ትኩረት የሳበው አዲሱ ልውጥ የኮሮና ተሐዋሲ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 16 2015![ፎቶ ከማኅደር፤ ኮሮና ተሐዋሲ](https://static.dw.com/image/62765777_800.webp)
ትኩረት የሳበው ልውጡ የኮሮና ተሐዋሲ
ከሁለት ዓመት በላይ የዓለምን እንቅስቃሴ ገትቶ የከረመው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወሬው በቀዘቀዘበት በዚህ ወቅትአዲስ የተከሰተው ልውጥ ተሐዋሲ ማነጋገር ጀምሯል። ልውጡ የኮሮና ተሐዋሲ በወረርሽኝ መልክ ከሆነ ሀገር ተነስቶ የሚያዳርስ ሳይሆን በየሀገሩ ያለው ወይም የነበረው ተሐዋሲ አይነቱን እየለዋወጠ ሊከሰት እንደሚችል ነው የዓለም የጤና ድርጅት የገለጸው። አስቀድሞ ተሐዋሲው በመላው ዓለም ተሰራጭቶ በየሃገራቱ የእንቅስቃሴ ገደብ በነበረበት ወቅት ብዙዎች አንዳች መከላከያ የሚሆን መድኃኒት ተገኝቶ እንደልብ ለመንቀሳቀስ ሲመኙ ነበር። ያኔም ቢሆን የህክምና ባለሙያዎች ተሐዋሲው አይነቱን እየለዋወጠ አብሮ ይከርም እንደሆነ እንጂ ተጠራርጎ ይወገዳል የሚል ግምት እንደሌላቸው ይገልጹ ነበር። አሁን በአራት ሃገራት የተገኘው ልውጡ ተሐዋሲ የባለሙያዎቹን ማሳሰቢያ ያረጋገጠ ይመስላል።
የዘርፉ ተመራማሪዎችም የልውጡን ተሐዋሲ ባህሪያት ለማጥናት ጥድፊያ ላይ መሆናቸውን የዓለም የጤና ድርጅት ገልጿል። በድርጅቱ ኮቪድ 19ን የመከላከል እንቅስቃሴ የሚመለከት ዘርፍ አስተባባሪዋ ዶክተር ማሪያ ፋን ኬርኮቭ ስለ ልውጡ ተሐዋሲ እንዲህ ይላሉ።
«ልውጦቹ ተሐዋስያን ከሌላ ሀገር ወይም ከሌላ ቦታ ሊመጡ ይችላሉ የሚለው አስተሳሰብ የተሳሳተ ይመስለኛል፤ አደገኛም ነው። ምክንያቱም ችግሩ ሌላ ቦታ ነው ተብሎ ይታሰባል። ሆኖም ግን ተሐዋሲው በአሁኑ ጊዜ በጣም እየተሰራጨ በመሆኑ ቀስ በቀስ እየተቀየረ ነው።»
ባለፈው ሳምንት ይፋ እንደተደረገው በጣም የተለየ የተባለው ልውጥ ተሐዋሲ በአራት ሃገራት ማለትም፤ በዴንማርክ፤ እስራኤል፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩናይትድ ስቴትስ ተገኝቷል።
የዓለም የጤና ድርጅት ለአዲሱ ልውጥ ተሐዋሲ BA.2.86 የሚል መለያ ሰጥቶታል። ሃገራትም በየበኩላቸው ክትትል እያደረጉ ስያሜውን እንዲንዲሰጡ በማመልከትም የየራሳቸውን ምዝገባ እንዲያካሂዱም አሳስቧል።
አሜሪካን ውስጥ የተሐዋሲው ስርጭት መጨመር
ዩናይትድ ስቴትስ የበሽታዎች ቁጥጥር እና መከከል ተቋም CDC ለኅብረተሰቡ ላከው በተባለውና በየማኅበራዊ መገናኛው በተራጨው ማሳሰቢያ XBB የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ ልውጥ ተሐዋሲ የህመም ምልክቶቹ ከወትሮው የተለዩ እና ሰዎች መያዛቸውን ሳያውቁ በፍጥነት ሊዛመት የሚችል አይነት እንደሆነ ያመለክታል። ባለፉት ዓመታት ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት ሕይወትም ሆነ ጤና ላይ ያስከተለው ከባድ ተጽዕኖ ያሳሰባቸው ወገኖች ያ አስጨናቂ ጊዜ ዳግም የመምጣቱ አዝማሚያ ይሆን በሚል ሰግተው መረጃውን ሲቀባበሉ በመመልከታችን ስለመረጃው ተአማኒነት እና በአሁኑ ጊዜ አሜሪካን ውስጥ የተሐዋሲውን ስርጭት ይዞታ እንዲያብራሩልን በዩናይትድ ስቴትስ ቨርጂኒያ ግዛት የውስጥ ደዌ ህክምና ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ያሬድ ወንድምኩንን ጠየቅን። እሳቸው እንደሚሉት ካለፈው ሰኔ ወር አንስቶ ባሉት ጊዜያት የተሐዋሲው ስርጭት ከፍ ብሏል። እንዲያም ሆኖ ልውጡን ተሐዋሲ ከግምት በማስገባት የተዘጋጁ የተሻሻሉ ክትባቶች በመጪው መስከረም ወር እንደሚወጣ መታወቁም የመከላከሉን አቅም ያጠናክራል ብለው ስባሉ።
አሁን አሜሪካን ውስጥ እየተሰራጨ የሚገኘውየኮሮና ተሐዋሲ አይነት ኦሚክሮን የተባለው መሆኑን የገለጹት የህክምና ባለሙያው እስከዛሬ የሚያገለግሉት የህክምናውም ሆነ የምርመራው ስልቶች ለዚህም እንደሚረዱ ነው የሚያስረዱት።
ስጋቱ ምን ይመስላል?
በአራት ሃገራት ውስጥ ስለተገኘው ልውጥ ተሐዋሲ ማብራሪያ የሰጡት በዓለም የጤና ድርጅት ኮቪድ 19ን ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚመለከተውን ዘርፍ የሚያስተባብሩት ዶክተር ማሪያ ፋን ኬርኮቭ እንደሚሉት አሁን የተገኘው ልውጡ ተሐዋሲ ፤ «በመላው ዓለም ላይ ተጽዕኖ የሚያመጣ አይነት አይደለም።»
በተለያዩ ሃገራት የተገኙትን ልውጥ ተሐዋስያን በተመለከተም የተለያየ ባህሪያቸውን፣ የዕድገታቸውን ሁኔታ፤ ያላቸውን የተለየ ቅርጽ፣ የአደገኛነታቸውን ይዞታ እንዲሁም እስካሁን ያለውን የመከላከል አቅም ማለትም ምርመራው፤ ህክምናውም ሆነ ክትባቱ ያለውን አቅም ተመራማሪዎቹ እያጠኑ መሆኑንም አመልክተዋል። እስካሁን በተገኘው መረጃ መሠረትም በፍጥነት የመተላለፍ አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑ ተደርሶበታል ነው ያሉት ባለሙያዋ። ያም ሆኖ ግን አሁንም ጥናት ምርምሩ መቀጠሉን አመልክተዋል።
«በቅርብ ክትትላችንን እንቀጥላለን፤ ለዚህም በተለይም በህክምናውም ሆነ በክትባቱ በኩል ለውጥ ማድረግ ያስፈልግ እንደሆነ መረጃዎችን ለማግኘት ብዙ ጥናቶች መደረግ ይኖርባቸዋል። እስካሁን ግን የተለወጠ ነገር አላገኘንም፤ ሆኖም ግን ይህንን መከታተል ይኖርብናል።»
ኮሮና ተሐዋሲ በወረርሽነቱ ዓለም ባዳረሰበት ወቅት በምርምሩም ሆነ በህክምናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሰዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከመምከር ጎን ለጎን ተሐዋሲው በቀላሉ እንደማይወገድ ሲያሳስቡ ነበር። የመተንፈሻ አካላትን በመጉዳት ለከፋ ችግር ብሎም ለሞት የሚዳረገው ኮቪድ 19 ፕሮፌሰር ያሬድ እንደሚሉትም አብሮን መክረሙ የማይቀር ነው።
ምንም እንኳን አይነቱ አዲስ ነው ስለተባለው ልውጥ የኮሮና ተሐዋሲ ተመራማሪዎች ያሉት ነገር ባለመኖሩ አሁን ብዙ መረጃ ባይኖርም ያለውን የኮቪድ 19 መከላከያም ሆነ ህክምናው በተመለከተ በቂ ልምድ መገኘቱን ነው ፕሮፌሰር ያሬድ አጽንኦት የሰጡት። ምንም እንኳን ተሐዋሲው እየተለዋወጠ አብሮን የሚቆይ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም በየአካባቢው ከታየው ተሞክሮ በመነሳት ኅብረተሰቡም የተሻለ ግንዛቤ ማግኘቱ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ባይ ናቸው።
ስለተሐዋስያን ጠባይ እና ምንነት የሚመራመሩ ባለሙያዎች ማንኛውም ተሐዋሲ ወደሰዎች አካል ሲገባ በተለያዩ ምክንያቶች እራሱን እንደሚለውጥ ያመለክታሉ። በኮሮና ተሐዋሲም የታየው ይኸው ነው። ምንም እንኳን አሁን የተሻለ የምርመራም ሆነ ህክምና እንዳለ ቢነገርም መዘናጋት ለችግር እንደሚዳርግ ግን የሁሉም ምክር ነው። ለሰጡን ማብራሪያ ፕሮፌሰር ያሬድ ወንድምኩንን እናመሰግናለን።
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ