1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትግራይ ዉስጥ በረሐብ የሚሞተዉ ሰዉ ቁጥር እየጨመረ ነዉ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 30 2016

የአበርገለ የጭላ ወረዳ ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ደግሞ በወረዳቸዉ ባለፉት አራት ወራት ብቻ ረሐብ 91 ሰዎች ገድሏል።የቤት እንስሳትም እያለቁ ነው ተብሏል።በክልሉ የተቋቋመው አስቸኳይ ምላሽ ለትግራይ የተባለ ኮሚቴ በበኩሉ ከተለያዩ አካላት ገንዘብ በማሰባሰብ ለችግረኛዉ ሕዝብ የምግብ እርዳታ የማቅረብ መጀመሩን አስታዉቋል።

ካለፈዉ መስከረም ወዲሕ በሁለት ወረዳዎች ብቻ ከ220 በላይ ሰዎች ሞተዋል
በትግራይ ክልል በረሐብ የሚሞተዉ ሰዉ ቁጥር እየጨመረ ነዉምስል Million Hailesilassie/DW

በሁለት ወረዳዎች ብቻ ካለፈዉ መስከረም ወዲሕ ከ220 በላይ ሰዉ ሞቷል

This browser does not support the audio element.

 

በትግራይ ክልል በረሃብና ረሐብ በሚያስከትለዉ በሽታ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ የተለያዩ ወረዳዎች ባለስልጣናት እስታወቁ።አፅቢ ወረዳ ዉስጥ ካለፈዉ መስከረም ወዲሕ 138 ሰዎች በረሐብ መሞታቸዉን የወረዳዉ ባለስልጣናት አስታዉቀዋል።የአበርገለ የጭላ ወረዳ ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ደግሞ በወረዳቸዉ ባለፉት አራት ወራት ብቻ ረሐብ 91 ሰዎች ገድሏል።የቤት እንስሳትም እያለቁ ነው ተብሏል።በክልሉ የተቋቋመው አስቸኳይ ምላሽ ለትግራይ የተባለ ኮሚቴ በበኩሉ ከተለያዩ አካላት ገንዘብ በማሰባሰብ ለችግረኛዉ ሕዝብ የምግብ እርዳታ የማቅረብ መጀመሩን አስታዉቋል።ይሁንና ኮሚቴዉ  ግልፅነት ይጎድለዋል የሚል ተቃዉሞ ገጥሞታል።

በትግራይ ከተካሄደ የሁለት ዓመት ጦርነት በኃላ በክልሉ የተከሰተው መጠነ ሰፊ ድርቅ ያስከተለው ረሃብአሁንም የበርካቶች ሕይወት መቅዘፍ መቀጠሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። በክልሉ በረሃብ በከፍተኛ መጠን ከተጎዱ ወረዳዎች መካከል ከሆነችው ከአበርገለ የጭላ ወረዳ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ከመስከረም ወር ወዲህ ባለው ግዜ የ91 ሰዎች ሕይወት በረሃብ ምክንያት ማለፉ የወረዳዎ የአስተዳደር አካላት ይገልፃሉ። እንደባለስልናቱ ገለፃ በአሁኑ ወቅት፥ ረሃብ ላይ ላሉ ዜጎች የተለያዩ ለጋሽ አካላት የተወሰነ ድጋፍ ማድረግ መጀመራቸው ተከትሎ ካለፉት ወራት ጋር ሲነፃፀር የሞት መጠኑ የቀነሰ ቢሆንም፥ አሁንም አሳሳቢ መሆኑ እንዲሁም የገበሬው ሃብት የሆኑ እንስሳትም የሚበሉት አጥተው እያለቁ ስለመሆኑ ያስረዳሉ። የአበርገለ የጭላ ወረዳ የማሕበራዊ ዘርፍ ሐላፊ አቶ አለማየሁ ገብረማርያም ለዶቼቬለ እንደገለፁት ወረዳው የከፋ ረሃብ እንደተከሰተበት፥ የሰው እና የእንስሳት ሞት እንደቀጠለበት ያነሳሉ። 

የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት በአፅቢ ወረዳ ለምግብ እጥረት ከተጋለጡት አብዛኞቹ ሕፃናትና እናቶች ናቸዉምስል Million Hailesilassie/DW

 

"በጥቅምት መጨረሻ እና ሕዳር መጀመርያ ከነበረው በረሃብ ምክንያት የሚሞት የሰው ቁጥር ብዛት አሁን ላይ ትንሽ ቀዝቀዝ ብሏል። ምክንያቱ ደግሞ ሰዎች በጣም ለተቸገሩት በተናጠል እርዳታ እያቀረቡ በመሆኑ ነው። ይሁንና ያልነበረ የእንስሳት ሞት ተበራክቷል። በአጠቃላይ ያለው መረጃ ሲታይም ከመስከረም ወር ወዲህ ባለው ግዜ በወረዳችን ብቻ 91 ሰዎች በረሃብ ምክንያት ሞተዋል። አሁንም አስቸኳይ እርዳታ ይፈለጋል" ሲሉ አቶ አለማየሁ ገብረማርያም ይገልፃሉ።

ሌላው በትግራይ የከፋ ረሃብና የታየባቸው ተብለው ከሚጠቀሱ ወረዳዎች መካከል በክልሉ ምስራቃዊ ዞን የምትገኘው እና ከአፋር ክልል ጋር የምትዋሰነው አፅቢ ወረዳ ሌላኛዋ ነች። በአፅቢ ረሃቡ በተለይም በህፃናት እና እናቶች ይበልጥ ከፍቷል። የአፅቢ ጤና ፅሕፈት ቤት ሐላፊ አቶ ሰለሙን ግርማይ እንደሚሉት ከሆነ፥ በወረዳው በተደረገ ጥናት መሰረት 96 ከመቶ እናቶች እንዲሁም 67 በመቶ የሚሆኑ ህፃናት ለረሃብ ተጋልጠው እንዳለ የጤና ባለሙያዎች ባደረጉት የዳሰሳ ጥናት መረጋገጡ ይናገራሉ። አቶ ሰለሙን "ጥናት ከተደረገባቸው እናቶች መካከል 96 በመቶ የምግብ እጥረት እንዳለባቸው ለማረጋገጥ ችለናል። በህፃናት በኩል ያለው መረጃ ስንመለከት ደግሞ 67 በመቶ የሚሆኑ በወረዳችን የሚገኙ ህፃናት የምግብ እጥረት ላይ መሆናቸው ባደረግነው ዳሰሳ አረጋግጠናል። ረሃቡ በተለይም በእናቶች እና ህፃናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑ፥ ፈጣን ምላሽ ካላገኘ ደግሞ አደጋው የከፋ እንደሚሆን ነው ይህ የጤና ባለሙያዎች ጥናት የሚያስረዳን" ይላሉ።

በአጠቃለይ በአፅቢ ወረዳ ከመስከረም ወር ወዲህ ባለው ግዜ 138 ሰዎች በረሃብ ምክንያት መሞታቸው በአስተዳደሩ ተገልጿል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ ለተከሰተው ረሃብ ምላሽ ለመስጠት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በቅርቡ ያቋቋመው አስቸኳይ ምላሽ ለትግራይ የተባለ የክልሉ አስተዳደር፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማሕበራት፣ የሃይማኖት ድርጅቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ባለሃብቶች ያካተተ ኮሚቴ የመጀመርያ ዙር የምግብ እርዳታ ለተራቡት ማቅረብ መጀመሩ አስታውቋል። እንደኮሚቴው ገለፃ በትግራይ በረሃቡ ምክንያት የእርዳታ ጠባቂዎች ቁጥር ወደ 4 ነጥብ 5 ሚልዮን ማደጉ ያስታወቀ ሲሆን ፥ ከነዚህ መካከል ለተወሰኑ የሚሆን 64 ሺህ ኩንታል እህል እስከ ነገ ረቡዕ ድረስ ለተረጂዎች ለማድረስ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑ ገልጿል። 

ትግራይ ክልል በረሐብ ለተጎዳዉ ህዝብ ርዳታ የሚያሰባስብና የሚያከፋፍል ኮሚቴ ተመስርቷልምስል Million Hailesilassie/DW

 

የአስቸኳይ ምላሽ ለትግራይ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋይ ገብረእግዚአብሔር "4 ነጥብ 5 ሚልዮን ህዝብ እርዳታ ፈላጊ መሆኑ መንግስት ገልጿል። ይህ ረሃብ ላይ ያለ ህዝብ ለመርዳታ 10 ሚልዮን ኩንታል እህል አልያም 40 ቢልዮን ብር መሰብሰብ ያስፈልጋል። ይህ ለማሰባሰብ ነው ኮሚቴው እየሰራ ያለው" ብለዋል።

በትግራይ የምግብ እርዳታ ላይ ዝርፍያ ተፈፅሟል ተብሎ ዓለምአቀፍ ተቋማት አቅርቦታቸው አቋርጠው እንደቆዩ ይታወቃል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በክልሉ አስተዳደር በተቋቋመው የእርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል የነበሩ የተወሰኑ አባላት ደግሞ የኮሚቴው አሰራር ግልፅነት የጎደለው እና ለሙስና የተጋለጠ በማለት ራሳቸው አግልለዋል። ከነዚህ መካከል የሆኑት የተቃዋሚው የፖለቲካ ፓርቲ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበር አቶ አሉላ ሃይሉ፥ ግልፅነት የጎደለው፣ ተጠያቂነት የሌለው እንዲሁም ተቋማዊ አሰራር የማይከተል የሃብት አሰባሰበ ዘዴ እንደማይቀበሉ ለክልሉ ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ ደብዳቤ በመፃፍ ከኮሚቴው አባልነት ራሳቸው ማግለላቸውን አስታውቀዋል። የባይቶና ጨምሮ ሌሎች አባላትም እንዲሁ ራሳቸው ከሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴው ማገልገላቸው በይፋዊ ገፃቸው እያስታወቁ ነው። በትግራይ ያለው ለረሃብ የተጋለጠ እርዳታ ፈላጊ ህዝብ ለመድረስ በሚደረግ ጥረት፥ ስርቆትና ማጭበርበር ፈተና ሆኖ እንዳለ ሲገልፁ ይስተዋላል።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ 

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW