም አለብን። የተሻለ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል። ኡጋንዳ የተሻለ የመደራደር አቅም ሊኖራት ይገባል። ብድሩን በተመለከተ የሚደራደሩ የመንግስት አካላት ለኡዳንዳ ጥሩ የድርድር ሐሳቦች ሊኖራቸው ይገባል። ምክንያቱም በመጨረሻው ሰዓት መጥፎ ድርድሮች ከተደረጉ ጦሱ ለሁላችንም ይተርፋል።»
በቅርቡ በኡጋንዳ የሚካሄደው ምርጫ ምን ይዞላት ወይ ይዞባት ይመጣ ይሁን? 

ነበ ቺዪ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር 

ታምራት ዲንሳ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW