1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 ቶማስ ሳንካራ፤ ቀጥተኛዉ አብዮተኛ

እሑድ፣ ጥር 6 2010

የቀድሞዉ የቡርኪናፋሶ አብዮታዊ መሪ ሻምበል ቶማስ ሳንካራ ሥልጣን ላይ የቆዩት ለዓራት ዓመታት ብቻ ነዉ።ሥም ዝናቸዉ ግን ከሐገራቸዉ፤ ከዘመናቸዉም አልፎ እስካሁን ድረስ በመላዉ አፍሪቃ እንደናኘ ነዉ።

Burkina Faso Päsident Thomas Sankara
ምስል picture-alliance/dpa/AFP

«የአፍሪቃ ቼ ጉቬራ» ተብለዉ የሚደነቁት ሳንካራ ለድሆች የሚቆረቆሩ፤እኩልነትን የሚያቀነቅኑ፤ ቅኝ ገዢዎችን እና ጨቋኞችን አጥብቀዉ የሚቃወሙ፤ ሕዝብን ለመብቱ እንዲታገል የሚያነሳሱ አብዮተኛ ነበሩ። በተገደሉ በ30 ዓመቱ ዘንድሮ ለተወዳጁ መሪ መታሰቢያ ተቋም ለመመሥረት ገንዘብ እየተዋጣ ነዉ። 
ሞተር ብስክሌት ጋላቢነታቸዉን፤ ወይም ጊታር ተጫዋችነታቸዉን ብቻ የሚያዉቅ «ቀበጥ »ይላቸዉ ይሆናል።መለሎ ሸንቃጣ ቁመናቸዉ ከመልከመልካም ገፅታቸዉ ጋር  ተዳምሮ የኮረዶችን ልብ በቀላሉ ማማለሉ አይቀርም።ሁሉም ነበር መባል ከጀመረ 30 ዓመት ማለፉ ነዉ ቁጭቱ።ቶማስ ኢሲዶሬ ኖኤል ሳንካራ።
በ1972 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሐገራቸዉ አፐር ቮልታ ከማሊ ጋር በገጠመችዉ ጦርነት ቆራጥ ወታደር፤ ጀግና የጦር መሪ መሆናቸዉን አስመስክረዋል።ሰዉዬዉ ሁሉንም ናቸዉ። ከሁሉም በላይ ቆራጥ አብዮተኛ ናቸዉ።በጀግንነት የተዋጉበትን ጦርነት ኋላ ጭቁኖችን ያጋደለ «ትርጉም የለሽ» በማለት አወገዙት።
ነሐሴ 1983 ሌሎች ጓዶቻቸዉን መርተዉ የአፐር ቮልታን የመሪነት ሥልጣን ተቆጣጠሩ።ያኔ ገና የሰላሳ ዓመት ወጣት ነበሩ።ሻምበል።«ለመብቱ የማይታገል ባሪያ ሊታዘንለት አይገባም» ዓይነት ብሒል ነበራቸዉ።                          
«ማመፅ ለማይፈልግ ባሪያ በሚደርስበት በደል ልናዝንለት አይገባም።አንድ ቀን ነፃ እለቅሐለሁ  የሚለዉን የጌታዉን ከንቱ ተስፋ አምኖ የሚቀበል ባሪያ ለሚደርስበት ሁሉ ኃላፊነቱን እራሱ መዉሰድ አለበት።ነፃ የሚያወጣዉ ትግል ብቻ ነዉ።»
የፈረንሳይ ቅኝ ገዢዎች አፐር ቮልታ ያሏትን ሐገር ስም ሳንካራ ለወጡት።ቡርኪና ፋሶ ብለዉ።የቀጥተኞች ወይም የትክክለኞች ሐገር እንደማለት ነዉ።ደሐዉ ሕዝባቸዉ በምግብ ራሱን እንዲችል የአስተራረስ ዜዴዉን እንዲያሻሻል አደረጉ።ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ፤ሕዝቡም የሐገር ዉስጥ ምርትን እንዲጠቀም አበረታቱ።ጓድ ፕሬዝደንት ትምሕርት እንዲስፋፋ፤ የጤና አገልግሎት እንዲዳረስ ብዙ ባከኑ።
«የቶማስን ራዕይ፤ አላማ እና ዕቅድ በተለይ ደኸዉ ሕዝብ በጣም ተረድቶት ነበር» ይላሉ ያኔ በሊቢያ የቡርኪና ፋሶ አምባሳደር የነበሩት ሞሱቢላ ሳንካራ።                   
«ቶማስ በነዚሕ ፍትሕ እና እዉቅና በሚፈልጉት ድሆች ዘንድ ተቀባይነት ነበረዉ።እኒያ ከድሕነታቸዉ በስተቀር የራሳቸዉ ስብዕና ባላቸዉ፤ የማሕበረሰባቸዉ አባል ወይም የሐገራቸዉ ዜጋ በመሆናቸዉ በሚኮሩት ዘንድ ተወዳጅ ነበር።እሱን ልዩ የሚያደርገዉ ፅናቱ ነዉ።ለሐገሩና ለሕዝቡ ለመስራት ያለዉ ፍላጎት ነዉ።»
ወጣቱ መሪ ከዘመናቸዉ የቀደሙ ነበሩ።በድሆቹ መወደዳቸዉ፤ በተለይ ማርክሲዝምን ማቀንቀናቸዉ እንደ ወዳጆቻቸዉ ሁሉ ፓሪስ እና ዋሽግተንን የመሳሰሉ ጠላቶቻቸዉም ጠንቅቀዉ ያዉቁት ነበር።ሳንካራ በተለይ ያኔ የአፍሪቃ እና የአረብን ሕዝብ ለአብዮት ከሚነቀንቁት ከኮሎኔል ሙዓመር ጋዳፊ ጋር መወዳጀታቸዉ ደግሞ ጠላቶቻቸዉን  ለ«ይቺ ባቄላ--» ዓይነት ሴራ አሳደመ።
ሐምሌ 1987 አዲስ አበባ ላይ ተሰይሞ በነበረዉ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር የብሬተን ዉድስ ተቋማት የሚባሉትን የዓለም ባንክ እና የዓለም ገንዘብ ድርጅትን አወገዙ። ተቋማቱ ብድር እያሉ አፍሪቃን መበዝበዛቸዉን አጋለጡ።የሳንካራ ዉግዘት እና ማሳጣት ምዕራባዉያንን ብቻ ሳይሆን በምዕራባዉያን ምዳና ድጋፍ ሥልጣን በተቆናጠጡ የአፍሪቃ መሪዎች ዘንድ ጥርስ አስነከሰባቸዉ።
ምዕራብም፤ አፍሪቃም ባንድ አሴረዉ፤ እንደ አብዮተኛ አብረዉ የቆሙ፤ እንደወታደር የተማማሉ ጓዶቻቸዉን ጃስ አሉባቸዉ።አስገደሏቸዉም።ብዙዎች እንደሚጠረጥሩት ካስገዳዮቹ አንዱ የሳንካራ የቅርብ ጓድ፤ ብሌዝ ኮምፓዎሬ ናቸዉ።የሳንካራ የሕወት ታሪክ  ፀሐፊ ብርኖ ጃፍሬ አንዱ ናቸዉ።
«በዚሕ ግድያ ይጠረጠራሉ።ተሳትፏቸዉ ግልፅ ነዉ።ሳንካራን የገደሉት ሰዎች በጂልበርት ዲንዴሬ የሚታዘዙ ናቸዉ።ዲንድሬ ደግሞ የደሕንነት ኃላፊ እና የብሌስ ኮምፓወሬ ቀኝ እጅ የነበሩ ሰዉ ናቸዉ።»
ኮምፓወሬ፤ ከሳንካራ መገደል በኃላ የቀድሞ ጓዳቸዉን ሥልጣን ይዘዉ ቡርኪናፋሶን  ለ27 ዓመት ገዝተዋል።ሳንካራ ከተገደሉ ከብዙ ዓመታት በኋላም ክብር ዝናቸዉ በመላዉ አፍሪቃ ሲናኝ ኮምፓወሬ ሕዝብ አይንሕ ላፈር ብሏቸዉ ክብር፤ ሥልጣናቸዉን ጥለዉ ከፈረጠጡ ሰወስት ዓመት አለፋቸዉ።
ክሌር ኮስትማን/ነጋሽ መሀመድ
ሂሩት መለሰ

ምስል Comic Republic

(Back-anno: ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አንድ አካል ነው።)
(Back-anno: This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.)

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW