1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቻይና እና የዓለም የኦሊምፒክ ጨዋታ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 2 1999

ቻይና ውስጥ ቁጥሩ «ስምንት» እንደ ጥሩ ዕድል የሚያስገኝ ቁጥር ይታያል።

በዚህም የተነሳ እአአ በ2008 ዓም የሚደረገው የዓለም የኦሊምፒክ ጨዋታ በቻይና መዲና ቤይዢንግ ውስጥ በስምንተኛው ወር፡ በስምንተኛው ቀን ይከፈታል። ይሁን እንጂ፡ የኦሊምፒኩ ጨዋታ ለሁሉም ቻይናዊ ጥሩ ዕድልና የሚያስገኝ አልሆነም። አንድ ዠኔቭ ስዊትዘርላንድ የሚገኝ በምህጻሩ ኮህር የሚሰኘው ጸረ ክትትልና ለመኖሪያ ቦታ መብት የሚሟገተው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባለፉት ሶስት ዓመታት የዓለም ኦሊምፒክ ጨዋታን የመሳሰሉና የግዳጁን ሰፈራ ያስከተሉ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ዝግጅቶችን መርምሮ አንድ ዘገባ አውጥቶዋል። የዘገባው ውጤት በሚቀጥለው ዓመት በቤይዢንግ ለሚደረገው የኦሊምፒክ ጨዋታ እጅግ ጎጂ ሆኖ ነው የተገኘው።

በጥናቱ ውጤት መሰረት፡ ባለፉት ሀያ ዓመታት ከኦሊምፒክ ጨዋታ ጋር በተያያዘ ከሁለት ሚልዮን የሚበልጥ ህዝብ ከሚኖርበት አካባቢ በግድ ካለፈቃዱ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰፍር ተደርጓል። ለምሳሌ በደቡብ ኮርያ መዲና ሶል እአአ በ 1988 ዓም በተካሄደበት ጊዜ ሰባት መቶ ሀያ ሺህ ሰዎች ነበሩ በግዳጁ ሰፈራ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉት። የኮህር ዋና ስራ አስኪያጅ ዣን ዲው ፕሌሲስ እንደሚገምቱት፡ የዚህን እጥፍ የሚሆን ሰው በ 2008 የቤይዢንጉ ጨዋታ ዝግጅት በግዳጅ በሌላ ቦታ እንዲሰፍር መገደዱ አይቀርም።
« እስካሁን ድረስ ከአንድ ሚልዮን የሚበልጥ ህዝብ፡ ጨዋታው እስኪጀመር ድረስ ደግሞ አንድ ሚልዮን ተኩል ቻይናውያን ወደሌላ እንዲሰፍር ተደርጓል፤ ይደረጋል። »

ቻይና ለኦሊምፒክ ጨዋታ ራስዋን የሀያ አንደኛው ምዕተ ዓመት ኃያል መንግስት አድርጋ ለማቅረብ ትፈልጋለች። በመሆኑም በሀገርዋ ግዙፍ የግንባታ ስራ በመካሄድ ላይ ይገኛል። የግዳጅ ሰፈራም የዚሁ ተግባር ውጤት ነው። አዘውትሮ እንደታየውም በሌላ ቦታ መስፈር የሚገደዱት ሰዎች የቀድሞ መኖሪያ ቤቶች ይደመሰሳሉ። የሚመለከተው ህዝብ ሳይጠየቅ፡ በቂ ጊዜና የገንዘብ ካሳ ሳይሰጠው፡ ካሳ ካገኘም የሚከፈለው ፈንዘብ እጅግ ንዑስ የሆነበትን አሰራር ዣን ዲው ፕሌሲስ ነቅፈዋል። ህዝብን ወደ ድህነት የሚያመራው የግዳጁ ሰፈራ ግን፡ እንደ ዣን ዲው ፕሌሲስ ገለጻ፡ ቻይና ውስጥ የሚካሄደው ግዙፍ ዝግጅት ሲኖር ብቻ አይደለም።
« ይህ የቻይና መንግስት እንደ ህጋዊ መሳሪያ የሚጠቀምበት አሰራር ነው። በተለይ ቤይዢንግ የኦሊምፒክ ጨዋታን እንድታስተናግድ ከተመረጠች ወዲህ የግዳጁ ሰፈራ በሚያሳስብ ደረጃ ከፍ ብሎዋል። በዚህም የተነሳ በጣም ሰግተናል። »

የቤይዢንግ የኦሊምፒክ ኮሚቴ እስካሁን በዚህ ወቀሳ አኳያ አንዳችም አስተያየት አልሰጠም። የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ግን የግዳጁ ሰፈራ አንድ ሚልዮን ተኩል ተነክቶዋል የተባለበትን ዘገባ የተጋነነ ስትል አስተባብላለች። ዣን ዲው ፕሌሲስ ግን የተጠቀሰው ቁጥጥር ትክክለኛ ነው። በተለይ፡ የግዳጁ ሰፈራ በኃይልና ጭቆና በታከለበት መንገድ መከናወኑን ነው ዣን ዲው ፕሌሲስ የገለጹት። የመኖሪያ አካባቢውን ለቆ በሌላ ቦታ እንዲሰፍር የሚሰጠውን ትዕዛዝ የማያከብር ሁሉ፡ የኮህር ዘገባ እንዳስታወቀው፡ የመታሰር ዕጣ ይገጥመዋል።

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW