1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኅዳር 13 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ 

ሰኞ፣ ኅዳር 13 2014

ለ10 ጊዜያት በማሸነፍ ሲገሰግስ የነበረው አርሰናል በሊቨርፑል ቡድን የ4 ለባዶ ብርቱ ሽንፈት ገጥሞታል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የኮሮና ተሐዋሲ ጣጣ የባየር ሙይንሽን ቡድንን ከታችኛው ዲቪዚዮን ባደገ ቡድን እንዲሸነፍ አድርጎታል። ነገ እና ከነገ በስትያ 16 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ይከናወናሉ።

BdTD | UK, Londen - Premier League - Arsenal v Crystal Palace
ምስል Hannah Mckay/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በሳምንቱ መጨረሻ አርሰናል ያልጠበቀው ነገር ተከስቶበታል። ለ10 ጊዜያት በማሸነፍ ሲገሰግስ የነበረው አርሰናል በእንግሊዝ እግር ኳስ ታሪክ የረዥም ዘመን ታሪክ ባለቤት በሆነው የሊቨርፑል ቡድን የ4 ለባዶ ብርቱ ሽንፈት ገጥሞታል።  በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የኮሮና ተሐዋሲ ጣጣ የባየር ሙይንሽን ቡድንን ከታችኛው ዲቪዚዮን ባደገ ቡድን እንዲሸነፍ አድርጎታል። ነገ እና ከነገ በስትያ 16 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ይከናወናሉ። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን እና ማክስ ፈርሽታፐን አንገት ለአንገት ተያይዘዋል። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጸሐይ ገመቹ በፖርቹጋል ሊዝበን በተካሄደ የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር ስታሸንፍ በወንዶች ፉክክር ክብረወሰን ተሰብሯል። አብራችሁን ቆዩ! ሙዚቃ፦

አትሌቲክስ

ፖርቹጋል ሊዛቦን ውስጥ ትናንት በተከናወነ የግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጸሐይ ገመቹ ለድል ስትበቃ፤ በወንዶች ፉክክር ዩጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊሞ ክብረወሰን ሰብሯል። ፀሐይ ውድድሩን በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 1:06:06 ነው። ኬኒያውያቱ ዴይሲ ቼሮቲች እና ጆይስ ቼፕኬሞይ ከፀሐይ በ9 እና 13 ሰከንዶች ተበልጠው የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

በተመሳሳይ ርቀት የወንዶች ፉክክር፦ ዩጋንዳዊው ጄኮብ ኪፕሊሞ የዓለም ክብረወሰንን በአንድ ሰከንድ ብቻ በማሻሻል አሸናፊ ኾኗል። የሊዛቦን ግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር ውድድሩን ለማጠናቀቅ የ21 ዓመቱ ወጣት የፈጀበት 57 ደቂቃ ከ31 ሰከንድ ነው። ጄኮብ ኪፕሊሞ ባለፈው ዓመትም በተመሳሳይ የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር አሸናፊ ነበር።  ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰለሞን ባረጋ የወርቅ ሜዳሊያ ባስገኘበት የዘንድሮው ቶኪዮ ኦሎምፒክ የ10,000 ሜትር የሩጫ ውድድር ጄኮብ ኪፕሊሞ የነሐስ ሜዳልያ ተሸላሚ ነበር።

ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

በትናንቱ ፉክክር ኪፕሊሞን ተከትለው ኢትዮጵያውያኑ ሁዘይዲን መሀመድ እና ገብሬ ቤይታ ዲባባ ሁለተኛ እና ሶስተና በመሆን ተከታትለው ገብተዋል። በሴቶቹ ምድብ ደግሞ ኬንያውያኑ ዴሲ ቼሮቲች እና ጆይሲ ቼፕኬሞይ ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመሆን ተከታትለው ገብተዋል።

እግር ኳስ

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት ኤቨርተንን 3 ለ0 ድል ያደረገው ማንቸስተር ሲቲ በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛነቱን አስጠብቋል። ነጥቡን ወደ 26 ከፍ አድርጎም መሪው ቸልሲን በ3 ነጥብ ደረስኩብህ እያለው ነው። ኤቨርተን በበኩሉ ባለበት 11ኛ ደረጃ ላይ በ15 ነጥቡ ተወስኗል።   ቶትንሀም ሆትስፐር ሊድስ ዩናይትድን 2 ለ1 በማሸነፍ ነጥቡን 19 በማድረስ ከ9ኛ ደረጃውን ወደ 7ኛ አሻሽሏል።

ከትናንት በስትያ በነበሩ ግጥሚያዎች በተለይ አርሰናል እና ሊቨርፑል ያደረጉት ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች ለዋንጫ ግስጋሴ እጅግ በጣም ወሳኝ ነበር። በተለይ ለዐሥር ጊዜያት አንዳችም ሳይሸነፍ ሲገሰግስ እዚህ ለደረሰው የአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ አርሰናል የሚያስቆጭ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አይሎ ለነበረው ሊቨርፑል አሸንፎ 3 ነጥብ መያዙ የሚገባ ነው ሆኖም 4 ለ0 ማሸነፉ ግን ለአርሰናሎች እጅግ ያልተጠበቀ ነበር። ጨዋታው በተፋፋመበት ወቅት የሊቨርፑሉ አጥቂ ሳዲዮ ማኔ ጥፋት ሰርቷል በሚል የአርሰናሉ አሰልጣኝ መቆታቸው እና የሊቨርፑሉ አቻቸው ዬርገን ክሎፕም በተመሳሳይ መናደዳቸው ሁለቱ አሰልጣኞችን ዱላ ቀረሽ ንትርክ ውስጥ ከቷቸው ነበር።  የማታ ማታ ግን የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ በውጤቱ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጠዋል።

ምስል Jason Cairnduff/AFP/Getty Images

የመጀመሪያዋን ግብ በ39ኛው ደቂቃ ላይ ሳይጠበቅ ድንገት ሳዲዮ ማኔ ከመረብ አሳርፏል። በሁለተኛው አጋማሽ 52ኛው ደቂቃ ላይ ዲዮጎ ጆታ ሁለተኛዋን ግብ ካስቆጠረ በኋላ ግን የአርሰናል የመከላከል ስልት ውጥንቅጡ ወጥቷል።  73ኛው ደቂቃ ላይ ሞሐመድ ሳላኅ እንዲሁም በ77ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ታኩሚ ሚናሚኖ ሦስተኛ እና አራተኛ ግባቸውን አስቆጥረው ሊቨርፑልን በስተመጨረሻ የ4 ለ0 ታላቅ ድል አጎናጽፈውታል። በዚህም መሰረት ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ካደረገው 12ኛው ዙር ጨዋታ በኋላ በ25 ነጥብ የሦተኛ ደረጃን ይዟል። ከመሪው ቸልሲ በ4 እንዲሁም ከማንቸስተር ሲቲ በ1 ነጥብ ብቻ ይበለጣል። 84ኛው ደቂቃ ላይ ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ከሊቨርፑል አካዳሚ የመጣውን የ19 ዓመቱ ታዳጊ ቴይለር ሞርቶንን አቅፈው ወደ ሜዳው በመላክ ከቡድኑ ጋር በወሳኝ ግጥሚያ የመጀመሪያ ልምድ እንዲካፈል ዕድሉን አመቻችተውለታል። አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ለአዳዲስ ታዳጊ ተጨዋቾች በሚያመቻቹት ዕድልም በበርካቶች ዘንድ ተደጋጋሚ ውዳሴዎች ይቀርብላቸዋል። ሊቨርፑል በሻምፒዮንስ ሊጉ ደግሞ ከነገ በስትያ የፖርቹጋሉ ፖርቶን ይገጥማል።

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ከተከናወኑ ሌሎች ግጥሚያዎች፦ በርንሌይ ከክርሪስታል ፓላስ እንዲሁም ኒውካስል ዩናይትድ ከብሬንትፎርድ ሦስት እኩል ተለያይተዋል። ኖርዊች ሳውዝሐምፕተንን 2 ለ1 ሲያሸንፍ፤ አስቶን ቪላ ብራይተንን 2 ለ0 ድል አድርጓል። ዌስትሀም በዎልቭስ የ1 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። ሌላው ከሳምንቱ መጨረሺያ ግጥሚያዎች በርካታ ደጋፊዎቹን እጅግ ያበሳጨው ማንቸስተር ዩናይትድ ከዋትፎርድ ጋር ያደረገው ጨዋታ ነበር። ማንቸስተር ዩናይትድ ከታችኛው ዲቪዚዮን ባገኘው ዋትፎርድ 4 ለ1መንኮታኮቱ በቋፍ ላይ የነበሩት አሸልጣኙ ኦሌ ጉናር ሶልሳካዬርን እንዲሰናበቱ አድርጓል።

ከዚህ ቀደም በሜዳቸው በሊቨርፑል የ5 ለ0 ሽንፈት አስተናግደው የነበሩት አሰልጣኝ ኦሌ ጉናር ሶልሳካዬር በማንቸስተር ሲቲም የ2 ለ0 ሽንፈት ገጥሟቸው ነበር። ከቅዳሜ ዕለቱ ሽንፈት በኋላ ግን ማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኙን ሊታገስ ባለመቻሉ ትናንት አሰናብቷቸዋል። በእሳቸው ፈንታም ብዙም ልምድ የሌላቸው ረዳታቸው ሚካኤል ካሪክን ለመሾም እንደ አማራጭ ማቅረቡም ተሰምቷል። ይህ ግን ሌላ ጊዜያዊ አሰልጣኝ እስኪመደብ ድረስ ነው ተብሏል።

ምስል picture-alliance/empics/S. Bellis

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባየርን ሙይንሽን በኮሮና ሰበብ ያልተጠበቀ ሽንፈት ባልተጠበቀ ቡድን ገጥሞታል። በኮሮና ተሐዋሲ ከተጠቃው ዮሱዋ ኪሚሽ ጋር ቅርበት የነበራቸው አራት ተጨዋቾች እራሳቸውን ነጥለው እንዲቆዩ ተደርገዋል። ባየርን ሙይንሽን በኮሮናው የተነሳ ስላልተከተቡ ግን ደግሞ ከኪሚሽ ጋር በመቀራረባቸው መሰለፍ ያልቻሉ 4 ተጨዋቾችን ደመወዝ ቅቆርጣለሁ ብሏል። ተጨዋቾቹም ሠርጌ ግናብሬ፤ ጃማል ሙሲያላ፤ ኤሪክ ማክሲም ቾፖ ሞቲንግ እና ሚሻኤል ኩይዛኔ ናቸው። እነዚህ ተጨዋቾች ባለመሰለፋቸውም ባየርን ሙይንሽን ከታችኛው ዲቪዚዮን ባደገው አውግስቡርግ ቡድን ሽንፈት ገጥሞታል። ሽቱትጋርትን 2 ለ1 ያሸነፈው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ነጥቡን 27 አድርሶ ባየርን ሙይንሽን በአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ ተጠግቶታል።

ባየርን ሙይንሽን በተሸነፈበት ጨዋታ ያልተሰለፈው ዮሱዋ ኪሚሽ የኮሮና ክትባት ወደፊት ረዘም ባለ ጊዜ ችግር ያመጣብኛል በሚል ሳይከተብ ቀርቷል። ይህ ውሳኔው በባለሞያዎች ተቀባይነት የሌለው ነው በሚል ቅጣት ይጠብቀዋል ተብሏል። በዚህም መሰረት ዮሱዋ ኪሚሽ በእየሳምንቱ ከደሞዙ €400,000 ዩሮ ገደማ ይቆረጥበታል ተብሏል። እሱም ሆነ ሌሎቹ አራት ተጨዋቾች ትቀጣላችሁ መባሉ «እንዳስደነቃቸው» በመግለጥ ጉዳዩን በሕግ ሊይዙት እያሰቡበት መሆኑንም ይፋ አድርገዋል።

ምስል MIS/imago images

ነገ እና ከነገ በስተያ 16 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ይኖራሉ። ነገ ማታ ባየርን ሙይንሽን ከዲናሞ ኪዬቭ እንዲሁም ማንቸስተር ዩናይትድ ከቪላሪያል በተመሳሳይ ሰአት ይጋጠማሉ። ከሁለቱ ጨዋታ በመቀጠል ነገ ማታ ስድስት ጨዋታዎች ይከናወናሉ። ባርሴሎና ከቤኔፊካ፤ ቸልሲ ከጁቬንቱስ፤ ቮልፍስቡርግ ከሴቪያ፤ ማልሚዮ ከዜኒት፤ ሊል ከኤርቢ ዛልስቡርግ እንዲሁም ያንግ ቦይስ ከአታላንታ ይጋጠማሉ። ረቡዕ ማታ ደግሞ፦ ኢንተር ሚላን ከዶኒዬትስክ እንዲሁም አያክስ አምስተርዳም ከቤሽኪታሽ ጋር በተመሳሳይ ሰአት ይጫወታሉ። ከዚያም እንደ ማክሰኞው ሁሉ ስድስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰአት ይኖራሉ። ማንቸስተር ሲቲ ከፓሪ ሳንጃርሞ፤ ዶርትሙንድ ከስፖርቲንግ፤ አትሌቲኮ ማድሪድ ከሚላን፤ ሊቨርፑል ከፖርቶ፤ ብሩዥ ከኤርቤ ላይፕትሲሽ እንዲሁም ሪያል ማድሪድ ከሸሪፍ ጋር ይጫወታሉ።

የመኪና ሽቅድምድም

በፎርሙላ አንድ የካታር የመኪና ሽቅድምድም የመርሴዲስ አሽከርካሪው ሌዊስ ሐሚልተን ድል ቀንቶታል። በካታሩ ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን ተቀናቃኙ ማክስ ፈርሽታፐንን አሸንፎ ለድል በቅቷል። ፈርናንዶ አሎንሶ በአልፓይኑ የሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል። ሁለት ዙር ውድድሮች በቀሩት የዘንድሮ የመኪና ሽቅድምድም የሬድ ቡሉ አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐን 351.5 ነጥብ አለው። የመርሴዲሱ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን የሚበለጠው በ8 ነጥብ ብቻ ነው። ቀጣዩ ውድድር ለሁለቱም የሞት ሽረት ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW