1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ትኩረት የሚያሻው የትልቁ አንጀት ካንሰር

ማክሰኞ፣ መጋቢት 16 2017

መጋቢት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለኅብረተሰቡ ስለትልቁ አንጀት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር ነው። የትልቁ አንጀት ካንሰር በቀዳሚነት የበርካቶችን ሕይወት ከሚቀጥፉ የካንሰር ዓይነቶች በሦስተኛ ደረጃ የሚገኝ ነው።

የትልቁ አንጀት ካንሰር ሥዕላዊ መግለጫ
የትልቁ አንጀት ካንሰር ሥዕላዊ መግለጫ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ crytallight/Depositphotos/IMAGO

ትኩረት የሚያሻው የትልቁ አንጀት ካንሰር

This browser does not support the audio element.

 

የትልቁ አንጀት ካንሰር አጠቃላይ መረጃ

በዓለም የጤና ድርጅት ጥናት መሠረት በጎርጎሪዮሳዊው 2022 ዓ,ም, በመላው ዓለም 20 ሚሊየን ገደማ ሰዎች በምርመራ ለካንሰር መጋለጣቸው ተረጋግጧል። 9,7 ሚሊየን ሰዎች ደግሞ በካንሰር ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። በተጠቀሰው ዓመትም በግንባር ቀደምትነት ለበርካቶች ሞት ምክንያት የሆኑት የሳንባ፤ የትልቁ አንጀት እና የማሕጸን በር ካንሰር እንደሆኑም ያመለክታል። 

በአዳማ ሆስፒታል የህክምና ኮሌጅ የአንጀት፤ የጉበት እና የጨጓራ ህክምና ልዩ ባለሙያ ዶክተር ፈቃዱ ግርማ እንደሚሉት ከትንሹ አንጀት ይልቅ በብዛት በካንሰር የሚጠቃው ትልቁ አንጀት ነው።

ለትልቁ አንጀት ካንሰር አጋላጭ ምክንያቶች

ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት ሴቶችን የሚያጠቃው የጡትና የማሕጸን በር ካንሰር ሲሆን የትልቁ አንጀት ካንሰር በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል። የትልቁ አንጀት ካንሰር ባደጉት ሃገራት አስቀድሞ በሚደረገው ክትትል አማካኝነት የሚያደርሰው ጉዳት እየቀነሰ መሄዱን ያስታወሱት ዶክተር ፈቃዱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ባላደጉ ሃገራት ግን እየጨመረ መሄዱን ጥናቶች እንደሚያሳዩም ገልጸዋል። ለትልቁ አንጀት ካንሰር ከሚያጋልጡ ምክንያቶች ቀዳሚው እና ሁሉንም ሰው የሚመለከተው ከዕድሜ ጋር የተያያዘው ነው። ይህንና ሌሎች መንስኤዎችን ዶክተር ፈቃዱ ያብራራሉ።

ከመጠን ያለፈ የሰውነት ውፍረት ሌላው አጋላጭ ሲሆን፤ የቅርብ ቤተሰብ ማለትም እናት አባት፤ ወንድም እህት ለካንሰር የተጋለጡ ከሆነ ቤተሰቦች ለካንሰር የመጋለጥ እድላቸው ሊሰፋ እንደሚችልም አመልክተዋል። ከዚህም ሌላ አመጋገብ እና የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግም ሌላው አጋላጭ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ነው የተናገሩት። 

በተለይ በቅርብ ቤተሰብ ደረጃ የካንሰር ታማሚ ካለ እነዚህ ወገኖች ቅድመ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ እንደሚመከር ነው ባለሙያው ያሳሰቡት።

ጀርመን ሀገር እያንዳንዱ ሰው የጤና መድኅን /ኢንሹራንስ/ሊኖረው ግድ ነው። እነዚህ የጤና መድኅኖች አንድ ደንበኛቸው 50 ዓመት ሲሞላው «የትልቁ አንጀት ካንሰር ከዚህ የእድሜ ክልል ጀምሮ ያሰጋልና ባስቸኳይ ካንሰር ቅድመ ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራሉ» የሚል ደብዳቤ ይልካል። እናም ያ ሰው ባያስብበትም የሚያስታውሱበት የጤና ስርዓት አላቸው። ይህም የጤና ችግሩ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት አስቀድሞ ለመከላከል እየረዳ ነው።

አስቀድሞ በሚደረግ ምርመራ ሊያስከትል የሚችለውን የጤና ጉዳትና የሕይወት አደጋ መከላከል እንደሚቻል የህክምና ባለሙያዎች በየጊዜው ይመክራሉ።ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ David Davies/empics/picture alliance

አንጀት ካንሰር ምልክቶች

የትልቁ አንጀት ካንሰር በዓለም ደረጃ ሰዎችን ሕይወት ከሚቀጥፉት ቀዳሚ ከሚባሉት አንዱ ነው። በአብዛኛው ወደ ካንሰር የሚቀየሩት አንጀት ውስጥ የሚፈጠሩ እባጮች በመሆናቸው ነው ቅድመ ምርመራ ምድረግ የሚመከረው። 

አንዳንዴ ምልክት ባይኖርም ስር ሰድዶ ከመባባሱ በፊትእነዚህ ምልክቶች ሲያጋጥሙ በቶሎ ወደ ሀኪም መሄድ ያስፈልጋል ይላሉ ዶክተር ፈቃዱ። ከወትሮው የተለየ የአይነምድር መቅጠን ወይም መድረቅ ሲያጋጥም፤ በዚያም ላይ ደም የተቀላቀለት አይነምድር ሲኖር፤ ወይም ደም ሲያስቀምጥ፤ ያልታሰበ ክብደት መቀነስ ሲያጋጥም ሰዎች ሊጠረጥሩ ይገባል ባይናቸው። በተለይ ድንገተኛ ተቅማጥ ሲያጋጥምም  አሜባ ነው በሚል መዘናጋት እንዳይኖር ዶክተር ፈቃዱ ያሳስባሉ፤

ህክምናው

ሰዎች ህመም ሲሰማቸው ፈጥነው ወደ ሀኪም ቤት እንዲሄዱ በየጊዜው የህክምና ባለሙያዎች ይመከራሉ። በተለይ እንደ ካንሰር ዓይነቱ ህመም ቶሎ ሲደረስበትና ህክምናውም ወዲያው ሲጀመር የመዳን እድሉ ከፍተኛ እንደሆነ በዚህ ህክምና ውስጥ አልፈው ጤናቸውን ያገኙ ወገኖችም እማኝነታቸውን ይሰጣሉ። ዶክተር ፈቃዱም ይህንኑ ያጠናክራሉ።

በጎርጎሪዮሳዊው 2022 ዓ,ም  የዓለም የጤና ድርጅት ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ውስጥ በተጠቀሰው ዓመት ከ80 ሺህ በላይ አዲስ የካንሰር ታማሚዎች ተመዝግበዋል። ቁጥሩ የሚያሳየው የተመዘገበው እንጂ ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ይገመታል። የዘርፉ የህክምና ባለሙያ እንዳሳሰቡት ከተለመደው የተለየ ስሜትም ሆነ ምልክቶች ሲታዩ ፈጥኖ መርመር የከፋ ጉዳት እንዳያጋጥም እንደሚረዳም ይታመናልና ሰዎች ለዚህ ትኩረት እንዲሰጡም መክረዋል። በአዳማ ሆስፒታል የህክምና ኮሌጅ የአንጀት፤ የጉበት እና የጨጓራ ህክምና ልዩ ባለሙያ ዶክተር ፈቃዱ ግርማን ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW