1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ኃላፊነቱ የሁላችንም ነው» ማስተር አብነት ከበደ

ዓርብ፣ መጋቢት 1 2015

ማስተር አብነት ከበደ ሰሞኑን በተለይ ቦረና ውስጥ ከተከሰተው ድርቅ እና ርሀብ ጋር በተያያዘ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ በተደጋጋሚ ስሙ እየተነሳ ይገኛል። ወጣቱ ቦታው ድረስ በመሄድ ርዳታ ሲለግስ እና ሲያሰባስብ ተስተውሏል።

 Äthiopien _ Master Abnet Kebede
ምስል privat

«ኃላፊነቱ የሁላችንም ነው» ማስተር አብነት ከበደ

This browser does not support the audio element.

በማርሻል አርት ስፖርት ማስተር የሚለውን ማዕረግ ያገኘው አብነት ባለፉት ዓመታት ሞተር ሳይክል ላይ ሆኖ በሚያሳያቸው ትዕይንቶቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ይታወቃል። ይበልጥ በማህበራዊ መገናኛው ትኩረት ያገኘው ደግሞ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ቦረና ላይ የደረሰውን ድርቅ እና ርሃብ የረዳበት መንገድ ነው። « ረዥም ኪሎ ሜትር አቋርጬ ነው ቦረና ወገኖቻችንን ለመጀመሪያ ጊዜ ላገኛቸው የሄድኩት።  መጀመሪያ ላይ አንዲት እናት ተርበው እንደተቸገሩ ሶሻል ሚዲያ ላይ አየሁ። ደርሼ ቦታው ላይ ችግራቸውን ለመካፈል ያለውንም ነገር ቦታው ላይ ለመገኘት ወስኜ አቅሜ የፈቀደውን ማድረግ ጀመርኩ። ሌሎችም መልካም ሰዎች ተነሳሱ። » 
«በቁጥር ይህን ያህል ሰዎችን ረድተናል ለማለት ከባድ ነው » የሚለው አብነት በየወረዳዎች እና ቤት ለቤት እንደ ግለሰብ « የተላከውን አደራ»  እያደረሰ መሆኑን ይናገል። « ብዙ ሚሊዮን ብር ለቦረና ወገኖቻችን ውኃ እና የሚያስፈልጋቸውን ነገር ድጋፍ እያደረግን ነው። በ15 ቀናት ውስጥ ሶሻል ሚዲያን እና ቲክቶክን በመጠቀም አገር ውስጥም ከአገር ውጪም ያሉ ወገኖችን በማስተባበር እጅግ በጣም መልካም ነገር ሰርተናል።»  አብነት በቦረና ቆይታው በርካታ ትምህርት የሆኑት እንዲሁም የታዘባቸው እና ልቡ ውስጥ የቀሩ ገጠመኞች አሉ። ከነዚህም መካከል አንዱን ሲገልፅ እንደዚህ አይነት ህይወት እያሳለፉ ለእነሱ ውኃ እንዲጠጡ ስንሰጣቸው እነሱ በክዳኑ ተከፋፍለው ይጠጣሉ። ለእንግዳ ግን ሀይላንዱን አንስተው ነው የሚሰጡት።» ይላል።

2013 ዓ ም ቦረና ውስጥ ውኃ ለመቅዳት የተሰለፉ ሰዎች ምስል Firaol Wako/PHD
ማስተር አብነት ከበደምስል privat

አብነት ነጋዴ እና ስፖርተኛ ነው።  ቦረና ላይ የሚያደርገው ድጋፍ ይበልጥ ከህዝብ ጋር አስተዋውቆት ይሆናል እንጂ እንደገለፀልን በተለይም ጎዳና ላይ ወድቀው የሚያገኛቸው እና የሰው እጅ የሚያዩ እናት እና አባትን መርዳት እንደሚያስቀድም ገልፆልናል። ማስተር አብነት በህይወቱ ብዙ ችግሮችን ማሳለፉ «የሰዎችን ህመም በቀላሉ እንድረዳ አድርጎኛል» ይላል።   « ዘርዝሬ አልጨርሰውም፤መንገድ ላይ ተርቤ አውቃለሁ፣ ሰው ሀገር ላይ ሄጄ የትራንስፖርት ብር አጥቼ በረንዳ ላይ አድሬ አውቃለሁ። ብር አጥቼ ከአንገቴ ወርቄን አውልቄ ሸጬ አውቃለሁ፣ ምግብ ለምኜ አውቃለሁ» ማስተር አብነት ተወልዶ ያደገው ደቡብ ክልል ከምባታ ጠንባሮ ዞን ነው።  ከወላጆቹ እንደተረዳው ዕድሜውን « 31 ወይም 32 ብሆን ነው » ይላል።  ባለ ትዳር እና የአንድ ልጅ አባት ነው። ቤተሰቡ ቢናፍቀውም ለጊዜው ቦረና ቆይቶ ርካታ የሚሰጠውን መልካም ሥራ ለመፈፀም ወስኗል።  « ፈጣሪ ዝናቡን እስኪያዘንብላቸው ድረስ ፣ የሰውም አደራ በእጄ ላይ ስላለ እዛቦታ ላይ ከእነዚህ ወገኖቼ ጋር ሆኜ እቆያለሁ። » ወጣቶች አሁንም ሊያግዙ ይችላሉ ብሎ የሚያስተላልፈው መልዕክት « የአንድ እና የሁለት ሰው ኃላፊነት አይደለም። የሁላችንም ነው» በማለት ሁሉም ሰዎች በፀሎት እና በሚችሉት ነገር ሁሉ ከወገኖች ጎን እንዲቆሙ ይጠይቃል።  « ስለ ቀጣይ ሁኔታ ሊታሰብበት ይገባል። ቦረና አካባቢ ብቻ አይደለም የተራበ እና የተጠማ ሰው የሚኖረው። ከዚህ በኋላም ቢሆን ለችግር የተጋለጡ ሰዎችን ለመርዳት ሁላችንም በአንድነት ልባችን ለመልካም ነገር ሊዘጋጅ ይገባል» ይላል።
በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቦረና ውስጥ በድርቅ እና ርሀብ ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን ርዳታ በማስተባበር ላይ የሚገኘው ማስተር አብነት ከበደ ርዳታ መለገስ ለሚፈልጉ ሁሌም ስልኩ ክፍት እንደሆነ ገልጻል። 

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW