1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ነጻነታቸውን ስለተነፈጉ ሰዎች የተደረገ ብሔራዊ ምርመራ

ሰኞ፣ መጋቢት 16 2016

ኢሰመኮ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሊ እንዲሁም በቀድሞው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የአቤቱታ መቀበያ መድረኮችን አካሂዶ ባሰባሰባቸው ማስረጃዎች "ነጻነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ እና ስልታዊ በሆኑ መንገዶች የሚደርሱ የመብት ጥሰቶች" መኖራቸውን አረጋግጧል።ስለምርመራ ውጤት ከመንግሥት አካል ምላሽ ማካተት አልቻልንም።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ብቶች ኮሚሽን
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ብቶች ኮሚሽን ምስል Solomon Muche/DW

ነጻነታቸውን ስለተነፈጉ ሰዎች የተደረገ ብሔራዊ ምርመራ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፉት አምስት ዓመታት ነጻነታቸውን ስለተነፈጉ ሰዎች መብቶች ጉዳይ በአራት ክልሎች ባከናወናቸው 4 ብሔራዊ ምርመራዎች "በተደጋጋሚ እና ስልታዊ በሆኑ መንገዶች የመብት ጥሰቶች" ይፈፀሙ እንደነበር ማረጋገጡን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ባደረጋቸው ምርመራዎች ነፃነታቸው የተነፈጉ ሰዎችን "መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ማሰርን፣ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝን፣ በፍርድ ቤት የተሰጠ የዋስትና መብትን በመጣስ ማሰርን ጨምሮ የዘፈቀደ እስራት" ሰለባ ሆነው እንደነበር ከተጎጅዎች እና ምስክሮች ማረጋገጡን ባወጣው ዘገባ አመልክቷል። የኮሚሽኑ ምርመራ "ወሲባዊ ጥቃትን፣ ደብዛን አጥፍቶ ማሰርን፣ በግዳጅ መሰወርን፣ እና በቂ ምግብና ውኃ በሌላቸው፣ በተጨናነቁ፣ የንጽሕና እና የሕክምና አገልግሎት ባልተሟላላቸው እስር ቤቶች ማሰርን ጨምሮ ማሠቃየትን እና ያልተገባ አያያዝን" የመሳሰሉ የመብት ጥሰቶች መድረሳቸውንም ገልጿል።

የኮሚሽኑ ዝርዝር የምርመራ ውጤት

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮምሽን ከሚያዝያ 2010 እስከ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ባሉት አምስት ዓመታት ነጻነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች መብቶች ላይ ባደረገው ባለ 130 ገፅ ዝርዝር ዘገባ አቤቱታ አቅራቢዎችን ፣ ምስክሮችን እና የመንግሥት አካላትን ፊት ለፊት በማገናኘት የመብት ጥሰቶችን አድምጧል።

 የኢሰመኮ አስቸኳይ ጥሪ

ኢሰመኮ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሊ እንዲሁም በቀድሞው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የአቤቱታ መቀበያ መድረኮችን አካሂዶ ባሰባሰባቸው ማስረጃዎች "ነጻነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ እና ስልታዊ በሆኑ መንገዶች የሚደርሱ የመብት ጥሰቶች" መኖራቸውን አረጋግጧል።

በነዚህን ሰዎች ላይ መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች "የማሰር፣ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ የመያዝ፣ በፍርድ ቤት የተሰጠ የዋስትና መብትን የመጣስ ፣ የዘፈቀደ እስራትን፣ ወሲባዊ ጥቃትን፣ ደብዛን አጥፍቶ ማሰርን፣ በግዳጅ መሰወርን፣ እና በቂ ምግብና ውኃ በሌላቸው፣ በተጨናነቁ፣ የንጽሕና እና የሕክምና አገልግሎት ባልተሟላላቸው እስር ቤቶች ማሰርን ጨምሮ ማሠቃየትን እና ያልተገባ አያያዝን፤ እንዲሁም በቤተሰብ፣ በሃይማኖት አማካሪዎች እና በሕግ አማካሪዎች የመጎብኘት መብትን መከልከል" እንደተፈፀመም ኮሚሽኑ ገልጿል።

ይህ በአይነቱ ለመጀመርያ ጊዜ የተደረገ የተበለው ብሔራዊ የመብት ጥሰት ምርመራ ስልት ውጤት የታየበት እና በጎ ልምድ መሆኑን በኮሚሽኑ የሲቪል፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች  ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።

አቶ ዳንኤል በቀለ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነርምስል Solomon Muche/DW

ነጻነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች በማቆያ ቤቶች እና በማረሚያ ቤቶች ረዘም ላለ ጊዜ ከመቆየታቸው አንጻር የመተዳደሪያ ገቢያቸውን የሚያጡ መሆናቸው እንዲሁም ለጥሰቶቹ የመፍትሔ እና የካሳ ሥርዓት አለመኖሩ ሌሎች የተለዩ ተጨማሪ ችግሮች ናቸው ተብሏል።ባለፈው አንድ ዓመት ከዚህ በፊት ያልታዩ የመብት ጥሰቶች ታይተዋል፤ ኢሰመኮ

አንዳንድ ጥሰቶች እና ችግሮች ስልታዊ ከመሆናቸውም ባሻገር በብዙ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ የመፈጸም አዝማሚያን ማሳየታቸው ተገልጿል። አብዛኛዎቹ የመብት ጥሰቶች የተፈጸሙባቸው ዐውዶች ከግጭት፣ ካልተመጣጠነ የመንግሥት የኃይል እርምጃ፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሁኔታዎች፣ ከምርጫ እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ ሁኔታዎች ጋር የተያያዙ መሆናቸውን እና ጥሰቶቹን በመፈጸም ረገድ ሚሊሻዎች፣ የቀበሌ አስተዳዳሪዎች፣ የመደበኛ እንዲሁም የልዩ ኃይል ፖሊስ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት ተሳትፎ የነበራቸው መሆኑን የኢሰመኮ የምርመራ ዘገባ ውጤት ያመለክታል።

የዋና ክሚሽነሩ መልእክት 

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ነጻነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች የሚጣሱባቸውን ዐውዶች በመመርመር፣ የጥሰት መንስኤዎችን እልባት ለመስጠት፣ ጥሰቶችን ለማስቆም፣ በጥሰቶች ተሳታፊ የሆኑ አጥፊዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ እና ለተጎጂዎች ተገቢ የሆነውን የካሳ ሥርዓት ለመዘርጋት እንዲሁም ይህንኑ በሥራ ላይ ለማዋል የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ማሳሰቢያ

የኮሚሽኑን የምርመራ ውጤት በሚያጠናክር ሁኔታ ሰሞኑን  የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ 14 በእሥር ላይ የሚገኙ ሰዎች ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ "አካላዊ ፣ ሞራላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት" እየተፈፀመባቸው መሆኑን ገልፀዋል።

ማሳያዎች

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ለፍትሕ ሚኒስቴር በእጅ የተፃፈው እና "እገታን፣ ስወራን እና ፍትሕ ማጣትን ይመለከታል" የሚል ርእስ የተሰጠው ደብዳቤ "የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት እና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት አያያዝን በጣሰ መልኩ ማንነትን መሠረት ያደረገ ስድብ፣ ዘለፋ ፣ ማስፈራራት፣ ዛቻ ፣ ድብደባ እና ዝርፊያ" በታሳሪዎች እና በቤተሰቦቻቸው ላይ ጭምር መፈፀሙን ይዘረዝራል። ይህንን የምርመራ ውጤት በተመለከተ ከመንግሥት አካል ምላሽ ለማካተት ጥረት ብናደርግም ጥረታችን አልሰመረም።

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW