1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"ሁልጊዜ ትልቅ ነገር ማድረግ እንችላለን" ሔመን በቀለ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 22 2016

"ሁልጊዜ ትልቅ ነገር ማድረግ እንችላለን ምንም የሚያግደን ነገር የለም።ቀለማችን ከየት ሃገር የመምጣታችን ከደሃም ሃገር መጥተን፣እንዲህ ዓይነት ትልቅ ቦታ በሳይንስ መሆን የለበትም፣ግን ባለን ዕውቀት ባለን ችሎታ ትልቅ ቦታ መድረስ እንችላለን" ሔመን በቀለ

USA | 3M Young Scientist Challenge | Hamam Bekele
ምስል 3M

ወጣቱ ተመራማሪ

This browser does not support the audio element.

ሔመን በቀለ፣ከኢትዮጵያ ወደ ዩናይትድስቴትስ የመጣው ገና የአራት ዓመት ልጅ ሳለ ነበር፤አሁን 14 ዓመት ሆኖታል። መኖሪያውን ከቤተሰቦቹ ጋር ቨርጂኒያ ውስጥ ያደረገው ሔመን ታዲያ የተወለደባት ኢትዮጵያን ዘንግቷት እንደማያውቅ ይናገራል። ልቁንም ይኖርባት በነበረው አዲስ አበባ ህይወትን ለማሸነፍ፣ ውሎአቸውን በከባድ ፀሐይ ቁር ጎዳና ላይ የሚያሳልፉ ብዙ ወገኖቹ  ሕይወት ዘወትር በአዕምሮው ይመላለስበታል።

ከእነዚህ ወገኖቹ መኻከል እንኳንየቆዳ ካንሰር ህክምና ማድረግ ቀርቶ፣የቆዳ ካንሰር የሚባል ህመም መኖር አለመኖሩን የማያውቁት በርካቶች መሆናቸውም ዕረፍት ይነሳው እንደነበር ይናገራል።

የቆዳ ካንሰር ህክምና ሳሙና

"ውልደትና ዕድገቴ ኢትዮጵያ ነው።በርካታ ሰዎች በከባድ ፀሐይ ላይ ለረጅም ሰዐት ሲሰሩ እመለከት ነበር።እያደግኹ ስሄድ ጉዳዩ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ እየገባኝ ሄደ።ካንሰርን ለመከላከል  በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች በማደግ ላይ ባሉ ሃገሮች ያለው ችግር በዚህ ጉዳይ  በትኩረት እንድሰራና የካንሰር ህክምና ሳሙና እንዳዘጋጅ አድርጎኛል።" ይላል።

የቆዳ ካንሰር ህክምና በትክክል የሚሰራ ብቻ ሳይሆን፣ለሁሉም ተደራሽ መሆን ቢችል፣ማንኛውም ሰው በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ሳይከፍል ዕድሜውን ለመቀጠል የሚያስችለውን ህክምና ማግኘት እንደሚያስችልም ወጣቱ ተመራማሪ ይናገራል።

እርሱ በምርምር ያገኘውና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገኘው ደረቅ ሳሙና፣የብዙዎች ህይወት ይቀየራል ብሎ ተስፋ አድርጓል።

ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሔመን፣ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በተሳተፉበት "የ 3M Young Scientist lab"ዓመታዊ ውድድር ተሳትፎ ነው የአሜሪካ ወጣቱ ተመራማሪ በመባል ሽልማትና ዕውቅናን የተጎናጸፈው። ወጣቱ የ25 ሺህ ዶላር ሽልማት ያገኘ ሲሆን ዕውቅናና ሽልማቱ ከዚህ የበለጠ እንዲሰራ እንዳነሳሳው አጫውቶናል።

አዳጊ ወጣት ሄመን በቀለ በምርምር ያገኘውና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገኘው ደረቅ ሳሙና፣የብዙዎች ህይወት ይቀየራል ብሎ ተስፋ አድርጓል።ምስል 3M

በትልቁ ማለም

ትልልቅ ነገሮችን ለመስራት ማለሙ ለጥሩ ውጤት እንዳበቃው የሚናገረው ወጣት ሔመን፣ሌሎችም የእርሱን ፈለግ እንዲከተሉ ምክር አለው።

"ትልልቅ ግቦች ካሏችሁ፣ማንኛውን ነገር ማከናወን የሚቻለው አልሞ በመነሳት ነው።በትልቁ አልማችሁ ተስታችሁ እሱን ለማሳካት ጠንክራችሁ ከተነሳችሁ ህልማችሁ ላይ እንደምትደርሱ ቃል እገባለኹ።"

የታዳጊው ሳይንቲስት ወላጅ እናት ወይዘሮ ሙሉእመቤት ጌታቸው እንደሚሉት፣ሔመን ከልጅነቱ አንስቶ ብዙ ማንበብና መጠየቅ የሚወድ ልጅ ነው።

"ከልጅነቱ ጀምሮ፣በጣም ብዙ ነገር ይጠይቃል።በአጭር መልስ ብዙም አይረካም።ብዙ ማብራሪያ ይፈልጋል ስለእያንዳንዱ ነገር ዓለም ላይ ያለውን ነገር።በጣም ጎበዝ አንባቢ ነው፤ልጅ ሆኖ ነው ገና ማንበብ የጀመረው።ማንበብ ለብዙ ነገር አስተዋውቆታል።ከእዛ ደግሞ አሁን እንደነገረህ ብዙ ጊዜ ትልቅ ነገሮች ላይ ነው የሚያልመው።እኛ እንደውም አንዳንድ ጊዜ፣ለራሳችን ቆይ ለእኛ አይሆንም በጣም ትልቅ ነገር ነው የሚፈልገው ለመወዳደር ከልጅነቱም።እኛ ያደረግነው ነገር ቢኖር በጣም ከማኀበረሰባችን ጋር የጠነከረ ግንኙነት አለን።የኢትዮጵያን እሴቶች ሰርቶ እዚህ ሃገር የመጣንበትን ዋናውን ነገር ለልጆቻችን በደንብ አድርገን ትልቁ ነገር ትምህርት ነውና ትምህርት ቅድሚያ እንደሆነ ስነስርዓቱንም በቤተክርስቲያንም ከማኀበረሰቡ ጋር ያለን ግንኙነት ጠቅሞናል።"

 ወይዘሮ ሙሉእመቤት፣ሔመን ያስመዘገበው ስኬት ሌሎች ልጆች ላይ የሚፈጥረው በራስ መተማመን  የበለጠ የደስታ ስሜት እንደፈጠረላቸውም ነው የሚናገሩት።

"እዚህ ሃገር ያሉ ልጆቻችን በሙሉ፣ሁልጊዜ ትልቅ ነገር ማድረግ እንችላለን ምንም የሚያግደን ነገር የለም።ቀለማችን ከየት ሃገር የመምጣታችን ከደሃም ሃገር መጥተን፣እንዲህ ዓይነት ትልቅ ቦታ በሳይንስ መሆን የለበትም፣ግን ባለን ዕውቀት  ባለን ችሎታ ትልቅ ቦታ መድረስ እንችላለን።"ብለዋል።
ታሪኩ ሃይሉ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW