ነዋሪዎችን ቅር ያሰኘው በዎላይታ ዞን ለግለሰቦች ተሽጧል የተባለው ጥብቅ ደን ጉዳይ
ሰኞ፣ ሐምሌ 29 2016በዎላይታ የደን ሽያጭ ያስነሳው ቅሬታ
ሲሞን አዳነ እና አብረሃም ወጋቶ በዎላይታ ዞን ሶዶ ዙሪያ ወረዳ ዝጋ ቦርኮሼ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው ፡፡ በሚኖሩበት ቀበሌው በአምስት ሄክታር መሬት ላይ የነበረው የደን ይዞታ ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ ነባር የደን ይዞታ እንደነበር ይናገራሉ ፡፡ የደን ይዞታው ጽድን ጨምሮ በተለያዩ አገር በቀል ዛፎች የተሞላ እንደነበር የጠቀሱት ሲሞን እና አብረሃም በሂደት ግን የአካባቢው አስተዳደር ለግለሰቦች በመሸጥ በውስጡ የሚገኙ ዛፎች እንዲቆረጡ መደረጉ ቅሬታ መፍጠሩ ነው ለዶቼ ቬለ የተናገሩት ፡፡
የሽያጩ ምክንያታዊነት
በዞኑ ሶዶ ዙሪያ ወረዳ ዝጋ ቦርኮሼ ቀበሌ የሚገኘው ደን ለግለሰቦች ሲሸጥ ከጅምሩ ጥያቄ ማንሳታቸውን የቀበሌው ነዋሪዎች ገልጸዋል ፡፡ የደን ሽያጬ ከ2015 እስከ 2016 ዓም ድረስ ቀስ በቀስ በሂደት መከናወኑን የሚናገሩት የቀበሌው ነዋሪዎች ሲሞን እና አብረሃም “ የወረዳውም ሆኑ የቀበሌው አመራሮች በጉዳይ ላይ ከህብረተሰቡ ጋር ያደረጉት ምንም አይነት ምክክር የለም ፡፡ ከ30 ዓመታት በፊት በህብረተሰቡ የለማ ጥብቅ የተፈጥሮ ደን ላይ ዝም ብለው ነው የወሰኑት “ ብለዋል ፡፡በሸካ ደን ላይ የደረሰዉ የእሳት ጉዳት
ደኑ ተሽጧል መባሉን የሰሙት ደኑን ገዝተናል የሚሉ ሰዎች ወደ አካባቢው ተሽከርካሪዎችን በማስገባት ዛፎችን መቁረጥ እንደጀመሩ መሆኑን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎች “ በወቅቱ ወደ ወረዳው አስተዳደር በመሄድ ድርጊቱ አግባብ አለመሆኑን ገልጸናል ፡፡ ይሁንእንጂ የሥራ ሃላፊዎች የደኑ ሽያጩ ለመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ክፍያ የሚውል ነው የሚል ምላሽ ሰጥተውናል ፡፡ የደን ሽፋንን ለማሳደግ በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ በሚከናወንበት በአሁኑወቅት ነባር ደኖችን መቁረጥ አግባብነት የጎደለው ተግባር መሆኑን በየደረጃው ለሚገኙ የዞኑ አስተዳደሮች አመልክተናል ፡፡ ነግር ግን በእኛ ጩኸት ብቻ ደኑን ከውድመት መታደግ አልተቻለም ፡፡ ምክንያቱም በተለያዩ ጫናዎች የተነሳ ድርጊቱን እስከመጨረሻው ገፍተን ለማውገዝ ባለመቻላችን አሁን ላይ በደኑ ውስጥ የሚገኙ ዛፎች ሙሉ በሙሉ ተቆርጠዋል “ ብለዋል ፡፡
የተጀመረው ምርመራ
ዶቼ ቬሌ ተሸጠ የተባለውን ደን አስመልክቶ ከሶዶ ዙሪያ ወረዳ የአካባቢ ጥበቃና የደን ልማት ጽህፈት ቤት የሥራ ሃላፊዎች ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቋል ፡፡ ይሁንአንጂ ሃላፊዎቹ ጉዳዩ በዞን ደረጃ የተያዘ ነው የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል ፡፡ ደኑን ገዝተዋል የተባሉ ግለሰቦችን በስልክ አድራሻቸው ፈልጎ ማግኘት አልተቻለም ፡፡ ወደ ሃላፊነት የመጡት በቅርቡ መሆኑን የተናገሩት የዎላይታ ዞን የአካባቢና ደን ጥበቃ መምሪያ ሃላፊ አቶ ማርክነህ ማለዳ ግን ደኑ መሸጡን እና ህብረተሰቡም ቅሬታ ማቅረቡን ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል ፡፡ደን ሕይወት ነዉ
ጉዳዩ እሳቸው ለሚያስተዳድሩት መምሪያና ለዎላይታ ዞን አስተዳደር መቅረቡን የጠቀሱት አቶ ማርክነህ “ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ የሚለውን ለማወቅ ግን ኮሚቴ ተቋቁሞ የማጣራት ሥራው እየተከናወነ ይገኛል ፡፡ ኮሚቴው በሚያቀርበው የምርመራ ውጤት መሠረት አሥፍላጊውን አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል “ ብለዋል ፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ጨምሮ በስተደቡብ በሚገኙ የኢትዮጵያ አካባቢ ከደን መመናመን ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች እንደሚከሰቱ ይታወቃል ፡፡ በያዝነው ወር አጋማሽ በጎፋ ዞን ከ240 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው የመሬት መንሸራተት መንስኤው ከዚሁ የአካባቢ መራቆት ጋር የተያያዘ ሥለመሆኑ ባለሞያዎች ሲገልጹ ነበር ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ