1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኔቶ በምሥራቅ አውሮፓ የመከላከላ ኃይሉን እንደሚያጠናክር ገለጸ

ሐሙስ፣ የካቲት 17 2014

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት በእንግሊዝኛ ምህጻሩ ኔቶ ዛሬ ካደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በኋላ ዩክሬን እና ሩሲያ በሚዋሰኑበት ምሥራቃዊ ግዛት የምድር፣ የባህር እና የአየር ኃይሉን ለማጠናከር መወሰኑን አስታውቋል። ቱርክ የሩሲያን እርምጃ "ኢ-ፍትኃዊ እና ሕገ-ወጥ" ስትለው ፈረንሳይ ለዩክሬን የምትሰጠውን እገዛ ለማጠናከር ቃል ገብታለች

Ukraine russischer Militäreinsatz in Ostukraine |   Tschuhujiw
ምስል፦ Aris Messinis/Getty Images/AFP

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት በእንግሊዝኛ ምህጻሩ ኔቶ ዛሬ ሐሙስ ካደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በኋላ ዩክሬን እና ሩሲያ በሚዋሰኑበት ምሥራቃዊ ግዛት የምድር፣ የባህር እና የአየር ኃይሉን ለማጠናከር መወሰኑን አስታወቀ። 

የኔቶ አምባሳደሮች ባወጡት መግለጫ "በጥምረቱ ምሥራቃዊ ክፍል ተጨማሪ የምድር፣ የአየር እና የባህር መከላከያ ኃይል ልናሰማራ ነው" ብለዋል። የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ የንስ ስቶልተንበርግ በምሥራቃዊ አውሮፓ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን የመከላከያ ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑን ለጋዜጠኞች አረጋግጠዋል።

የድርጅቱ አባላት የሆኑት የምስራቅ አዉሮጳ ሐገራት ኢስቶኒያ፣ ላቲቪያ፣ ሉቱኒያ እና ፖላንድ የሰሜን  የግዛት አንድነት፣ የፖለቲካ ነጻነት ወይም ጸጥታ አደጋ ውስጥ ሲወድቅ ሌላ ስብስባ እንዲጠራ ጠይቀዋል። ለግጭቱ ቅርበት ካላቸው አገራት አንዷ የሆነችው ሉቱኒያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጋለች።

የሩሲያ ወታደራዊ ሔሊኮፕተሮች በዛሬው ዕለት ከኪየቭ ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ ጎስቶሜል የተባለ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን የዩክሬን ባለሥልጣናት እንደተናገሩ ሬውተርስ ዘግቧል። ባለሥልጣናቱ እንዳሉት ከሩሲያ ሔሊኮፕተሮች መካከል ሶስቱን ዩክሬን መትታ ጥላለች። 

የኔቶ ዋና ጸሐፊ የንስ ስቶልተንበርግ በምሥራቃዊ አውሮፓ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን የመከላከያ ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑን ለጋዜጠኞች አረጋግጠዋል።ምስል፦ Yves Herman/REUTERS

የዩክሬን የድንበር ጥበቃ ባለሥልጣናት የሩሲያ ጦር ኪየቭ የተባለውን የዩክሬን ግዛት እና ዚይቶምይር የተባለውን ግዛት አገሪቱ ከቤላሩስ ከምትዋሰንበት ድንበር ጥሰው ለመግባት መሞከራቸውን ገልጸዋል። 

የኪየቭ ከተማ ከንቲባ ቪታሊ ክሊትሽኮ ዓለም ከዩክሬን ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። የቀድሞው ቦክሰኛ "በጦርነት ውስጥ ነን። ለአገራችን እየተዋጋን ነው። ነገር ግን የመላውን ዓለም እርዳታ እንፈልጋለን። በሩሲያ ላይ ጠንካራ ማዕቀብ መጣል አለበት" ብለዋል። በኪየቭ ከተማ ያለው ሁኔታ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ቢሆንም ከንቲባው በነዋሪዎች ዘንድ ሥጋት መኖሩን ግን አልሸሸጉም።

በኪየቭ ከተማ ያለው ሁኔታ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ቢሆንም ከንቲባው በነዋሪዎች ዘንድ ሥጋት መኖሩን ግን አልሸሸጉም።ምስል፦ Emilio Morenatti/AP Photo/picture alliance

ፈረንሳይ ለዩክሬን የምትሰጠውን ድጋፍ እንደምታጠናክር አስታውቃለች። ፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ "ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት ካወጀች በኋላ" የፈረንሳይ የመከላከያ ምክር ቤትን መሰብሰባቸውን የኤሊዜ ቤተ-መንግሥት አስታውቋል።  የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "ጦርነትን መምረጥ አስከፊ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው። ግዙፍ እና ከባድ ዋጋ በፍጥነት ያስከፍላል" ብለዋል። 

ቱርክ "ኢ-ፍትኃዊ እና ሕገ-ወጥ" ያለችው ሩሲያ የጀመረችውን ወታደራዊ እርምጃ በአፋጣኝ እንዲቆም ጥሪ አቅርባለች። የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "ወታደራዊ ተልዕኮው ተቀባይነት የሌለው ነው ብለን እናምናለን" ያለ ሲሆን "የሩሲያ ፌዴሬሽን ይኸን ኢ-ፍትኃዊ እና ሕገ-ወጥ እርምጃ በአፋጣኝ እንድታቆም ጥሪ" አቅርቧል።

ሩሲያ በቱርክ ጎረቤት ዩክሬን ላይ ጥቃት ከከፈተች በኋላ ፕሬዝደንት ረቺብ ጣይብ ኤርዶኻን በዋና ከተማዋ አንካራ የጸጥታ ስብሰባ አካሒደዋል። የሩሲያ እርምጃ "የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት" ነው ከሚል ድምዳሜ የደረሰው ስብሰባ "ተቀባይነት የለውም" ማለቱን የፕሬዝደንት ረቺብ ጣይብ ኤርዶኻን ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ይኸ ኩነት በፍጥነት የሚቀያየር ነው። ዶይቼ ቬለ ጉዳዩን በመከታተል አዳዲስ ዘገባዎችን ያቀርባል። ከምሽቱ አንድ ሰዓት የሚጀምረው የራዲዮ ሥርጭት በዚሁ ጉዳዮች ላይ ዘገባዎች ይኖሩታል።

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW