ቻይና፧ ዳርፉርና የኪነ ጥበብ ሰዎች ተማጽኖ፧
ሐሙስ፣ የካቲት 6 2000በተለይ፧ ከሰሞኑ፧ እውቁ አሜሪካዊ የፊልም አዘጋጅ Steven Spielberg፧ ከቻይና የኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በማቋረጣቸው፧ መገናኛ ብዙኀን፧ ለዳርፉር እንደገና ዐቢይ ትኩረት መስጠት ይዘዋል። በዓለም ዙሪያ፧ በዳርፉር እንደሆነው ሁሉ፧ ሰብአዊ መብት የሚረገጥባቸው አካባቢዎች ጥቂቶች እንዳልሆኑ እየታወቀ፧ የኪነ ጥበብ ሰዎቹ፧ በአንድ ቦታ ላይ መረባረባቸው የሚያስገርም ነው።
እውቁ አሜሪካዊ የ Hollywood ፊልም አዘጋጅ፧ Steven Spielberg ነሐሴ 2 ቀን 2000 ዓ ም በቤይጂንግ የሚጀመረው የኦሊምፒክ እስፖርት ውድድር፧ በከፍተኛ ደረጃ አምሮና ደምቆ እንዲከፈት፧ ሲደመደምም ተመሳሳይ ድምቀት እንዲኖረው ለማድረግ፧ በኪነ ጠበባዊ አማካሪነት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፧ ራሳቸውን ከዚሁ የዝግጅት ሂደት ማግለላቸውን አስታውቀዋል። የሰጡት ምክንያት የኅሊና ሙግት ነው። እስፒልበርግ ከዚሁ ጋር በማያያዝ፧ ቻይና ወደፊት፧ ለሰላም የበለጠ አስተዋጽዖ እንደምታደርግ ያላቸውን ተስፋ አንጸባርቀዋል። ታዋቂው የሆንግ ኮንግ የቴሌቭዥን ሐተታ አቅራቢ ቺው ዠንሃይ፧ የእስፒልበርግ ተማጽኖ ያን ያህል ፋይዳ አይኖረውም ይላሉ።.........
«ቻይናውያን በጣም ኩሩዎች ናቸው። ቀጥተኛ የሆነ ተጽእኖም ሆነ ግፊት ሲያጋጥማቸው መንግሥትና ህዝቡ፧ የመከላከል አቋም ነው የሚይዙት።«
እስፒልበርግ፧ ከአማካሪነት ራሳቸውን ስላገለሉበት ሁኔታ፧ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚንስቴርም ሆነ ብሔራዊው የኦሊምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴ.፧ ገና ይፋ መልስ አልሰጡም። እርግጥ ነው፧ ከሁለት ሳምንት በፊት፧ ሱዳንን በተመለከተ፧ «ፖለቲካንና ኦሊምፒክን ማዛመድ ትክክል አይደለም« ሲል የቻይና መንግሥት ማውገዙ የሚታወስ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ሊው ዢያንቻዎም፧ በዛሬው ዕለት፧ ተመሳሳይ መግለጫ ነው የሰጡት። ከዚህ አንጻር፧ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች፧ የእስፒልበርግን እርምጃ፧ ትክክል ነው በማለት ነው የደገፉት። ስለዳርፉር ከሚቆረቆሩት መካከል የፊልም ተዋናዪት ሚያ ፋሮው በበኩሏ እንዲህ ብላለች።
«ዘር የማጥፋት ወንጀል ነው የተፈጸመው። እንደሚመስለኝ፧ አምስት ዓመታት አንዳች ነገር አለማድረጋችን፧ ከሰብአዊ ፍጡር ባህርይ አንጻር ይህ ተቀባይነት የሌለው ነው።«
ቻይና በአፍሪቃው ክፍለ ዓለም፧ ለጥቅሟ እንጂ ለሰብአዊ መብት መጠበቅ አንዳች ደንታ የላትም የሚሉ አሉ። የቻይና አዲስ የአፍሪቃ ፖለቲካ ከምን የመነጨ ነው? በላይፕዚኽ የአፍሪቃ ጉዳይ ተመራማሪ ፕሮፌሰር Asche.....
«ቻይና በአፍሪቃ የምትከተለው ሥልታዊ መርኅ፧ ሥር የሰደደ አይደለም። በአፍሪቃ ለመሠማራት የገፋፋት ዋናው ምክንያት የኃይል ምንጭና ጥሬ አላባ የማግኘት ጉጉት ነው። ሌላው፧ በአፍሪቃ የሸቀጥ ማራገፊያ ገበያ የማግኘት ፍላጎቷ ነው የገፋፋት።«
ቺው ዠንሃይ፧ በሚመጡት ወራት፧ ብዙ ሳንኮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ነው የጠቆሙት......
«የኦሊምፒክ እስፖርት እስኪጀመር፧ በሚመጡት ስድስት ወራት፧ ብዙ ችግሮች ያጋጥማሉ። ቻይና ያለመታወክ ነው ኦሊምፒክን ማስተናገድ የምትሻው። በተለይ ጸጥታው አስተማማኝ እንዲሆንላት ትፈልጋለች። የተሻለ ገጽ እንዳላት ማሳያ መስታውት አድርጋም ልትጠቅምበት ትፈልጋለች። አስተማማኝና በሚገባ የተደራጀ የኦሊምፒክ ውድድር ማዘጋጀት የሚያስችግር አደለም። ነገር ግን ቻይናን ግልጽ ሀገር አድርጎ ለማቅረብ መቃጣት አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።«
ምዕራባውያን ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎች በተለይ የሃሊውድ ፊልም ተዋንያን ለዳርፉር የሚያሳዩት መቆርቆር ከልብ እስከሆነ ድረስ፧ ይበል የሚያሰኝ ነው። የዳርፉር ውዝግብ በእርግጥ ዐቢይ ግምት ተሰጥቶት በተቻለ ፍጥነት ዘላቂ መፍትኄ ሊያገኝ የሚገባው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፧ በዓለማችን፧ በዐራቱም ማዕዘን፧ ብዙ ዳርፉሮች መኖራቸውን ተገንዝበው ተዋንያኑ ቢረባረቡ ምንኛ ባስመሠገናቸው! የሰብአዊ መብት ረገጣ፧ በሱዳን ብቻ አይደለም የሚካሄደው። በተለያዩ ምክንያቶች እያሳበቡ፧ የሰውን ልጅ መብት የሚረግጡ፧ ቅጥፈት በተመላበት ምርጫ፧ በሥልጣን ለረጅም ጊዜ ተደላድሎ ለመኖር በማሰለሰል፧ ያልመረጣቸውን ህዝብ የሚያንገላቱ፧ የሚቃወቸውን፧ የሚያሳድዱ፧ የሚያሥሩ፧ የሚገድሉ፧ መንግሥታት አሉ። በቅርቡ በኬንያ የተፈጸመውን ሁኔታ ልብ ይሏል። በኬንያ ሰዎች፧ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቻው አሳዝኗቸው፧ የተፈናቀሉትንም ለማቋቋም ስንቶች ዓለም አቀፍ የኪነ ጥበብ ሰዎች ናቸው፧ የተረባረቡት??!