1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትግራይ ክልል እየተፈፀሙ ናቸው በተባሉ ወንጀሎች ላይ ዘመቻ መከፈቱ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 9 2016

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በሕገወጥ ማዕድን ምዝበራ፣ ሰብአዊ ርዳታ መሸጥ እና በሌሎች የሕዝብ ሀብት ስርቆት ተሳትፎ ያላቸውን አካላት መያዝ መጀመሩ ዐሳወቀ። ስተዳደሩ በሕገወጥ ተግባራቱ ተሳትፎ ያላቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ይሁኑ ወታደራዊ መሪዎች አልያም ባለሀብቶች ለሕግ እንደሚቀርቡ ገልጿል።

ፎቶ ከማኅደር፦ የመቐለ ከተማ በከፊል
ፎቶ ከማኅደር፦ የመቐለ ከተማ በከፊልምስል Million Hailesilassie/DW

በክልሉ እየተፈፀሙ ናቸው በተባሉ ወንጀሎች ላይ ዘመቻ መክፈቱ ተገልጧል

This browser does not support the audio element.

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በሕገወጥ ማዕድን ምዝበራ፣ ሰብአዊ ርዳታ መሸጥ እና በሌሎች የሕዝብ ሀብት ስርቆት ተሳትፎ ያላቸውን አካላት መያዝ መጀመሩ ዐሳወቀ። አስተዳደሩ በሕገወጥ ተግባራቱ ተሳትፎ ያላቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ይሁኑ ወታደራዊ መሪዎች አልያም ባለሀብቶች ለሕግ እንደሚቀርቡ ገልጿል። እንዲያም ሆኖ በቅርቡ ከ20 በላይ በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ሲቪክ ድርጅቶች ከጦርነቱ በኋላ ጭምር በሴቶች ላይ ይፈጸማሉ ያሏቸውን ተደራራቢ ወንጀሎች በተመለከተ የተባለ ነገር የለም።

በትግራይ በተለይም በጦርነቱ እና ከጦርነቱ በኋላ ባሉ ጊዜያት በስፋት እየታዩ ናቸው ተብለው ከሚገለፁ ሕገወጥ ተግባራት መካከል በሕገወጥ መንገድ ወርቅን ጨምሮ የተለያዩ ማዕድናት አውጥቶ፣ ለሕገወጥ ገበያ አቅርቦ መሸጥ አንዱ መሆኑ ይገለፃል። በዚህ ተግባር የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ወታደራዊ አዛዦች እና የውጭ ሃገራት ዜጎች ጭምር እየተሳተፉበት እንዳለ በተለያዩ አካላት ይነገራል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ይህ በሕገወጥ መንገድ የሚፈፀም ማዕድናት የማውጣት እና መሸጥ ተግባር የሀገር ሃብት ከመዝረፍ በዘለለ፣ ዘላቂ የስነምህዳር ችግር የሚፈጥር እና ዝውውሩም ለተደራራቢ ወንጀል የተጋለጠ መሆኑን የሚገልፅ ሲሆን፥ ይህን ጨምሮ በክልሉ እየተፈፀሙ ናቸው በተባሉ ወንጀሎች ላይ ዘመቻ መክፈቱ አስታውቋል።

የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ «ሕገወጥ የማዕድን ማውጣት ሥራው፥ ኤክስካቫተር እና ሌሎች ተጠቅሞ በተለያዩ ቦታዎች የሚደረግ ቁፋሮ ነው። አደገኛ ኬሚካሎች ጭምር የሚጠቀሙበት፣ ቀጣይ ትውልድን ጭምር ወደ አደጋ የሚያስገባ ሆኖ ያለ፥ ማዕድኑ ከየት ወደ የት ይንቀሳቀሳል የሚል ደግሞ፥ ከዚህ ጋር የተሳሰሩ በርካታ ትልልቅ ወንጀሎች የሚፈፀሙበት ነው» ብለዋል።

ከዚህ የማዕድንና ምዝበራ በዘለለ በትግራይ በጦርነቱ ወቅት የወደሙ ተሽከርካሪዎች እና ከባባድ ወታደራዊ መሳሪያዎች  እንዲሁም ሌሎች በከፍተኛ ዋጋ የሚገመቱ ብረታብረት የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ወታደራዊ አመራሮች ጭምር በሚሳተፉበት የዝርፍያ ሰንሰለት የተሸጡበት ሁኔታ መኖሩን ይገለፃል።

በቅርቡ ከ20 በላይ በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ሲቪክ ድርጅቶች ከጦርነቱ በኋላ ጭምር በሴቶች ላይ ይፈጸማሉ ያሏቸውን ተደራራቢ ወንጀሎች በተመለከተ የተባለ ነገር የለም።ምስል Ximena Borrazas

ጀነራል ታደሰ ወረደ፦ «ሁሉም የብረታብረት ነጋዴ የሆነበት፣ ሁሉም ብረት መሠረተ ልማት ጨምሮ ለሽያጭ የሚቀርብበት ሁኔታ ነው ያለው። በጦርነቱ ግዜ የተቃጠሉ ወታደራዊ መሣሪያዎች ገዝቶ ወደ ሌላ አካባቢ የሚሸጥበት፣ ከትግራይ ክልል የሚያሸሽበት ሁኔታ አለ። ይህም ሌላ ትልቅ ችግር ነው» ሲሉ ገልፀዋል።

በዚህ ወንጀሎች የተሳተፉ የመለየት ሥራ እየከወነ መቆየቱን የሚገልፀው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፥ ካለፈው ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን፣ ጀምሮ ደግሞ ወደ ተግባር መግባቱን እና ተጠርጣሪዎችን ማደን መጀመሩን በክልሉ ኮምኒኬሽን መሥሪያ ቤት በኩል ተነግሯል። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ  ለክልሉ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እንዳሉትም፥ ማናቸውም በእነዚህ ወንጀሎች የተሳተፈ አካል በቁጥጥር ስር ይውላል። «ርምጃው ወደ ፈለገ አቅጣጫ ቢያመራም አጠናክረን እንቀጥላለን። ወደ መንግሥት መዋቅር ያምራ፣ ወደ ፀጥታው ኃይል ይሂድ፣ ወደ ባለሃብቶች ያቅና ወደፈለገ አቅጣጫ ይሂድ እስከ መጨረሻ እንሄዳለን» ሲሉ ጀነራሉ ገልፀዋል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ወንጀለኞችን ማደን ጀምሬያለሁ ቢልም፥ እስካሁን የተያዙ እነማን መሆናቸውን በተመለከተ የገለፀው ነገር የለም።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW