1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
የሕግ የበላይነትአፍሪቃ

ትግራይ ውስጥ ለተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ተጠየቀ

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 10 2017

በትግራይ በጦርነቱ ወቅት ለተፈፀሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እንዲሰራ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ገለፁ። «የትግራይ ጀኖሳይድ አጣሪ ኮምሽን» የተባለ ተቋም ባዘጋጀው መድረክ ፥ በጦርነቱ ወቅት የተፈፀሙ ወንጀሎች የሚያመለክቱ በርካታ መረጃዎች ማሰሰቡ አስታውቋል።

መቀለ ከተማ
መቀለ ከተማ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Million Hailessilassie/DW

ትግራይ ውስጥ ለተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ተጠየቀ

This browser does not support the audio element.

በዋነኝነት በትግራይ ጦርነት ወቅት የተፈፀሙ የፆታ ጥቃቶች፣ ሰብአዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ወንጀሎችን ለማጣራት እንዲሁም ተቀባይነት ያለው መረጃ ለመሰነድ በሚል ዓላማ፥ ግንቦት 2014 ዓ.ም. በአዋጅ የተመሰረተው የትግራይ ጀኖሳይድ አጣሪ ኮምሽን ትናንት በመቐለ ባዘጋጀው መድረክ ንግግር ያደረጉት የአጣሪ ኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ የማነ ዘርአይ እንዳሉት ባለፊት ዓመታት በተደረገ እንቅስቃሴ በርካታ በትግራይ የተፈፀሙ ወንጀሎች የሚያመለክቱ ሰነዶች ተመዝግበዋል። ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ እንዲሁም ታሪክ ለመሰነድ ታስቦ የሚደረግ ይህ ስራ፥ በርካታ ፈተናዎች እየገጠሙት እንዳለም የትግራይ ጀኖሳይድ አጣሪ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ የማነ ዘርአይ ገልፀዋል።

የማነ ዘርአይ «በአስር ሺህዎች የሚቆጠር የመሰረተ ልማት ውድመትእና ከ480 የጀምላ መቃብሮች በኮሚሽናችን ተሰንደው ይገኛሉ። እነዚህ የተመዘገቡ እና ገና ያልተመዘገቡ ጉዳቶች በቁሳዊ መልክ ተጠብቀው ካልቆዩ፥ የሚፈለገው ዘላቂ ፍትህ ይሁን የትግራይ ታሪክ አካል አድርጎ ለትውልዶች ለማስተላለፍ ክፍተት ይገጥመናል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ያደረግናቸው ውሱን ጥረቶች የሚፈለገው ውጤት ስላላስገኙ በርካታ ቁሳዊ መረጃዎች በተለይም ጅምላ መቃብሮች ትላቅ አደጋ ላይ ናቸው» ብለዋል።

የትግራይ ጀኖሳይድ አጣሪ ኮምሽን የተፈፀሙ ወንጀሎች በማጣራት፣ ተጨባጭ መረጃዎች በመሰብሰብ፣ ማስረጃዎች በማጠናቀር ረገድ በርካታ ተግባራት መፈፀሙ ያነሱት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጀነራል ታደሰ ወረደ በበኩላቸው፥ ይህ መሰረት አድርጎ ፍትህ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። 

ፕሬዝደንቱ «በመጀመርያ በሕዝብ፣ ቤተሰብ ይሁን ግለሰብ ላይ የደረሰ ጥቃት በፍትህ እና ተጠያቂነት መቋጫ ማግኘት እንዲችል የሚደረገው ጥረት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ በርካታ እንቅፋቶች ይገጥሙታል። ይሁንና ተበዳይ ሕዝብ፣ ቤተሰብ እና ግለሰብ ፍትህ ሊያገኝ ለዚህ ኮምሽን አደራ ሰጥቶት ያለ ስለሆነ ፍትህ ማረጋገጥ የግድ ይሆናል» ሲሉ ተናግረዋል።

ፍትህ ከማረጋገጥ እና ወንጀለኞችን ተጠያቂ ከማድረግ በተጨማሪ የተፈፀመውን ድርጊት በዘላቂነት የሚያስታውሱ ቤተመዘክር የመሳሰሉ ሕያው ምልክቶች መገንባት እንደሚያስፈልግ ፕሬዝደንቱ ጨምረው ገልፀዋል። 

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ «ያለፈው ጥፋት አልፎ ግን ደግሞ ለትውልድም ትምህርት ሊሆን ስለሚያስፈልግ፣ በአንድ ትውልድ ላይ የተፈፀመው ይህ ወንጀል እንዳይደገም እንዲሁም እንዳይረሳ ትምህርት መወሰድ መቻል አለበት። ይህ ትልቅ ሥራ ነው። በትምህርት ስርዓት በማካተት ሕጻናት ጀምሮ እንዲያውቁት ከማድረግ በተጨማሪ ህያው የሆኑ ምስክሮች ማስቀመጥ ያስፈልጋሉ። ጀኖሳይድ የተፈፀመባቸው ሁሉም ሃገራት ስንመለከት ቋሚ እና ወንጀሉን የሚያመለክቱ ህያው ምስክሮች ይቀመጣሉ» ብለዋል።

በትግራዩ ጦርነት ወቅት በበርካታ ሴቶች ላይ ፆታ መሰረት ያደረገ ጥቃት መድረሱ፣ በሲቪሎች ላይ ግድያ፣ እስር፣ ማሰቃየት ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎች መፈፀማቸው እንዲሁም ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና የጦር ወንጀል ድርጊቶች መታየታቸው ዓለምአቀፍ የመብት ተሟጓቾች ተቋማት ሲገልፁ መቆየታቸው ይታወሳል። ለእነዚህ ወንጀሎች ተጠያቂነት አለመረጋገጡም ይገለፃል።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW