«ንግስተ ሳባ የመጀመሪያዋ ዲፕሎማት ናት» የእስራኤል አምባሳደር በኢትዮጵያ
ዓርብ፣ የካቲት 14 2017
የዚህ ሳምንት የዶቼ ቬለ የአንድ ለአንድ ዝግጅት እንግዳ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ዶክተር አብርሃም ንጉሴ ፤ትውልድ እና እድገታቸው በአሁኑ የአማራ ክልል በቀድሞው የጎንደር ክፍለ ሀገር፤ ጎርጎራ ጣና ሀይቅ አካባቢ በምትኝ ፈንታይ በተባለች የገጠር ቀበሌ ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ጀንዳይ በተባለ በአካባቢው በሚገኝ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፤የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በጎንደር ፋሲለደስ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታኅለዋል።
በጎርጎሪያኑ 1985 ዓ/ም ወደ እስራኤል ያመሩት ዶክተር አብርሃም ንጉሴ የከፍተኛ ተቋም ትምህርታቸውን በህግ እና በማህበራዊ አገልግሎት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በህብሪው ዩንቨርሲቲ፤ ሌላ ሁለተኛ ዲግሪ በቢዝነስ አስተዳደር በአወስትራሊያ ስዊንበርን ዩንቨርሲቲ፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በትምህርት በብሪታንያ ሳሲክስ ዩንቨርስቲ ተከታትለዋል።
በእስራኤል ፖለቲካ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች በንቃት የሚሳተፉት ዶክተር አብርሃም ከ2015 እስከ 2019 «ክኔሰት»ተብሎ በሚጠራው የእስራኤል ፓርላማ አባል የነበሩ ሲሆን፤ከዚህ ቀደም ብሎም የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪ ሆነው ሰርተዋል።
ወደ ፖለቲካ ከመግባታቸው በፊትም የፅዮን የደቡብ ክንፍ /South wing to Zion/ የተባለ የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላውያን የመብት ተሟጋች ድርጅት መስራች እና ሊቀ መንበር ነበሩ። በዚህ ወቅትም፤ኢትዮጵያውያን ቤተ እስራኤሎች እኩል የትምህርት እድል እንዲያገኙ ለቤተ እስራኤላውያን መብትና እኩልነት እንዲሁም ለማህበራዊ ፍትህም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
ከነሀሴ 2024 ጀምሮ ደግሞ የእስራኤል አምሳደር ሆነው ተወልደው ወደ አደጉባት ኢትዮጵያ መጥተዋል። «ንግስተ ሳባ ወደ ኢየሩሳሌም የሄደች የመጀመሪዋ ዲፕሎማት ናት»የሚሉት ዶክተር አብርሃም፤ አምሳደር ሆነው ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ይህንን የእስራኤል እና የኢትዮጵያ የብዙ አመታት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማጠናከር ለእሳቸው ትልቅ እድል መሆኑን ገልፀዋል።
አምሳደር አብርሃም ንጉሴ ከዶቼቤለ ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለሁለቱ ሀገሮች ሁለንተናዊ ግንኙነት፤በቆይታቸው በኢትዮጵያ ሊሰሩ ስላቀዷቸው ጉዳዮች፣ በእስራኤል ሀገር ስለሚገኙ ቤተእስራኤላውያን አኗኗር፣ስለእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ሙሉ ቃለመጠይቁን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።
ፀሐይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ