1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የማኅበረሰቡን ትኩረት የሚሻው የሴት ልጅ ግርዛት

ማክሰኞ፣ የካቲት 4 2017

የሴቶችን የመዋለጃ አካል መተልተል አስከፊና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት መሆኑን በተለይ በሂደቱ ያለፉበት ሰለባዎች ከሚያሳድረው አካላዊም ሆነ ስነልቦናዊ ጉዳት አኳያ አጥብቀው ይቃወሙታል። ዛሬም ግን በሚሊየኖች የሚቆጠሩ አዳጊ ሴት ልጆች ለዚህ የመጋለጥ ስጋት ላይ መሆናቸው እየተነገረ ነው።

FGM
የሴትን ልጅ የመዋለጃ አካል መተልተል ይቁም! ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Reuters/S. Modola

የማኅበረሰቡን ትኩረት የሚሻው የሴት ልጅ ግርዛት

This browser does not support the audio element.

 

 

በየዓመቱ በጎርጎሪዮሳዊው የዘመን አቆጣጠር የካቲት 6 ቀን በሴት ልጅ ላይ የሚፈጸመው ግርዛት ይቁም የሚለው ዘመቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይታሰባል። በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም 230 ሚሊዮን በላይ ግርዛት የተፈጸመባቸው አዳጊ እና አዋቂ ሴቶች እንደሚገኙ UNICEF ያወጣው መረጃ ያመለክታል። ጉዳቱ ከፍተኛ ነው። በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥም እንዲሁ 27 ሚሊዮን ተጨማሪ አዳጊ ሴት ልጆች ለዚሁ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት የመጋለጥ አደጋ ላይ ናቸው። በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2025 ብቻ 4.4 ሚሊዮን የሚጠጉት ሴት ልጆች ለግርዛት ሊጋለጡ እንደሚችሉ ተገምቷል። ኢትዮጵያ ውስጥም በአንዳንድ አካባቢዎች ድርጊቱ መፈጸሙ እንደቀረ የሚገልጹ ቢኖሩም በተቃራኒው ለዓመታት የተከናወኑ ቅስቀሳና ትምህርቶች ምንም ለውጥ አለማምጣታቸው እየተነገረ ነው።

የሴቶችን የመዋለጃ አካል መተልተል አስከፊና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት መሆኑን በተለይ በሂደቱ ያለፉበት ሰለባዎች ከሚያሳድረው አካላዊም ሆነ ስነልቦናዊ ጉዳት አኳያ አጥብቀው ይቃወሙታል። ዛሬም ግን በሚሊየኖች የሚቆጠሩ አዳጊ ሴት ልጆች ለዚህ የመጋለጥ ስጋት ላይ መሆናቸው እየተነገረ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በአንዳንድ የከተሞች አካባቢ ጊዜ ያለፈበትና እየቀረ የመጣ ነው ቢባልም አንዳንዱ ጋ ደግሞ ዛሬም ስጋት እንደሆነ ነው።

የሴት ልጅ ግርዛት የሚፈጸምባቸው ሃገራት

በመላው ዓለም ከ190 በላይ ሃገራት ቢያንስ በ92ቱ የሴት ልጅ ግርዛት እንደሚፈጸም መረጃዎችን ዋቢ ያደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ። ይህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ይቁም የሚለው ቅስቀሳ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተጀመረ ወዲህ ግን ከእነዚህ መካከል 51 የሚሆኑት ሃገራት ድርጊቱ እንዳይፈጸም በሕግ አግደዋል። ሕጉን በመቀበል ደረጃም አንዳንዶች እራሱን የቻለ ደንብ አውጥተውለት ገሚሶቹ ደግሞ በተለየ የሴት ልጅን የመዋለጃ አካልን መተልተልን የሚቃወም በወንጀለኛ መቅጫ ደንብ፤ ልጆችን የመካለል  ሕግ አድርገው፤ ቅጣትም ደንግገውለታል።

በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት ይህን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትበመፈጸም ይወቀሳሉ ይተቻሉ። አንዳንዶቹ ጋ ድርጊቱ እያደር እየቀነሰ ብቻ ሳይሆን እየቀረ ቢመጣም የባህል አልፎ አልፎም የሃይማኖት ሽፋን እየተሰጠው እንዳይቆም የሚሟገቱለት አልጠፉም። ለምሳሌ ሶማሊያ እና ማሊ ድርጊቱ ዛሬም በስፋት የሚፈጸምባቸው ሃገራት ናቸው።

የዘንድሮው የሴት ልጅ ግርዛት ይቁም የሚለው ዘመቻ የታሰበው ይህን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለማስቆም የሚደረገው ጥረት ፍጥነቱን ይጨምር በሚል መሪ ቃል ነው።

የሴት ልጅ ግርዛት በኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸመው የሴት ልጅ ግርዛት ቢቀንስም ድርጊቱን ሙሉ ለሙሉ ለማስቆም የተጠናከረ ጥረት እንደሚያሻ የተመድ ተቋማት አመልክተዋል። በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት ተራድኦ UNICIF እና በመንግሥታቱ ድርጅት የስነሕዝብ ድጋፍ UNFPA ይፋ ያደረጉት መረጃ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ፈጽሞ ለማስቆም ጥረቱ በአምስት እጅ እጥፍ መፍጠን ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ግን እስከ በጎርጎሪዮሳዊው 2030 ዓ,ም ድረስ ከ2,5 ሚሊየን በላይ አዳጊ ሴት ልጆች ለዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት የተጋለጡ መሆናቸው ተገልጿል።

ከዓመታት በፊት በተከታታይ በሰፊው የተከናወኑኅብረተሰቡን የማስተማሪያ እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ውጤት እያመጡ መሆኑን የሚገልጹ ብዙዎች ናቸው። ከእነሱ መካከል በሲዳማ ክልል ይርጋለም ከተማ የህክምና ባለሙያ የሆኑት ሲስተር ኂሩት፤ በአሁኑ ጊዜ የሴት ልጅ ግርዛት በከተሞች አካባቢ መቅረቱን ነው የገለጹልን።

ሲስተር ኂሩት እንደውም ከተሞች አካባቢ ይሄ ጎጂ ልማዳዊድርጊት አልቀረም እንዴ ብለው የሚጠይቁ ሁሉ አሉ ብለውናል። በገጠር አካባቢ ድርጊቱ በስፋት የሚፈጸም ቢሆን ኖሮ ጉዳዩ አደባባይ መውጣቱ አይቀርም ነበርም ባይ ናቸው።

ጋምቢያ ውስጥ የሴት ልጅ ግርዛት እንዲቆም የሚደረገው ቅስቀሳና ጥረት ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Malick Njie/REUTERS

በአንጻሩ ይህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ዛሬም በስፋት የሚፈጸምበት አካባቢ አለ ያሉን ሌላዋ የጤና ባለሙያ ሲስተር መዲና ናቸው ከደሴ። እሳቸው እንደሚሉት ድርጊቱን የሚፈጸመው በባህል ሽፋን እንደመሆኑ እንዲቀር የማይፈልጉ አሉ።  

የይርጋለም ከተማን ተሞክሮ እንደአብነት በመጥቀስ ከተሞች አካባቢ ቀርቷል የመባሉን ነገር ያነሳንላቸው ሲስተር መዲናም በደሴ ከተማም ሴት ልጅን የሚያስገርዝ ወላጅ የለም ነው የሚሉት።

በደቡባዊ ኢትዮጵያ አማሮ ልዩ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ ያነጋገርናቸውእናት በተቃራኒው በሚኖሩበት አካባቢ የሴት ልጅ ግርዛት አይፈጸምም። ከአጎራባች ክልል ስለዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ከሚሰሙት በቀር በባህላቸው እንደሌለ ይናገራሉ።

የአማሮዋ እናት እንደሚሉት ከሆነም ሴትን ልጅ ገና በለጋ ዕድሜ መዳርም እነሱ ጋ አልተለመደም። ቤተሰቦች እንደየአቅማቸው በአካባቢው ትምህርት ቤቶች ካሉም እንዲማሩ ያደርጋሉ። 

የሴትን ልጅ የመዋለጃ አካል መተልተል ፊሜል ጀኒታል ሙትሌሽን የሚለው አገላለጽ፤ ድርጊቱ በሴቷ የመዋለጃ አካል ላይ የሚያደርሰውን አካላዊና ስነልቡናዊ ጉዳት ለማሳየት የቀረበ ሃሳብ ነው። ድርጊቱን አጥብቀው የሚቃወሙት ሁሉ፤ ግርዛቱ ከተፈጸመበት የልጅነት ዕድሜ አንስቶ ሴቲቱ አድጋ ለአቅመ ሔዋን ደርሳ ልጅ ለመውለድ ብትበቃ ከዚያም አልፎ በዕድሜዋ ገፍታም ጉዳቱን እያስታመመች ለመኖር እንደምትገደድ በመግለጽ ነው እንዲቀር የሚያሳስቡት። ሲስተር መዲናም ይህንን ያጠናክራሉ።

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱን ለማስቆም የሚደረገው ቅስቀሳ መቀዛቀዝ  

የሴት ልጅ ግርዛት ይቁም የሚለው ቅስቀሳ እና ትምህርት መቀዛቀዙ ይታያል። በተለይም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንቅስቃሴ በተለያዩ ምክንያቶች ሲስተጓጎል ይደረጉ የነበሩ ጥረቶች መደብዘዛቸው አያጠያይቅም። ሲስተር መዲና እንዲህ ያለውን ስር የሰደደ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለማስቆም በየደረጃው ያልተቆራረጠ ቅስቀሳና ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ያሳስባሉ።

UNICEF እና UNPA በጋራ ባወጡት መግለጫቸው የሴት ልጅን ግርዛት ለማስቆም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ያመለከቱት። ለዚህ ደግሞ አዋቂ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች፤ እንዲሁም ወጣቶች፤ የዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ሁሉ፤ ኅብረተሰቡም ሆነ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በትብብር ይህን ለማስቆም እንዲያደርጉም አሳስበዋል። ዩኒሴፍ ያወጣው አንድ ጥናት ከ25 ዓመታት በኋላ በ29 ሃገራት የሚወለዱ 500 ሚሊየን የሚገመቱ አዳጊ እና አዋቂ ሴቶች ተወልደው ይኖራሉ። ይህ ድርጊት ከወዲሁ እንዲቆም ካልተደረገም እነዚህ ሁሉ የጎጂው ልማድ ሰለባ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው። ሃሳባቸውን ያካፈሉንን እናመስግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW