1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት የተነፈገ የመሰለው በሴቶች ላይ የሚፈጸም አስገድዶ መድፈር

ሰኞ፣ ጥቅምት 18 2017

«ድርጊቱ የተፈጸመው ምዕራብ ኦሮሚያ ጊምቢ ነው የሚል ጥቆማ ነበር የደረሰን፡፡ ወንጀሉ የተፈጸመበትን ስፍራ ለመለያት ጥረት ላይ እንገኛለን፡፡ ቢያንስ እስካሁን በዚያ ባሉ መዋቅሮቻችን መለየት የቻልነው መሰል ወንጀል በጊምቢ እና ጊምቢ ዙሪያ የተፈጸመ አለመሆኑን ነው፡፡ነቀምቴ ላይ ከሆነም ብለን በማጣራት ላይ ነን»የኦሮሚያ ክልል የሴቶች ጉዳይ ቢሮ

Hände
ምስል Colourbox

ትኩረት የተነፈገ የመሰለው በሴቶች ላይ የሚፈጸም አስገድዶ መድፈር

This browser does not support the audio element.

ትኩረት የተነፈገ የመሰለው በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት

በኢትዮጵያ በተለይም ግጭት በሚካሄድባቸው አከባቢዎች ለጥቃት ተጋላጭ ከሚሆኑ የማበረሰብ አካላት ሴቶችና ህጻናት ግንባር ቀደሞቹ መሆናቸው ይገለጻል፡፡ ይህንንም የሚያረጋግጡ ተደጋጋሚ ዘገባዎች ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ እየቀረቡ ነው። ሰሞኑን ደግሞ በምዕራብ ኦሮሚያ ትክክለኛ ስፍራው እስካሁን ባልተለየ፤ ነገር ግን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴ በርካቶች ባጋሩት በሁለት ታዳጊ ሴቶች ላይ በቡድን የተፈጸመ አስገድዶ መድፈርን በሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ብዙዎች ተረብሸል፡፡የኦሮሚያ ክልል የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ጉዳዩን እየተከታተለ ለሚመለከተውም አካል እያስገነዘበ መሆኑን ለዶቼቬለ ተናግሯል።ስዩም ጌቱ ከአዲስ አበባ ቀጣዩን ዘገባ ልኮልናል።

የአስገድዶ መድፈር አሳፋሪ ድርጊቱ አፈጻጸም

በተለይም ከትንንት ጀምሮ በስፋት የተጋራውና ብዙዎች እያወገዙት የሚገኘው ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ትክክለኛ ስፍራው እስካሁን ባልተለየ ቦታ ተከወነ የተባለው በሁለት ታዳጊ ሴቶች ላይ ስፈጸም በማህበራዊ መገናኛ ዘዴ የተጋራው ተንቀሳቃሽ ምስል እጅግ የሚረብሽ ነው፡፡ ሁለት ሴቶች በግዳጅ ስደፈሩ በግልጽ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስሉ በጸያፍ ቃላት የታጀበና የማህበረሰብን ባህል እሴት በጉልህ የጠሳ ስለመሆኑ ይስተዋላል፡፡
ዶይቼ ቬለ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጎጂዎችን አሊያም የተጎጂ ቤተሰቦችን በቀጥታ አግኝቶ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ለዛሬ ባይሰምርም ክትትሉን ግን ይቀጥላል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ሴቶች እና ህጻናት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ መብራት ባጫ እንደነገሩን ግን የወንጀሉ ድርጊቱ ገና መሰማቱ እንደመሆኑ የተፈጸመበትን ስፍራ በመለየት ለቀጣይ ሕጋዊ እርምጃ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ “መረጃውን እኔም ዛሬ ጠዋት ነው ያገኘሁት፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው ምዕራብ ኦሮሚያ ጊምቢ ነው የሚል ጥቆማ ነበር የደረሰን፡፡ ነቀምቴ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ግን ወንጀሉ የተፈጸመበትን ስፍራ ለመለያት ጥረት ላይ እንገኛለን፡፡ ቢያንስ እስካሁን በዚያ ባሉ መዋቅሮቻችን መለየት የቻልነው መሰል ወንጀል በጊምቢ እና ጊምቢ ዙሪያ የተፈጸመ አለመሆኑን ነው፡፡ በጸጥታ አካላትም ሆነ በመዋቅሮቻችን በኩል የደረሰ መሰል መረጃ እስካሁን ባይኖርም በጸጥታ ማደፍረስ ውስጥ በሚሳተፉ አካላት መሰል ቪዲዮ በመልቀቅ ተጠረጠሩት ግን ስላሉ እሱን ግን በማጣራት ላይ ናቸው፡፡ ነገሩ የተፈጸመው ነቀምቴ ላይ ከሆነም ብለን በማጣራት ላይ ነን” ብለዋል፡፡

ምስል Nariman El-Mofty/AP/picture allianc

ተጠርጣሪዎች እንዴት በቁጥጥር ስር ይዋሉ

አሰቃቂው የአስገድዶ መድፈር ድርጊቱ የተፈጸመበትን በመለየት ላይ እንገኛለን ያሉት የቢሮው ኃላፊዋ የጉዳዩ ተጨባጭነት ሳይረጋገጥ ወደ ሌሎች እርምጃ ለመሄድ አስቸጋሪ እንደሆነባቸውም ነው ያመለከቱት፡፡ “አሁን ቪዲዮውን ተመልክተን ከሌላ ቦታም መጥቶ ወለጋ የተፈጸመ ነው በሚል የተለቀቀ እንዳይሆን የት ተፈጸመ የሚለውን ማጣራት ቀዳሚው እርምጃችን ነው፡፡ የት ተፈጸመ የሚለውን ሳንለይ ወንጀሉን የፈጸሙትን በቁጥጥር ስር ማዋልም ሆነ ሌላ እርምጃ ማቀድ አስቸጋሪ ነው፡፡ ወንጀሉ የተፈጸመበትን ስፍራ ለመለየት ዛሬ ጠዋት አንድ ኮሚቴ አዋቅረን ስራውን እንዲሰራ አሰማርተናል፡፡ ቦታውን ስንለይ ግን ምን አይነት እርምጃ ነው የምንወስደው እንዴት እንህድበት እንዴትስ እናገኛቸዋለን የምለውን የምንሄድበት ይሆናል” ብለዋል፡፡

በምስራቅ ቦረና ዋጪሌ ወረዳ የተከሰተው የአደባባይ ሴት ልጅ ድብደባ

ከዚህ በፊት በምስራቅ ቦረና ዞን ዋጪሌ ወረዳ አንዲት የሶስት ልጆች እናት በገቢያ ፊት በእንጨት ላይ ታስራ በባለቤቷ ስትደበደብ የሚያሳይ ምስልም በርካቶችን ያስደነገጠ ነበር፡፡ የአከባቢው ሽማግሌዎች ወሰኑት በተባሌ ውሳኔ ሴትቷ እንዲያ በአሰቃቂ ሁኔታ ስትደበደብ የተመለከቱ ሁሉ ቁጣቸውን መግለጻቸውንም ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ይህንንም በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡን የኦሮሚያ ሴቶች እና ህጻናት ቢሮ ኃላፊዋ ጉዳዩ ልዩ ትኩረት አግኝቶ ተገቢ ያሉትን ፍትህ እንዲያገኝ ሂደት ላይ ነው፡፡ “ከህግ ጋር ተያይዞ አስተማሪ ቅጣት በድርጊት ፈጻሚው ግለሰብ ላይ እንዲወሰድ፤ በጉዳዩ ውስጥ የተሳተፉ የአገር ሽማግሌ የተባሉትም ከተለቀቁ በኋላ አሁን ዳግም በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ ተገቢው ክስ ተመስርቶ ፍርድ እንዲያገኝ ከክልሉ አቃቤሕግ ጋር በቅንጅት እየሰራንበት ነው፡፡ ጉዳዩን አባገዳዎችም እንዲያወግዙት በማድረግ ተጎጂዋ ሴትም ከልጆቿ ጋር እንድትረዳ እያደረግን ነው” ብለዋልም፡፡

የቀረበው ምክረ-ሃሳብ

የስነ-ጾታ ባለሙያ እና በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን በማቅረብ የሚታወቁት ናርዶስ ጩታ እየከፋ የመጣ የመሰለውን የሴት ልጅ ጥቃት እልባት ለመስጠት ይበጃል ያሉትን ሀሳባቸውን አስቀምጠዋል፡፡ “አንዱና ዋነኛው በተሌም ከባህል ጋር ተያይዞ ያለ ክፍተት ካለ ወርዶ ግንዛቤ በማስጨበጥ አብሮ መስራት ይፈልጋል፤ የሕግ ክፍተትም ሌላው በጥብቅ ሊሰራበት የሚገባው ጉዳይ ነው” ነው ሲሉ ምክረ-ሀሳባቸውን አስቀምጠዋል፡፡ 

ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW