1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቻግኒ ከተማ ዉስጥ በተደረገ የተኩስ ልዉዉጥ ሰዎች መገደላቸዉ የቀሰቀሰዉ ዉዝግብ

ሐሙስ፣ ግንቦት 29 2016

በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የቻግኒ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በቀለ መኩሪያ የተፈጠረው ሁኔታ ከብሔርም ሆነ ከሐይማኖት አይገናኝም ብለዋል፡፡ በአካባቢው በዘረፋ ተሰማርተው የነበሩ አካላት በመንግስት የፀጥታ አካላት ላይ ተኩስ በመክፈታቸው እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰው በተኩስ ልውውጡ፣ ከመንግስት የፀጥታ አካላት---

በዞኑ አሁንም ታጣቂዎች ግድያ እገታ፣ ዘረፋና ጥቃት እንደሚያደርሱ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ይናገራሉ
በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ ዞን ከመንግሥት ኃይላት ጋር ይዋጉ የነበሩ አማፂ ኃይላት አምና ትጥቅ መፍታታቸዉ ተነግሮ ነበርምስል Awi zone communication office

ቻግኒ ከተማ ዉስጥ በተደረገ የተኩስ ልዉዉጥ ሰዎች መገደላቸዉ የቀሰቀሰዉ ዉዝግብ

This browser does not support the audio element.

ትናንት በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ቻግኒ ከተማ በነበረ የተኩስ ልውውጥ የ5 ሰዎች ህይዎት መጥፋቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ፣ ግጭቱ የተከሰተው “ዘራፊዎች” ካላቸው ኃይሎች ጋር መሆኑን መንግስት ሲገልፅ በአካባቢው ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ከማንነት ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ፡፡

በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አንድ የቻጊኒ ከተማ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ በስልክ እንደተናገሩት “በአገው ብሔራዊ ሸንጎ ስም በሚንቀሳቀሱና በዝርፊያና በማገት የተሰማሩ” ባሏቸው አካላትና በመንግስት ኃይሎች መካከል በነበረ ውጊያ ሰዎች ተገድለዋል፡፡

“... የአገው ሸንጎ የሚለውን ባይወክሉም፣ የታጠቁ ኃይሎች አሉ፣ በድርጅቱ ስም የሚንቀሳቀሱ፣ ዝርፊያና የመሳሰለውን ነገር ነው የሚያደርጉ፣ ከተማ ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ፣ በህገ ወጥ የታጠቁ ናቸው ይባላል፣ መኪና እያስቆሙ ይዘርፋሉ፣ ሰው ያግታሉ፣ በዚያ ምክንያት ሰው በጣም ተማርሯል፣ መንግስትም የሚያደርገው ነገር ግራ ገብቶት ነበር፣ ... ትናንትና ቀን 8 ሰዓት አካባቢ ከተማ ውስጥ የታጠቁ 3 ሰዎች ከመንግስት የፀጥታ አካላት ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል፣ ከዚያ በኋላ ተመትተዋል፡፡” ነው ያሉት፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስና ድምፃቸው እንዲቀየር የፈለጉ ሌላ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ከአገው ብሔራዊ ሸንጎ ጋር ግንኙነት ያላቸው ያሏቸው አካላት በአካባቢው ህብረተሰብ ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ እንደነበር አመልክተው ከመንግስት የፀጥታ አካላት ጋር በነበረ የተኩስ ልውውጥ ሰላማዊ ሰዎች ጭምር ተገድለዋል ብለዋል፡፡

“ የነበረው ሁኔታ ከቻግኒ ወደ ወንበራ በሚወስደው መንገድ ተደራጅተው የሚዘርፉ ዘራፊዎች አሉ፣ እነኚህ ሰዎች መሳሪያ አውርዱ ተብለው ተጠይቀው ነበር፣ ግን ህዝቡን ሲያሰቃዩ የነበሩ፣ ይጠልፋሉ፣ ይዘርፋሉ፣ መሳሪያ ለሌሎች እያስታጠቁ ሲዘርፉ፣ ሲዘርፉ ነበር፣ የመንግስት የፀጥታ አካል ያለውን ኃይል ተጠቅሞ ውጊያ ገጠማቸው፣ ዘራፊ የተባሉትን ያቋቋሙ አንዳንድ ሰዎች ሽፋን ለመስጠት መሳሪያ ይዘው ወጡ የመንግስት የፀጥታ አካላት እርምጃ ወስደውባቸዋል፡፡”

የአገው ለፍትሕና ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር አዲሱ መኮንን  ወንጀል የፈፀመ አካል መጠየቅ እንዳለበት እንደሚያምኑ ጠቁመው  የትናንትናውን ግጭት መንስኤ ባያውቁትም ሰዎቹ ግን የተገደሉት በማንነታቸው ብቻ ነው ሲሉ ገልጠዋል፡፡

“...አገው ናቸው እነኚህ ሰዎች፣ በማንነታቸው ምክንያት ነው የተገደሉት፣ ለፍቶ አዳሪ ባለሆቴል ነጋዴ ከሶስት ወንድሞቹና ከሆቴሉ ገንዘብ ያዥ ጋር ነው የተገደሉት፣ ችግር ያለበትና ከህግ አግባብ ውጪ የሚንቀሳቀስ ኃይል ካለ መንግስት የራሱን መዋቅር ተጠቅሞ፣ ያንንም ቢሆን በመግደል አይደለም፣ በህጋዊ መልኩ ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ ነው፣ የመንግስት ኃላፊነትም ይህ ነው፣ የህግ የበላይነት መከበር አለበት፣ ይህንን እኔ አምናለሁ፣ ሰርዓት አልባ ዜግነትን አልፈቅድም፡፡” ብለዋል፡፡

የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ሊቀመንበር አቶ አላምረው ይርዳው በበኩላቸው ፓርቲያቸው የታጠቀ ኃይል እንደሌለው አስረድተዋል፣ ቢሮም በአማራ ክልል ውስጥ መክፈት እንዳልቻለም ተባግረዋል፡፡  ትናንት ግን በሁለት ወጣቶች መካከል የተጀመረው አልመግባባትን ተከትሎ የአገው ሸንጎ ደጋፊ የሆኑ ሰዎች መገደላቸውን ነው ያብራሩት፣ እንደ አቶ አላማረው ሟቾቹ የታጠቁ አልነበሩም፡፡

ከዚሕ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በመተከል ዞን የሚደረጉ ግጭቶች የሸሹ ነዋሪዎች ቻግኒ ከተማ ዉስጥ ሰፍረዋልምስል Maria Gerth-Niculescu/DW

“ እንኳን ትጥቅ ሊኖረን ቢሮም አማራ ክልል ውስጥ መክፈት አልቻልንም፣ የችግሩ መንስኤ ሁለት ወጣቶች “ቻግኒ የአማራ ነው”፣ አይደለም “ቻግኒ የአገው ነው” በሚል የተነሳ ነው፡፡ ነገሩ ከበረደ በኋላ አድማ በታኝ የተባለው የመንግስት ታጣቂ ኃይል ወደ ቻግኒ መጥቶ አንድን ወጣት ተኩሶ ሲገድል፣ “የአገውን ትግል ትደግፋለህ” የሚባል በከተማው ታዋቂ ሆቴል ያለው ሰው አለ፣ የዚህን ሰው ወንድም ነው የገደሉት፣ “ወድምህ ተገደለ” ተብሎ አስከሬን ለማንሳት ሲሄድ እሱንም ገደሉት፣ እስስካሁን 5 ሰዎች ተገድለዋል፤ ማቾቹ አንዳቸውም ትጥቅ የታጠቁ አይደሉም፡፡፡”

በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የቻግኒ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በቀለ መኩሪያ የተፈጠረው ሁኔታ ከብሔርም ሆነ ከሐይማኖት አይገናኝም ብለዋል፡፡ በአካባቢው  በዘረፋ ተሰማርተው የነበሩ አካላት በመንግስት የፀጥታ አካላት ላይ ተኩስ በመክፈታቸው እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰው በተኩስ ልውውጡ፣ ከመንግስት የፀጥታ አካላት በተቃራኒ ለተሰለፉ አካላት ሽፋን ሲሰጡ የነበሩ ሰዎችም እርማጃ እንደተወሰደባቸው ነው ያስረዱት፡፡

“ግጭቱ የብሔርም፣ የሐይማኖትም መልክ የለውም፣ በእኛ አካባቢ ሰው ማገት አለ፣ መኪና አስቁሞ መዝረፍ አለ፣ ይህን ወንጀል ለመከላከል በተደረገ እንቅስቃሴ ነው የትናንትነው ክስተት የተፈጠረው፣ “አገው ስለሆንን ነው”፣ “አገው ሸንጎ ስለሆንን ነው” የሚለው የፖለቲካ ንግድ እንጂ በማንነቱ ማንም ጥቃት አልደረሰበትም፣ እንግዲህ ውጊያ ነው፣ ተኩስ ተከፈተ፣ በዚህ የተኩስ ልውውጥ ከዘራፊ ቡድኑ ጋር በመደራጀት እያውቁም ሆነ ሳያውቁ በነበሩ ሰዎችና በፀጥታ ኃይሉ ላይ መልሰው ተኩስ በከፈቱ ኃሎች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በአማራ ክልል ከተደራጁት የብሔረሰብ አስተዳደሮች አንዱ ሲሆን በአብዛኘው ህዝቡ አገውኛ ተናጋሪ ነው፡፡

ዓለምነው መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW