ናዳ ያስከተለው ስጋት ሺህዎችን ከመኖሪያ አካባቢያቸው ማስለቀቁ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 23 2017
በወረዳው ኮመር በተባለ ቀበሌ ባለፈው ሳምንት አምስት ሰዎች በናዳ ተቀብረው ሕይወታቸው ካለፈ ወዲህ ተጨማሪ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል የመሬት አንቅስቃሴ መታየቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በናዳ ሥጋት የተፈናቀሉ ቤተሰቦች በቤተ እምነቶች ተጠልለው እንደሚገኙ የገለጹት የወረዳው ባለሥልጣናት በረድኤት ድርጅቶች እና በባለሀብቶች የዕለት ደራሽ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የመሬት ናዳ ያሰጋቸው የኮመር ቀበሌ ነዋሪዎች
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአሪ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳየኮመር ቀበሌ ነዋሪዎች በአካባቢው በሚስተዋለው የመሬት እንቅስቃሴ የተነሳ 1,118 ሰዎች ቀበሌውን ለቀው መውጣታቸው እየተነገረ ነው። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ባለፈው ሳምንት ናዳ የአምስት ሰዎችን ሕወት ከቀጠፈ ወዲህ ሥጋት ገብቷቸዋል። በአሁኑ ወቅት በቀበሌው የመሬት መሠንጠቅ ምልክት መታየቱን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት የደቡብ አሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግዛው ሀይሌ «ክስተቱን ተከትሎም ሰዎች አካባቢውን እንዲለቁ አድረገናል» ብለዋል።
የሥጋቱ መጠን
የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አምስት ሰዎች በናዳ ተቀብረው ከሞቱ ከቀናት በኋላ ተጨማሪ ናዳሊከሰት ይችላል የሚል ሥጋት ማሳደሩን ነዋሪዎች ተናግረዋል። የመሬት መሰንጠቅ ምልክት ከባለፈው ሳምንት መግቢያ አንስቶ በቀበሌው መታየቱን የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው አቶ ግዛው ሀይሌ «በተለይም ናዳው አምስት ሰዎችን ቀብሮ ከገደለበት ሥፍራ አንስቶ እስከ ታች ድረስ እንዲሁም ግራና ቀኝ ባሉት መንደሮች የመሬት መሰንጠቅ አጋጥሟል። ሁኔታው በጣም አስጊ ነው። አካባቢው የሥጋት ቀጠና ውስጥ ነው የሚገኘው ማለት ይቻላል። አደጋ ከደረሰ በኋላ ከመሯሯጥ ቀድመን ሰዎች ቀበሌውን በመልቀቅ ወደ ቤተ እምነተ እንዲጠለሉ አድርገናል» ብለዋል።
ዘላቂ መፍትሄ
በአሁኑ ወቅት በቤተ እምነት ተጠልለው ለሚገኙ ነዋሪዎች በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር እና በባለሀብቶች አማካኝነት የዕለት ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል። በተለይም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር እንደ ድንኳን፣ ብርድ ልብስ፣የንጽሕና መጠበቂያ ሳሙናን ጨምሮ ምግብ ነክ ያልሆኑ ደጋፎችን ማድረጉን አስታውቋል። ነገር ግን ከጊዜያዊ ድጋፍ ባለፈ ዘላቂ አማራጮችን ማየት እንደሚገባ የጠቀሱት በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህር የደቡብ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ዱንዳ «ነዋሪዎች ምንአልባት እንደ ገዜ ጎፋ ወረዳ ነዋሪዎች በተለዋጭ መንደሮች ሊሰፍሩ የሚችሉበት ሁኔታ ማመቻቸት ወይንም የናዳ አደጋን ሊከላከሉ የሚችሉ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎችን በማከናወን ነሯቸውን በቀደመ መንደራቸው ሊቀጥሉ የሚችሉበትን አማራጭ በጥናት መለየት ያሥፈልጋል» ብለዋል።
የሚቲሪዎሎጂ ማስጠንቀቂያ
በኢትዮጵያ አብዛኞቹ አካባቢዎች በሚቀጥሉት 10 ቀናት ከመካከለኛ እስከ ከባድ የዝናብ ሥርጭት ስለሚኖር በወንዝ ዳርቻዎችና ረግረጋማ አካባቢዎች የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሲል የኢትዮጵያ ሚቲሬዎሎጂ ኢንስቲትዩት ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ አይዘነጋም። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተዳፋታማ በሆኑ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በሚከሰት የመሬት ናዳ ለበርካቶች ሕይወት መጥፋት ምክንያት እየሆነ ይገኛል። በክልሉ ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ባለፈው ዓመት ክረምት ደረሶ በነበረው የመሬት መንሸራተት አደጋ ከ300 በላይ ሰዎች ለሞት መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ