ሰብዓዊ መብቶችን በኪነ - ጥበብ የማስተማር ጥረት
ቅዳሜ፣ ኅዳር 15 2016ወጣት ሊያ ደስታ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የ አምስተኛ አመት የሕግ ተማሪ እና በዩኒቨርሲቲው የተቋቋመው የሰብዓዊ መብት ክበብ ተሳታፊ ናት። የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል በየ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያቋቋማቸው ክበቦች ላይ ከሚሳተፉ ሴቶች አንዷ የሆነቸው ወጣቷ ሴቶች ላይ ከተለያየ አቅጣጫ የመብት ጥሰት ከሚፈፀምባት ሀገር ውስጥ ስለ መብት በምን መልኩ መቆርቆርን እና ጥብቅና መቆምን እንደምትሰራ ተናግራለች። "የሴቶች መብትን በተመለከተ ፣ የአካል ጉዳተኞችን መብት በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንሠራለን" በማለት ገልጻለች።
ሌላኛው ወጣት ኢዮብ ሙሉጌታ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአምስተኛ አመት የሕግ ተማሪ እና የዩኒቨርሲቲውን የሰብዓዊ መብት ክበብ የሚመራ ነው። መብቶች የሚታወቁበትን አማራጭ መፍጠር ለመብቶች መከበር ጅምር መሆኑን በማመን እዚህ ውስጥ እንደሚሳተፍ ገልጾ የሰብዓዊ መብት መቆርቆር ላይ ያተኮረው በዚሁ ምክንያት መሆኑን ተናግሯል።
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያ ከዛሬ ጀምሮ እስከ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ቀን መታሰቢያ ታህሳስ 10 ድረስ የሚቆየውን የሴቶች መብት ጥሰት ማስቆምን በሚያቀነቅነው አለም አቀፍ ክብረ በዓል ላይ በየ ዩኒቨርሲቲው ያሰባሰባችኋቸው የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ ተማሪዎች ምን አበረከቱ የሚለውን ይመልሳሉ።
"እዛው ዩኒቨርሲቱዎቻቸው ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች እንዲቆሙ ፣ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብም ለሴቶች መብት መከበር ዘብ እንዲቆም ቅስቀሳ ያደርጋሉ" ብለዋል።
ሲቪክ ድርጅቶችና ምሁራን ለዘላቂ ሰላም መስፈን ምን ሠሩ?
በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚፈፀመው ጥቃቶች በአለም አቀፍ ደረጃም ይሁን በኢትዮጵያ እጅግ የተስፋፋ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው። የሴቶችን መብት ጥሰት በኪነ ጥበብ መልኩ ለማሳየት የተደረገው ጥረት መልካም ውጤት ያለው በመሆኑ ድጋፍ ማድረጋቸውን በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ሽቴፈን ዐውር ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ባለፉት ጥቂት አመታት ሴቶች በጦርነት ምክንያት ለከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጋልጠዋል፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ተደፍረዋል፣ ደብዛቸው የጠፉ ተጠላፊዎች ታይተዋል፣ የግድያ እና የአካል መጉደል ቀጥተኛ ሰለባም ሆነዋል።
ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ