ትግራይ ክልል የሴቶችን ጥቃት የሚመለከቱ ዳኞች ላይ የሚደርስ ጫናና ማስፈራሪያ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 2 2017
በትግራይ ክልል ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት እና የግድያ ወንጀሎች በሚዳኙ ዳኞች ላይ ጫናዎችና ማስፈራርያ እየደረሰ ነው ሲል የትግራይ ክልል ዳኞች ማኅበር አስታወቀ ። የማኅበሩ ፕሬዝደንት አቶ ዳዊት ኃይለሥላሴ በዳኞች ላይ ማስፈራሪያዎች እየደረሱ ነው ሲሉ ለዶቼቬለ ገልፀዋል ። እየደረሱ ባሉ ጫናዎች እና ምቹ ባልሆኑ ሁኔታዎች ምክንያት ከ138 በላይ ዳኞች ከሥራ መልቀቃቸውንም ማኅበበሩ ጨምሮ ዐሳውቋል ።
ከትግራይ ክልል የዳኞች ማኅበር የወጣ መግለጫ እንደሚያመለክተው፥ በነፃነት ሥራቸውን መከወን በሚገባቸው ዳኞች ላይ ጣልቃ ገብነት እና ጫና ማድረግ የቆየ እንኳን ቢሆን ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን በከፋ ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ይገልፃል። እንደ ማሕበሩ ገለፃ በትግራይ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በሴቶች ላይ የፆታ ጥቃት እና ግድያ ወንጀል ተበራክቷል፣ በነዚህ ጉዳዮችም ፍርድቤቶች ብይን እየሰጡ ይገኛሉ ይላል። እነዚህን ክሶች በሚያዩ ዳኞች ላይ ከፍርድ በኃላ ይሁን በማጣራት ሂደት በተለያየ መንገድ ጫናዎች እየደረሱ መሆኑ የትግራይ ዳኞች ማሕበር አሳውቋል።
ይህ ጫና ደግሞ ዳኞች ሥራቸውን በነፃነት እንዳይሠሩ የሚያደርግ እና ከዚህ በዘለለ ደግሞ ድህንነታቸው አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ የጠየቀው የዳኞች ማሕበሩ ይህ ጫናና የድህንነት ስጋት የሚመለከታቸው አካላት አጢነው አስቸኳይ መፍትሔ የማይሰጡ ከሆነ ግን እነዚህ ከባድ የፆታ ጥቃት እና ግድያ ወንጀሎች የሚዳኙ ዳኞች ለድህንነታቸው በመስጋት አንሠራም የሚሉበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ያወሳል። የትግራይ ክልልዳኞች ማሕበር ፕሬዝደንት አቶ ዳዊት ኃይለስላሴ እንደሚሉት ከከሳሽ እና ተከሻሽ ወገን ዳኛች ላይ የሚደርስ ማስፈራሪያ እና ወከባ ባለበት ሕግ የሚፈቅደው ጥበቃ እንኳን ለዳኛ እየተደረገ አይደለም ይላሉ።
በዳኝነት ላይ ከመንግስት መስርያቤቶች ጭምር ጫና እየተፈጠረ መሆኑ የሚገልፀው የትግራይ ዳኞች ማሕበር፥ የትግራይ ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ባለፈው መጋቢት 25 ቀን፣ 2017 ዓመተምህረት ያወጡት የተባለ የፍርድቤት ውሳኔ በደፈናው የሚያጣጥል መግለጫ በማንሳት ሊታረም ይገባል ብሏል። በፍርድቤት ውሳኔ ላይ ቅሬታ ካለም በሕግ መሰረት ይግባኝ ማለት እንደሚቻልም ጠቀሟል። ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ዳኞች ማሕበር ፕሬዝደንት አቶ ዳዊት ኃይለስላሴ የዳኞች ደሞዝና ጥቅማጥቅም ለማሻሻል እንዲሁም አመቺ የስራ ሁኔታ እንዲኖር ለማድረግ ባለፈው ዓመት በክልሉ አስተዳደር ቃል ተገብቶ የነበረ ቢሆንም፥ እስካሁን አለፈፀሙ እና በዚህም በመቶዎች የሚቆጠሩ ዳኞች ስራ እየለቀቁ መሆኑ ያነሳሉ። ይህም በፍትህ ስርዓቱ የራሱ አሉታዊ ጫና እንዳለው ጠቁመዋል።
የትግራይ ዳኞች ማሕበር ጨምሮም የተጠቀሱ እና ሌሎች በርካታ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተቋቁመው ሥራቸውን እየከወኑ የሚገኙ በትግራይ የሚገኙ ዳኞች በፌደራል ደረጃ እና በሌሎች ክልሎች እየተተገበረ ያለው የዳኞች ደሞዝ እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ሊረጋገጥላቸው እንደሚገባም አሳስቧል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሠ