ናይጀሪያውያን በዘንድሮው ምርጫ የሚመኙት መሪ
ቅዳሜ፣ የካቲት 18 2015
ናይጀሪያውያን ዛሬ መሪያቸውን ለመምረጥ ድምጻቸውን ሲሰጡ ውለዋል። በእጩ ተወዳዳሪነት የተሰለፉት 18 ፖለቲከኞች ቢሆኑም በህዝብ አስተያየት መመዘኛ ውጤቶች መሠረት ሦስቱ ብቻ ናቸው ዋነኞቹ ተፋላሚዎች። ከ18ንቱ ውስጥ ያሉት አንዲት ሴት ብቻ ናቸው። ተሰናባቹ የናይጀሪያ ፕሬዝደንት ሙሀማዱ ቡሀሪ ለስምንት ዓመታት ገደማ በሥልጣን ቆይተዋል። የአስተዳደር ጊዜያቸውም ያለመረጋጋት ያጀበው፤ አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍልም የገንዘብ ለውጥ ባስከተለው እጥረት ምክንያት የሚመገበውን እንኳን ለመግዣ ቤሳ ቤስቲን በማጣት ሲቸገር የታየበት ነው በሚል ይተቻሉ። በአንጻሩ ደጋፊዎቻቸው የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር እንዲሁም ጽንፈኝነትን ለመዋጋት መድከማቸውን በአዎንታዊነት ያነሱላቸዋል።
አረረም መረረም ቡሀሪ በትረ ሥልጣኑን ለተረኛ የሚያስረክቡበት ጊዜ ላይ ደርሰዋል። በቀጣይ በጫማቸው የሚገባው የሀገሪቱ መሪም ከፊቱ ከባድ ሥራ እንደሚጠብቀው ነው የሚነገረው።
ለፕሬዝደንትነት በቀዳሚነት ከተሰለፉት ተፎካካሪዎች የገዢው የሁሉም ተራማጆች ምክር ቤት ፓርቲ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ APC እጩ የ70 ዓመቱ ቦላ አህመድ ቲኑቡ «የፕሬዝደንትነቱ ተራ የዩሩባ» ነው በሚል ደጋፊዎቻቸውን ለማሰባሰብ ተንቀሳቅሰዋል። ከጤና እክል በተጨማሪ በሙስና ስማቸው የሚነሳው ቲኑቡ ግን ጭምጭምታውን ሁሉ ያስተባብላሉ።
በአንጻሩ ተቀናቃኛቸው የተቃዋሚው የህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ PDP እጩ የ76 ዓመቱ አቲኩ አቡበከር በበኩላቸው ናይጀሪያውያን ድምጻቸውን ሲሰጡ ከዩሩባም ሆነ ኢግቦ ጎሳ የመጣ ብለው አይደለም ማለታቸው ተሰምቷል። በኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ ዘመን ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ያገለገሉት አቡበከር እስካሁን አምስት ጊዜ ለፕሬዝደንትነት ተወዳድረው አልተሳካላቸውም። ቱጃሩ የንግድ ሰው አቲኩ አቡበከር እንደ አህመድ ቲኒቡ ሁሉም በሙስና ይወቀሳሉ።
ሌላኛው ፕሬዝደንታዊ ውጩ የ61 ዓመቱ ፒተር ኦቢ ቀድሞ የPDP አባል የነበሩ ሲሆን ከ20 ዓመት በላይ በናይጀሪያ የዘለቀውን የሁለት ፓርቲ አገዛዝ ለመለወጥ ያለሙ እና በአብዛኛው የሀገሪቱ ወጣቶች ድጋፍ ያላቸው የንግድ ሰው ናቸው።
የፕሬዝደንት ምርጫ ናይጀሪያ ውስጥ ሲካሄድ ውጥረት የተለመደ ነው። አንደኛው በሌላኛው ጎሳ የመበለጥ፣ ተጽዕኖ ስር የመግባት ወይም የመገለል ፍርሃት ይውጠዋል። ከ200 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት ናይጀሪያ በርካታ ጎሳዎች ሲኖሩባት ከ500 በላይ ቋንቋዎች ይነገሩባታል። በሀገሪቱ አብላጫውን ቁጥርም ሆነ በፖለቲካው ተሳትፎ ተጽዕኖ ያላቸው ብዙሃኑ ሙስሊም የሆነው የሃውሳ ፉላኒ ማኅበረሰብ በሰሜን፤ አብዛኛው የክርስትና እምነት ተከታይ የሚገኝበት የዩሩባ ጎሳ በደቡብ ምዕራብ፤ እንዲሁም በደቡብ ምሥራቅ የሚገኘው የኢግቦ ጎሳ ናቸው።
የናይጀሪያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጎሳና ሃይማኖትን ያዛነቁ ናቸው። በዚህ ምክንያትም ፕሬዝደንት የሚሆኑትን አብዛኛው የክርስትና እምነት ተከታይ ከሆነበት ከደቡብ እንዲሁም ሙስሊም ከሚበዛበት ከሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በማፈራረቅ ለማቻቻል ሲሞከር ቆይቷል። ባለፉት ዓመታት ግን ይኽ አካሄድ አልተጠበቀም። ታዛቢዎች እንደሚሉት ሦስተኛው ተፎካካሪ ፒተር ኦቢ ከተሳካላቸው ብቻ ነው በናይጀሪያ የፕሬዝደንት ምርጫ የተለመደው የፍርርቅ ሥርዓት ዳግም ሊታይ የሚችለው። በሌጎስ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ ውስጥ ስለጎሳን ሚና ምርምር የሚያካሂዱት ፍራይዴይ ንዋንኮ ግን አሁን ናይጀሪያ በዋናነት የምትሻው አንድነቷን የሚያጸና መሪ ነው ይላሉ።
«በመጨረሻ ግን ሀገሪቱን ወደፊት ሊያራምዳት የሚችለው ሁላችንም የአንድ ሀገር ሰዎች መሆናችንን የሚያሳይ ሰው ነው። ይኽም ነው ዞሮዞሮ ሀገሪቱን ወደ አንድነት የያመጣው።»
ናይጀሪያ ከቅኝ አገዛዝ ነጻነቷን ካገኘችበት ከጎርጎሪዮሳዊው 1960 አንስቶ በሦስቱ ጎሳዎች መካከል ለሥልጣን የሚደረገው ፍትጊያ ጎልቶ ታይቷል። ሃይማኖት እና ጎሳን በሚጠቀሙት ፖለቲከኞች አማካኝነትም ተቃውሞዎች እና ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶችም ተደርገዋል። የፖለቲካ ልኂቃኑን አሰላለፍ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ራህማቱ ላዋል ታዝበዋል።
«የናይጀሪያ የፖለቲካ ልሂቃን እንደ ሀገር ለናይጀሪያ ሳይሆን ወደመጡበት አካባቢ ይበልጥ ያዘነበሉ ናቸው። ናይጀሪያ መንግሥትም ዋነኛው እና ብቸኛው የናይጀሪያ ህዝብ ጠባቂ እንደሆነ ተደርጎ ታይቶ አይታወቅም።»
የናይጀሪያን ፖለቲካዊ ይዞታ በቅርብ የሚከታተሉ ታዛቢዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ መጠን ያጣው ልዩነት፤ ድህነት እና የወደፊት ተስፋ ማጣት ወደ ውጥረት እያመራ እንደሆነ ይናገራሉ። በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኘው የኢግቦ ጎሳ ከዛሬ 80 ዓመታት በፊት የእርስ በእርስ ጦርነት አስነስቶ ወደነበረው በመገንጠል ቢያፍራ የሚሉትን ግዛት የመመስረት ጥሪ ዳግም እያቀረበ ነው። ብዙዎችም በፕሬዝደንት ቡሀሪ አስተዳደር ደስተኛ ባለመሆናቸው ከሳምንታት በፊት ታጣቂዎች የምርጫ እና በፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት ማድረሳቸው ተሰምቷል። ፍራይዴይ ንዋንኮ እንደሚሉትም የፕሬዝደንትነት ሥልጣን የመያዙ ተራ የእነሱ እንደሆነ እያሳሰቡ ነው።
«ፕሬዝደንቱ ላለፉት ስምንት ዓመታት በሥልጣን ላይ ሆነው ተመልክተዋል፤ ሆኖም ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ የናጀሪያውያንን ችግር መፍታት ያልቻሉበትንም ምክንያት ሊረዱት አልቻሉም። ደቡቦቹ አሁን ሥልጣኑ ወደ እነሱ መምጣት አለበት እያሉ ነው። ይኽም ተራቸው ነው። በደቡብ ምዕራብ ያሉትም ከእኛ ፕሬዝደንት ወጥቶ አያውቅም። ፕሬዝደንት እንፈልጋለን እያሉ ነው።»
እንዲያም ሆኖ የህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች የምርጫ ድሉ ከሁለቱ ዋነኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአንዱ ሊሆን እንደሚችል አመላክተዋል። የኦቢ ደጋፊዎችም ወጣቶችን ከኋላቸው ማሰለፍ ስለቻሉ አስገራሚ ስኬት ሊያስመዘግቡ እንደሚችሉ ይገምታሉ።የናይጄሪያ ምርጫ ለጀርመን ያለው አንድምታ
በትናንትናው ዕለትም በደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል የሴናተር ምርጫ እጩ የሆኑ ተወዳዳሪ በመገደላቸው በአካባቢው የሚካሄደው ምርጫ ለጊዜው መታገዱን የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል። አንድ የምክር ቤት አባልም በሚወዳደሩበት አካባቢ 500 ሺህ ዶላር በእጃቸው ይዘው በመገኘታቸው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል። በሀገሪቱ ሕግ በመንግሥት ካልተመዘገበ በቀር ከ10 ሺህ ዶላር በላይ ይዞ መንቀሳቀስ አይቻልም። በምርጫው ዋዜማ ዓርብ ዕለት ውጥረቱ ያሰጋቸው ናይጀሪያውያን በውጤቱ ምክንያት አመጽ ሊከተል ይችላል ብለው በመስጋት ምግብ እና አስፈላጊ ሸቀጦችን ሲሸምቱ መዋላቸውም ተሰምቷል። በተለመደው አሠራር ከሄደ የምርጫ ውጤቱ በሦስት ቀናት ውስጥ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ሸዋዬ ለገሠ