1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ትግራይ ክልል ከጦርነቱ በኋላ የኅብረተሰብ አገልግሎቶች ታጉለዋል ተባለ

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ሐሙስ፣ ግንቦት 28 2017

ትግራይ ክልል ከጦርነቱ በኋላ የዳግም ግንባታ ሥራዎች ባለመከወናቸው በርካታ የኅብረተሰብ አገልግሎቶች እንደተስተጓጎሉ መሆናቸው ተገለጠ ። በሸራሮ ጤናና ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የመሰረተ ልማቶችም ለዓመታት ከአገልግሎት ውጪ ናቸው ተብሏል ።

ትግራይ ክልል፤ ሽሬ ከተማ የሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ
ትግራይ ክልል፤ ሽሬ ከተማ የሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ምስል፦ Million Haileselassie Brhane/DW

የኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ታጉለዋል

This browser does not support the audio element.

ትግራይ ክልል ውስጥ ከጦርነቱ በኋላ የዳግም ግንባታ ሥራዎች ባለመከወናቸው በርካታ የኅብረተሰብ አገልግሎቶች አሁንም እንደተስተጓጎሉ ተገለጠ ። በሸራሮ ጤና እና ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የመሰረተ ልማቶችም ለዓመታት ከአገልግሎት ውጪ ናቸው ተብሏል ። የክልሉ አስተዳደር በዓለምአቀፍ ተቋማት ድጋፍ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ለመጠገን ጥረት እያደረገ መሆኑ ዐሳውቋል ።

የትግራዩ ጦርነት ያደረሰው ዕልቂት

የትግራዩ ጦርነት በሰው ሕይወት ላይ ካደረሰው ጉዳት በተጨማሪ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት አውድሟል፣ መሰረተ ልማት በከፍተኛ ደረጃ ጎድቷል ። በጦርነቱ ሰማንያ በመቶ የሚሆኑ የጤና ተቋማት በተለያየ ደረጃ የሚገለፅ ውድመት እንደደረሰባቸው፣ በርካታ ትምህርት ቤቶች እንደወደሙ፤ በተለይም በገጠር አካባቢዎች የሚገኙ የንፁሕ ውኃ ማእከላት እንደተጎዱ መረጃዎች ያመለክታሉ ። ከጦርነቱ በኋላ በመሰረተ ልማት ላይ የደረሰውን ውድመት የሚተካ የዳግም ግንባታ ሥራዎች ሊሠሩ ይጠበቁ የነበሩ ቢሆኑም በሚፈለገው መጠን እየተከወነ አለመሆኑ ይገለፃል። 

በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን የምትገኘው ሸራሮ ከተማ በጦርነቱ ከፍተኛ ውድመት ከደረሰባቸው አካባቢዎች መካከል ናት። የሸራሮ ከተማ ኮምኒኬሽን ፅሕፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ገብረመድህን ኪሮስ፥ በሸረሮ የነበሩ ትምህርት ቤቶቾ፣ ጤና ተቋማት ጨምሮ ሌሎች አገልግሎት ሰጪ መሰረተ ልማቶች በጦርነቱ ከወደሙ በኋላ አሁንም ድረስ ከስራ ውጭ ሆነው ይገኛሉ ይላሉ። 

የኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች መስተጓጐል

ይህ ወድመት ከሚፈጥረው የኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ እንቅስቃሴ መስተጓጐል በተጨማሪ ከሰላም ስምምነቱ በኃላ ዳግም ተሰርተው አልያም ተጠግነው ወደ ስራ አለመመለሳቸው በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ የፈጠረ መሆኑ ኃላፊው ይገልፃሉ። በሸራሮ እስካሁን በዳግም ግምባር ስራዎች ተጠግኖ ወደ ሥራ የተመለሰ አንድ ወድሞ የነበረ የውኃ ተቋም ብቻ መሆኑ ተገልጿል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር  በበጀት ውሱንነት እና ሌሎች ምክንያቶች በሚፈለገው ልክ የዳግም ግንባታ ሥራዎች እየተከወኑ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ይገልፃል። ይሁንና ከዓለምአቀፍ ተቋማት ጋር በመነጋገር የዳግም ግንባታ ስራዎች ለመከወን እንቅስቃሴዎች መኖራቸው ያመለክታል። 

በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የዳግም ግንባታ ጉዳዮች አስተባባሪ ኢንጅነር ቴድሮስ ገብረእግዚአብሔር ባለፉት ዓመታ የወደሙ የጤና ተቋማት እና ትምህርት ቤቶች ጨምሮ ሌሎች ወደሥራ ለመመለስ የጥገና ስራዎች ሲከወኑ መቆየታቸው የሚገልፁ ሲሆን፥ በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ይህ በከፍተኛ መጠን ለመከወን የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ስለመኖራቸውም ጠቁመዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW