1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትግራይ ዉስጥ በኤርትራ ወታደሮች ስለተፈፀመ ግድያ የዓይን እማኝ መረጃ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 5 2015

የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)የሰላም ስምምነት ከመፈራረማቸው ከሳምንት በፊት የኤርትራ ወታደሮች አድዋ አካባቢ በምትገኘው በማርያም ሸዊቶ መንደር በትንሹ 300 ሰዎች መገደላቸዉን አንዲት የመንደርዋ ነዋሪ ተናገሩ። ወይዘሮዋ የ 70 ዓመቱ ባለቤታቸዉና የ28 ዓመቱ ልጃቸዉ በኤርትራ ወታደሮች ተገድለዉባቸዋል።

Äthiopien Tigray nach Massaker und Krieg
ባለቤታቸው እና ልጃቸው የተገደሉባቸው እናት ምስል privat

91 የግፍ ጥቃት ከደረሰባቸው መካከል 12 ሴቶች፤ 10 ደግሞ የሃይማኖት አባቶች ናቸዉ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)የሰላም ስምምነት ከመፈራረማቸው ከሳምንት በፊት የኤርትራ ወታደሮች አድዋ አካባቢ በምትገኘው በማርያም ሸዊቶ መንደር  በትንሹ 300 ሰዎች መገደላቸዉን አንዲት የመንደርዋ ነዋሪ ተናገሩ። በዚች ትንሽ መንደር የሚኖሩት የ63 ዓመቷ አዛውንት  ወ/ሮ አብረኸት  ሀጎስ በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ እንዲሁም በቤተሰባቸው ላይ ስለደረሰባቸው  ጥቃት ለዶቼ ቬሌ የእንሊዘኛ ክፍል በምስል በተደገፈ ማስረጃ ተናግረዋል ።
በ2012 ዓ.ም ጥቅምት ወር መጨረሻ ቀናት የኤርትራ ወታደሮች አዛዉንቷ ወ/ሮ አብረኸት ሃጎስ  ከአድዋ ከተማ ወጣ ብሎ የሚኖርባት መንደርን እንደተቆጣጠሩ እና ሰዎች እየተገደሉ በወሬ ደረጃ እንደሰሙ መኖርያ ቤታቸዉን   ለቀው ለመሸሽ ከቤተሰባቸው ጋር ቢያስቡም በወቅቱ መሸሸጊያ ቦታ ባለማግኘታቸዉ ምሽት ላይ ከመኖሪያቸው ወጣ ብሎ ባለ ቦታ ተሸሸጉ። እረፋድ ላይ ግን ይላሉ የ 63 ዓመት እድሜ ባለፀጋዋ ወ/ሮ አብረኸት «የቤት ውስጥ የነበሩት እንስሶቻችን ያልተለመደ ድምጽ ማሰማት ጀመሩ።  በዚህ ግዜ የ 70 ዓመቱ ባለቤታቸዉ እና የ28 ዓመቱ ጎልማሳ ልጄ ምን እንደተፈጠረ ለማየት ወደ መኖርያ ቤታችን ሄዱ። በዚህ ግዜ ነበር በኤርትራ ወታደሮች እጅ ውስጥ ወድቀዉ ሁለቱም የተገደሉት። የመኖርያ ቤቱ ግድግዳ በአምስት ወይንም ስድስት ጥይት ተበሳስቷል።  ልጄ ቤት ዉስጥ ተደብቆ ከሞት ለማምለጥ ከወታደሮቹ ለመሸሸግ ሞክሮ ነበር። ወ/ሮ አብረኸት እና ሴት ልጃቸዉ ከተሸሸጉበት ወጥተዉ መኖርያ ቤታቸዉ ሲደርሱ ባለቤታቸዉ እና ወንዱ ልጃቸዉ በደም ተነክረዉ ወድቀዉ አገኝዋቸዉ።  
 
 «ውይ !ብዬ ሴት ልጄን  አባትሽ ሞቱ አልኩ፤ ከዛ አንስተን ወደ ቤት አስገብተን አየት ስናደርግ ልጄም ጭምር እዛው ጥቅልል ብሏል። ያለ ምግብ፣ያለ ውሃ ከዛው ደከመኝ ቦኋላ  በቃ እዛው ጨርቅ አለበስናቸው። ከዛ ከብቶቹንም ቤት ውስጥ  ዘግተን እቤት ውስጥ ስናለቅስ ቆየን።»

ወ/ሮ አብረኸት ሀጎስ መኖርያ ቤታቸዉ በኤርትራ ወታደሮች በጥይት እንደተደበደበ ያሳያሉምስል privat

የወይዘሮዋ ባለቤት ቄስ ናቸዉ። ትዳር ለመያዝ ታጭቶ የነበረዉ  የ28 ዓመቱ ልጃቸው ግደይ በርይሁ ሊሰረግ የቀሩት ቀናቶች እንደነበሩ እናቱ ወ/ሮ  አብረኸት ተናግረዋል። አስተዋይ እና ታታሪ ልጅ ነበር ይላሉ በሃዘን። ወሮ አብረኸት ከሴት ልጃቸው ጋር በመኖርያ ቤታቸዉ ለአራት ቀናት ከባለቤታቸዉ እና ከልጃቸዉ አስክሬን ጎን  ከተቀመጡ በኃላ ግብአተ መሬታቸውን በቤተክርስቲያን ለማድረግ ወደ አቅርያብያ ቤተ ክርስትያን ቢሄዱም የኤርትራ ወታደሮች እንደከለከዋቸው ተናግረዋል።

«የኤርትራ ወታደሮች የሻብያ ከፍተኛ ባለስልጣንን አገኘሁ ቤተክርስቲያን ውስጥ አገነሁ ከዛ በቤተክርስትያን ቀብር የለም እዝያዉ ቅበሪ አይፈቀድም አሉኝ  እናንተ አደላችሁም የገደላችሁት?  በቃ እዛው ቤት ዉስጥ ቅበሪያቸዉ አለኝ።``

የ63 ዓመቷ አዛውንት  ወ/ሮ አብረኸት፤ ባለቤታቸዉን እና ልጃቸዉን የቀበሩት በጓሯቸዉ ነበርምስል privat


 ከዛም ወ/ሮ አብረኸት እና ባለቤታቸውን እና ወንዱ ልጃቸዉን ከመኖርያ ቤታቸዉ ጓሮ ቀበሩ። ከሁለት ወር በኋላ ወይዘሮዋ የባለቤታቸዉን እና የልጃቸዉን አስክሬን ከጓሮዋ አስወጥተው በቤተክርስቲያን ስርዓተ ስርዓተ ቀብራቸው ን አስፈጽመዋል ። ወ/ሮ አብረኸት ሴት ልጃቸዉ ከዚህ ሁሉ አስከፊ ሁኔታ በኋላ የአይምሮ ጭንቀት ዉስጥ እንዳትገባ ስጋት ይዟቸዋል። እሳቸዉም ቢሆን ከዚa ጊዜ ወዲህ ሰዉነታቸዉ እጅግ እየመነመነ መምጣቱን ተናግረዋል።
ለአንድ ሳምንት በዘለቀው እልቂት ክፉኛ ከተጎዱ መንደሮች መካከል አድዋ አቅራብያ የምትገኘዉ ማሪያም ሸዊቶ መንደር አንዷ ነች፤ ስትል ለዶቼ ቬሌ የተናገረችው የማህበራዊ ጉዳይ ባለሙያዋ አፀደ አባይ በመንደሩ የተጎጂዎችን ስም፣ ቀን እና ሞት ምክንያት፣ ከዘመዶቻቸው ፎቶ በመሰብሰብ፣ በህይወት የተረፉ እና የዓይን እማኞችን በማነጋገር መረጃ ሰንጠረዥ አዘጋጅታለች 

  «91 ጥቃት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል 12 ሴቶች ናቸው 10 ደግሞ የሃይማኖት አባቶች ናቸው ። በእድሜ ክልል ከፋፍለን ስንመለከተው ደግሞ ከ2 ዓመት ጀምሮ  እስከ 92 እድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው » 

የማህበራዊ ጉዳይ ባለሙያዋ አፀደ አባይ የሰበሰበችዉ ማስረጃምስል privat

አፀደ አባይ የሰበሰበችው ማስረጃ አንድ ቀን ለተጎጂዎች ፍትህ ለመስጠት ይረዳል የሚል ተስፋ እንዳላት እና ግድያዎቹ ዘግናኝ መሆናቸዉን ለዶቼ ቬሌ ተናግራለች። 

  የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)  መካከል ለሁለት ዓመት በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት በግምት 600 ሺህ ሰዎች ተገድለዋል፤ በሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል። በእርስ በርስ ጦርነቱ ወቅት የኤርትራ ጦር ወደ ትግራይ ክልል ጥሶ በመግባት የኢትዮጵያ መንግስን በጦርነቱ ሲደግፍ መቆየቱ ይታወቃል።  የደቡብ አፍሪቃው የሰላም ስምምነት ያልተካተተችዉ ኤርትራ ጦሯ ከትግራይ ክልል አሁንም ባለመዉጣቱ ለተፈረመው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት ትልቅ ፈተና ተደርጎ ይወሰዳል።

ማኅሌት ፋሲል 

አዜብ ታደሰ 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW