1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ነገን ዛሬ እንትከል» አረንጓዴ አሻራ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 11 2015

በኢትዮጵያ የተራቆተው የደን ሃብት እንዲያገግም የችግኝ ዘመቻ በየዓመቱ መካሄድ ከጀመረ ዘንድሮ አራት ዓመትን ያዘ። የአየር ንብረት ለውጥ ላስከተለው ተጽዕኖ ከተጋለጡት የአፍሪቃ ቀንድ ሃገራት በቀዳሚነት ከሚሰኑት ተርታ የምትገኘው የኢትዮጵያ ጥረት የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።

Äthiopien Green Legacy-Kampagne | Pflanzung von 500 Millionen Setzlingen
ምስል Dr Adefires Worku

በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞች የመትከሉ ጥረት

This browser does not support the audio element.


120 ሚሊየን ገደማ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቅ ከሚጎዱ ሃገራት አንዷ መሆኗን የተመድ መረጃ ያመለክታል። ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ተጋላጭ የሆኑት የዝናብ ጥገኛ የሆነው የግብርናው ዘርፍ፤ የውኃ አቅርቦቱ፤ ቱሪዝምም ሆነ የደን ይዞታው የኢትዮጵያን ተጋላጭነት የሚያባብሱ ምክንያቶች መሆናቸውንም ይጠቁማል። ጤና ይስጥልን 
ኢትዮጵያ ውስጥ በአራት ዓመታት 20 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ የዘመቻ ችግኝ ተከላው በ2011 ዓ,ም ነው የተጀመረው። እስካሁን ባጠቃላይ ስንት ችግኝ እንደተተከለ መረጃዎች ከየክልሉ እየተሰባሰቡ መሆኑን የገለጹልን የደን ዘርፍ ባለሙያ እና የብሔራዊ አረንጓዴ አሻራ የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ፤ እስካሁን ባለው መረጃ ከታቀደው በላይ ችግኝ መተከሉን ይናገራሉ። ሆኖም የተባለውን በገለልተኛ ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋም ለማጣራት ሥራ መጀመሩንም ያመለክታሉ።
የደን ባለሙያው እንደሚሉት በዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ 92 ሺህ ሄክታር ደን ይጨፈጨፍ እንደነበር የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ። ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የተደረገ ጥናት ደግሞ የሚመነጠረው የደን መሬት መጠኑ በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን አመላክቷል። ወደ 32 እና 33 ሺህ ሄክታር ወርዷል። አረጓዴ አሻራ የደን ጭፍጨፋ እንዲቀንስ ለማደርጉ ማሳያ ቢሆንም ይህም ግን እንደኢትዮጵያ ላለ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ተጋላጭ ሀገር ትንሽ የሚባል እንዳልሆነም ነው ያመለከቱት። እንዲያም ሆኖ ግን የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ አድርጎታል ብለው ያስባሉ ዶክተር አደፍርስ።
እናም በሚቀጥሉትም ዓመታት በተመሳሳይ መልኩ የችግኝ ተከላው መቀጠል እንደሚኖርበትም ነው ባለሙያው ያሳሰቡት። የኢትዮጵያ የደን ዘርፍ ትኩረት የተነፈገው እንደሆነ ለዓመታት ድምጻቸውን ሲያሰሙ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር አደፍርስ ወርቁ፤ በአሁኑ ጊዜ ለዘርፉ የሚመደብ የፋይናንስ መጠንም ሆነ የሚሰጠው ቦታ ከደን ባለሙያዎች አልፎ የመንግሥትን ጆሮ ያገኘ መሆኑን እንደ አንድ እርምጃም ጠቅሰዋል። አረንጓዴ አሻራ ዛሬ የሁሉም ጉዳይ ሆናልም ባይ ናቸው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡ በዘመቻ እየወጣ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎችን እየሠራ መኖሩ ያስታወሱት ባለሙያው፤ አረንጓዴ አሻራ በሚል መንግሥት ትኩረት የሰጠው የችግኝ ተከላ ለዓመታት ሳያሰልስ መቀጠሉ አዎንታዊ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል እምነታቸው ነው። በብሔራዊ ደረጃ የአረንግዴ አሻራ ማስጀመሪያ ቀን መኖሩን፤ እያንዳንዱ ክልልም በየበኩሉ የችግኝ ተከላውን ቀን እንደሚያውጅም አስታውሰዋል። የችግኝ ተከላዎቹም በየጊዜው መሪ ቃል አላቸው፤ የመጀመሪያው 40 ችግኝ በነፍስ ወከፍ»፤ በኮቪድ ጊዜ «እየተጠነቀቅን እንተክላለን»  ከዚያም፤ «ኢትዮጵያን እናልብሳት» የአምናው፤ «አሻራችንን ለትውልዳችን እናኑር» የዘንድሮው ደግሞ ፤ «ነገን ዛሬ እንትከል» የሚሉ ሲሆን ዶክተር አደፍርስ እነዚህ ሁሉ የደን ልማት እና ጥበቃን ማዕከል ያደረጉ ፍልስፍናዎች ይሏቸዋል። 
ችግኝ መተከሉ አዎንታዊነቱ አያነጋግርም የሚሉት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት የደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ የደን ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ አቶ ዘላለም ታደለ፤ ከችግኝ ተከላው ጎን ለጎን ቅድመ ተከላ፣ በተከላው ጊዜ እና ድህረ ተከላ ትኩረት ያሻዋል ይላሉ። 
ትናንት በተካሄደው የአንድ ጀንበር መርሃግብር 500 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ነው የታለመው። ዶክተር አደፍርስ በዚህ ረገድ የመረጃ ፍሰትን ተአማኒ በሆነ ምልኩ ለማሰባሰብ እየተሞከረ ነው ይላሉ። 
የዘመቻው ችግኝ ተከላ የሚደገፍና የአየር ንብረት ለውጡ ጫና ላይ ሊያሰከትል የሚችለው ውጤትም አዎንታዊ እንደሚሆን የሚናገሩት የደን ሳይንስ መምህርና ተመራማሪው አቶ ዘላለም፤ ተተከለ የሚባለውን የችግኝ ብዛት ጥያቄ ከፈጠረባቸው አንዱ ናቸው። ችግኝ መተከሉ እውነት መሆኑን በመግለጽ ቁጥሩ ግን ተጋኗል ባይ ናቸው። 
የእሳቸውን ሃሳብ ብዙዎች ይጋሩታል። 120 ሚሊየን ሕዝብ ባላት ኢትዮጵያ ያውም በተወሰነ አካባቢ በአንድ ጀንበር ከ500 ሚሊየን በላይ ችግኝ መተከሉ ተነግሯል።  በዘመቻው የችግኝ ተከላ ለደን፤ ለውበት፤ ለጥምር ግብርና እንዲሁም እንደቀርከሃ ያሉ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሀገር በቀል እንዲሁም ኤኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው እንደሚገኙበት ዶክተር አደፍርስ ወርቁ ገልጸውልናል። ለሰጡን ማብራሪያ ባለሙያዎቹን እናመሰግናለን።

በደቡብ ኢትዮጵያ የችግኝ ተከላው ዘመቻምስል Shewangizaw wegayoh/DW
የችግኝ ተከላው ዘመቻ በየመሥሪያ ቤቱም ይከናወናልምስል Dr Adefires Worku
በዘመቻው ችግኝ ተከላ የተራቆቱ አካባቢዎች ላይ ጥረቱ ይደረጋልምስል Dr Adefires Worku
«ዛሬ የተከሉት ዛፍ ነገ ጥላ ይሆናል»ምስል Shewangizaw wegayoh/DW

 ሸዋዬ ለገሠ 

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW