ንጉጊ ዋ ቲዮንጎ - ታላቁ የአፍሪቃ ዘመናዊ የሥነ-ጽሑፍ ሰው
ሐሙስ፣ ሰኔ 12 2017
ታላቁ የአፍሪቃ ዘመናዊ የሥነ-ጽሑፍ ሰው - ንጉጊ ዋ ቲዮንጎ
“ዲያብሎስ በመስቀል ላይ” እና “ማቲጋሪ” በተባሉት የልብ ወለድ ስራዎቻቸዉ ንጉጊ ዋ ቲዮንጎ ከቅኝ ግዛት በተላቀቀችዉ ኬንያ ያለውን ኢ-ፍትሃዊነት አጉልተዉ ያሳዩበት ነዉ። በዚህም ምክንያት ለስደት ተዳርገዋል። አፍሪቃ አህጉር እና የትውልድ አገራቸዉን ኬንያን ከምዕራባውያን የባህል የበላይነት ነፃ ማውጣት የኬንያው ፀሐፊ ንጉጊ ዋ ቲዮንጎ ዋንኛ ተልእኮም ነበር። ልጃቸው ዋንጂኩ ዋ ንጉጊ ግንቦት 21 ቀን 2017 ማለዳ በፌስቡክ ገጻቸዉ ላይ «አባታችን ንጉጊ ዋ ቲዮንጎ ማለፉን ስንገልፅ በተሰበረ ልብ ነው። ሙሉ ህይወቱን የኖረዉ ለበጎ ዓላማ በመታገል ነዉ» ሲሉ የንጉጊ ዋ ቲዮንጎ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ለዓለም አሳዉቀዋል።
በ 30 ዓመቱ ታዋቂ የሆነዉ ፀሐፊ
በማዕከላዊ ኬንያ በሊሙሩ ክልል በጎርጎረሳዉያኑ ጥር 5 ቀን 1938 ዓ.ም የተወለዱት ታዋቂዉ ኬንያዊ ደራሲ፤ ቤተሰቦቻቸዉ ያወጡላቸዉ ስም ጄምስ ነበር። ጀምስ ለአካለ መጠን ሲደርሱና ዓለምን በራሳቸዉ ሚዛን ማስቀመጥ ከጀመሩ በኋላ ግን ይህ ስም የእንጊሊዝ-አሜሪካን ቅኝ አገዛዝ ምልክት ነዉ ብለዉ ስላመኑበት፤ ከክርስትና ጊዜ ጀምሮ ሲጠሩበት የነበረዉን ስማቸዉን ወደ ንጉጊ ቀየሩት።የማዳም ቤትዋ ገጣሚ - ከሳዉዲ አረብያ - ፎዝያ ጀማል
በጎርጎረሳዉያኑ 1960ዎቹ መጀመሪያ ንጉጊ በካምፓላ፣ ዩጋንዳ በዝያን ጊዜዉ ኮሌጅ በዛሪዉ ማካሪሪ ዩንቨርስቲ እንዲሁም በታላቅዋ ብሪታንያ በሊድስ ዩኒቨርሲቲ የከፍተኛ ትምህርታቸዉን ተከታትለዋል።
ንጉጊ 30 ዓመት እንደሞላቸዉ በዓለም ታዋቂ ያደረጋቸዉን «The Black Hermit» የተሰኘዉን ሥነ-ጽሁፍ በጎርጎረሳዉያኑ 1962 በዩጋናዳ የነጻነት በዓላት ላይ አቅርቧል። በመቀጠል በጎርጎረሳዉያኑ 1964 «Weep Not, Child» የተሰኘዉን ልብ ወለድ አሳትመዋል። ይህ ልብወለድ በምስራቅ አፍሪቃ ደራሲ ለመጀመሪያ ጊዜ በእንጊሊዘኛ የታተመ እንደነበር ተዘግቧል።
የአፍ መፍቻ ቋንቋ ኃይል
ንጉጊ ዋ ቲዮንጎ በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ጽሑፍ መምህር ሳሉ መዲና ናይሮቢ አቅራቢያ ላሚገኝ ብሔራዊ ቲያትር፤ ከአንዲት ኬንያዊት ፀሐፊ ጋር ለተዉኔት የሚሆን ጽሑፍ እንዲያቀርቡ ተጠይቀዉ፤ ድራማዉን በየትኛው ቋንቋ ቢጽፉ ተስማሚ እንደሚሆን አሰቡ። ኋላ ላይ ግን ንጉጊ ዋ ቲዮንጎ «ድራማውን በየትኛው ቋንቋ እንደምንጽፍ ራሳችንን መጠየቃችን በራሱ ከትውልድ አገራችን ምን ያህል መራቃችንን ብዙ ያሳብቃል» ሲሉ መናገራቸዉ ተጠቅሷል። ሁለቱ የሥነ-ጽሑፍ ባለሞያዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸዉ በኩኩዩ እጅግ ተወዳጅነትን ያገኘን እና በብዙ ኬንያዉያን ዘንድ ታዋቂ ያደረጋቸዉን «በፈለኩ ጊዜ አገባለሁ» የተሰኘዉን ተዉኔት ጻፉ።
በመጸዳጃ ቤት ወረቀት ላይ ልብ ወለድ
በህዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን ያገኘዉ ትያትር በናይሮቢ ያለውን መንግስት ግን ቅር አሰኝቶታል። የንጉጊ ሂሳዊ አስተሳሰብ እና ያሳደረዉ ተፅዕኖ ትያትሩ ከዘጠነኛ ጊዜ እይታ በኋላ እንዳይቀርብ ተከልክሏል። የተዉኔቱ ደራስያን እነ ንጉጊም ለአንድ ዓመት ዘብጥያ ወርደዋል።
ንጉጊ በመታሰራቸዉ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ለመጻፍ ያላቸዉን ቁርጠኝነት አጠናክሮለታል። ገና በእስር ቤት ሳሉ፣ «Devil on the Cross » የሚለውን የመጀመሪያውን ልብ ወለድ ለአንባቢ አብቅተዋል። ንጉጊ ልብወለዱን የጻፉት እስር ቤት ዉስጥ ባገኙት መጽዳጃ ቤት ወረቀት ላይ ነበር። ከዓመታት በኋላ ስለዚህ ጽሑፍ ሲናገሩ፤ «እስር ቤት ሳለን ለመፀዳጃ ቤት መጠቀምያ የሚሰጠን ወረቀት እንደቅጣት ሆኖ በጣም ጠንካራ በመሆኑ፤ ወረቀቱ ለኔ ሥነ-ጽሑፍ መከተብያ በጣም ረድቶኛል ሲሉ ተናግረዋል።ህጸጽን በሽሙጥ፤ በእፀገነት ከበደ
የቅኝ ግዛት ዘመን ውርስ
በኬንያ ሥነ-ጽሑፍን በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማግኘት እስከዚያ ጊዜ ድረስ ያልተለመደ ነበር። ንጉጊ ከእንግሊዘኛ ሥነ ጽሑፍ ወጥተዉ ወደ እናት ቋንቋቸዉ መግባታቸዉ በራሱ ክርክር አስነስቶም ነበር። ደራሲ ንጉጊ ዋ ቲዮንጎ ግን የአፍሪቃ ቅኝ ገዥዎች ቋንቋዎች የቅኝ ግዛት ጭቆና ምልክት ናቸዉ የሚል አቋምም ነበራቸዉ። ንኑጊ በጎርጎረሳዉያኑ 1986 ዓ.ም ይፋ ባደረጉት ጽሑፍ «በክፍል ውስጥ የሥነ-ልቦና ጥቃት» ከተፈጸመ በኋላ በጦር ሜዳ ላይ አካላዊ ጥቃትን እንዳደረሰ ጽፈዋል። በወቅቱ ንጉጊ የፕሬዚዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይ መንግስት ሊገድላቸው ማቀዱን ከሰሙ በኋላ ግን ወደ እንግሊዝ ተሰደዱ።
በኬንያ የወደፊት ተስፋ የለም
ንጉጊ ዋ ቲዮንጎ ለ22 ዓመታት እንጊሊዝ ዉስጥ በስደት ቆይቷል። የቀድሞዉ የኬንያ ፕሬዚዳንት አራፕ ሞይ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ ንጉጊ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2004 ወደ ሃገራቸዉ ወደ ኬንያ ተመለሱ። ንጉጊ ሃገራቸዉ ሲገቡ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ በደስታ ተቀብሎዋቸዋል። ይሁንና ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ንጉጊ ዋ ቲዮንጎ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች መኖሪያ ቤታቸዉን ሰብረዉ ገብተዉ ደራሲዉን አሰቃይተዋቸዋል፤ ሚስታቸዉንም ደፍረዋል።
ንጉጊ በህይወታቸዉ የመጨረሻዎቹን አስርት ዓመታት ያሳለፉት በዩናይትድ ስቴትስ ሲሆን በተለያዩ የመምህርነት ፈርጆች ተሰማርተዉ አገልግለዋል። የንጉጊ ልብ ወለዶች ወደ 30 በላይ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል። በኩኩዩ ቋንቋ የተፃፉት አብዛኛዎቹ ስራዎቻቸዉ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎሙት በራሳቸዉ በንጉጊ ነዉ።
በጎርጎረሳዉያኑ 2006 «Wizard of the Crow» ሲል የሰየሙት እና ስለ ሙሰኛ ገዥዎች በፌዝ የከተቡት የንጉጊ ልቦለድ፤ በዓለም አቀፍ እውቅናን አስገኝቶላቸዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሥነ-ጽሑፍ ለኖቤል ሽልማት ለተደጋጋሚ ጊዜ ታጭተዋል። ከዚህ ሌላ ታዋቂዉ ኬንያዊ ደራሲ ንጉጊ ዋ ቲዮንጎ ጀርመን ከባይሮይት ዩኒቨርሲቲ እና በአሜሪካ ከዬል ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተቀብለዋል። የሥነ-ጽሑፍ ኖቤል ሽልማትና የኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ሐብት
በህይወቱ ሙሉ የምዕራባውያንን የባህል የበላይነት ሲዋጉ የነበሩት ንጉጊ ዋ ቲዮንጎ የመጨረሻዎቹን የህይወታቸዉን ዘመናት የምዕራባውያንን የባህል የበላይነት ባሳየችው በዩናይትድ ስቴትስ ማሳለፉፋቸዉ ግን ግራ የሚያጋባ ይመስላል። የዘጠኝ ልጆች አባቱ ንጉጊ ዋ ቲዮንጎ 87 ዓመታቸዉ ነበር።
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ