1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«አልሚ ልቦች ለኢትዮጵያ» ማህበር

ዓርብ፣ ሐምሌ 12 2016

«አልሚ ልቦች ለኢትዮጵያ» ከቅርብ አመታት ወዲህ ጀርመን ውስጥ የተመሰረተ ማህበር ነው። ማህበሩ በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ስለ ጀርመን ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ እና ማኅበራዊ ኑሮ ማስተማር አንዱ አላማው አድርጎ እየሰራ እንደሆነ ይናገራል።

 Grünes Herz für Äthiopien e.V.
«አልሚ ልቦች ለኢትዮጵያ» ማህበር አባላት እና ተሳታፊዎችምስል Grünes Herz für Äthiopien e.V.

«አልሚ ልቦች ለኢትዮጵያ» ማህበር

This browser does not support the audio element.

ሰሞኑን በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ በተለያዩ የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተለይ በትምህርት እና በስራ ዘርፍ ላይ ለመወያየት ፣ ተሞክሮዋቸውንም ለመለዋወጥ ተሰባስበው ነበር። ጤና ይስጥልኝ  የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ተከታታዮቻችን። ሰዎች ሀሳባቸውን የሚለዋወጡበት መድረክ ካገኙ ብዙ እውቀት መለዋወጥ ይችላሉ።  እንደዚህ አይነት መድረኮችን ማመቻቸት ይመስላል  የ« አልሚ ልቦች ለኢትዮጵያ» ማህበር አላማ።  « በዚህ በጀርመን ሀገር ለመንቀሳቀስ የሚያስችሉን እውቅና ያገኘንባቸው ብዙ ዘርፎች አሉ።» ይላል  የማህበሩ ሰብሳቢ እና መስራች አባል ስምኦን መኮንን።  «በዋናነት ለማህበረሰባችን ማህበራዊ ድጋፍ መስጠት ነው። ትምህርት ፣ በተደራጀ መልኩ ለጀርመን ማህበረሰብ ባህላችንን የምናስተዋውቅበት ነገሮች መፍጠር ነው። ከዛ በተጨማሪ የሙያ ልውውጦች ፣ ልምድ ያላቸው ሰዎች ወደ ሀገር ቤት ሄደው ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት ሁኔታ መፍጠር ነው።»

«አልሚ ልቦች ለኢትዮጵያ» ለምን ተባለ?

እጎአ ከ 2022 ዓ ም አንስቶ በጀርመን ሀገር ህጋዊ እውቅና ያገኘው ይኼው ማህበር  በጀርመንኛ Grünes Herz für Äthiopien የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል። «ይህም ስም መረጣ ረዥም ጊዜ ወስዶብናል» ይላል ስምኦን የማህበሩን መጠሪያ ሲያንራራልን « አረንጓዴ የሚለው ዘላቂነት ያለው ፣ ተፈጥሮ የሚለውን ለማገናኘት ነው።  ልብ የሚለው ደግሞ ሰብዓዊነት፣ መረዳዳት ፣ መደጋጋፍን ለማሳየት ነው። ለልማት እና ለትብብር የተሰበሰቡ ልቦች በዚህ ማህበር ውስጥ ማሰባበብ እንፈልጋለን ከሚል እሳቤ አንፃር « አልሚ ልቦች ለኢትዮጵያ» ብለንዋል። ኢትዮጵያ የሚለውን የጨመርንበት ደግሞ ኢትዮጵያ ላይ መስራት ስለምንፈልግ ነው። » የሚለው ስምኦን ማህበሩ የቀረፃቸው በርካታ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም በአሁኑ ሰዓት እዚሁ ጀርመን የሚገኘውን ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ መርዳታ እና ማሰባሰብ ቀዳሚ ትኩረታቸው እንደሆነም ገልፆልናል። 

« ነፃ ትምህርት የት እንደሚሰጥ የማያውቁ ብዙ አሉ»

ወጣት ሰለሞን መንገሻ ማህበሩ ባለፈው ቅዳሜ ያዘጋጃቸውን መድረክ ጨምሮ ሁለት ዝግጅቶች ላይ ተካፍሏል።  የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ የሆነው ሰለሞን ጀርመን ሀገር ከመጣ አራት አመት ሆኖታል። ይሁንና ወደዚህ ከመጣ አንስቶ ሰዎች የሚሰባሰቡበት እና ተሞክሯቸውን የሚለዋወጡበት ጠንካራ መድረክ እስካሁን ገጥሞት አያውቅም። «ይኼ ለእኔ የመጀመሪያው ነው። እንደዚህ አይነት ነገሮች ባለመኖራቸው ቋንቋውን ለመማር ምን አይነት መንገድ መሄድ እንዳለባቸው የማያውቁ ብዙ ሰዎች አሉ።  ከፍለው መማር አይችሉም ገንዘብ ያላቸውም ። ነፃ ትምህርት ደግሞ የት እንደሚሰጥ አያውቁም። ስለዚህ እንደዚህ መሰባሰቡ እና የኔት ዎርኪንግ ዝግጅቶች በጣም ጠቃሚ ናቸው። እኔም ያለፍኩባቸውን በተለይም ቋንቋን በተመለከተ ያለፍኩባቸውን መንገዶች ማካፈል ችያለሁ። እና አሁን እኔም ከተሳታፊነት አስተዋፅዎ ወደማድረጉ የመሄድ ሀሳብ አለኝ። »

«አልሚ ልቦች ለኢትዮጵያ» ማህበር ሁለተኛ ዝግጅትምስል Grünes Herz für Äthiopien e.V.

የማህበሩ አባላት ተሞክሮ

ከእቅድ አልፋ በተግባር ወደ ስራ የገባችው ሌላዋ ወጣት ነፃነት ዘላለም ትባላለች። «ማህበሩን በቅርቡ ነው የተቀላቀልኩት» የምትለው  የቢዝነዝ ኢንፎርሜሽን ተማሪ በአሁኑ ሰዓት ማህበሩ የቀረፃቸውን ፕሮጀክቶች ለማስፈፀም በአስተባባሪነት እያገለገለች እንደሆነ ገልፃልናለች።  ከአምስተኛ ክፍል አንስቶ ጀርመን ሀገር የተማረችው ነፃነት በብዛት ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት የጀርመን ከተማ እንደማደጓ የታዘበችው እና ቢሻሻል የምትለው ነገር አለ። « መጀመሪያ ላይ ቋንቋ ላይ አተኩሮ መስራት ያስፈልጋል። በተለይ ለትምህርት የሚመጡት የሀገሩን ቋንቋ ቢችሉ ብዙ ነገሮችን ማድረግ ይቻላል። ብዙ ሰው እዚህ ሀገር ለትምህርት ሲመጣ እዚህ ሀገር አልኖርበትም በሚል ቋንቋውን ችላ የማለት ሁኔታ ይታያል እና ቋንቋ ላይ ብንሰራ እላለው። »
ነፃነት በተለያዩ የጀርመን ትምህርት  ተቋሟት ውስጥ መሟሯ ረድቷታል። የማህበሩ ሰብሳሲ ስምኦንም ቢሆን ጀርመን ሀገር ሲኖር 15 ዓመት ሆኖታል። እሱም የተለያዩ የትምህርት ተቋማትንም ጎብኝቷል። «እዚሁ ጀርመን ሀገር ሀይ ስኩል ጨርሼ የሙያ ትምህርት ተምሬያለሁ።  ዩንቨርስቲ ገብቼም ቢዝነስ ኢንፎርማቲክ ተምሬ በዚሁ ሙያ እየሰራሁ ነው። እኛ በመጣንባት ሰዓት ከፍተኛ የሆነ የመረጃ እጥረት ነበር። እና ያም ቁጭት ነበረብኝ። ከዛም በፊት ባለፉት አራት አመታት Dan Tube በሚል ዩ ቲውብ ላይ ጀርመንኛ ሳስተምር ቆይቼያለሁ። »

የኢትዮጵያውያን ሴቶች ማህበር በጀርመን

በተለያየ የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተለይ በትምህርት እና የስራ ተሞክሮዋቸው ላይ ተወያይተዋል።ምስል Grünes Herz für Äthiopien e.V.

አንዳንድ ጊዜ ጥሩ አላማ ይዘው የተነሱ ማህበራት የሆነ ጊዜ የማህበሩ የጀርባ አጥንት የሆኑ በጎ ፍቃደኛ አባላት በመዳከማቸው ሌላ ጊዜ ደግሞ በማህበር አባላት መካከል በሚፈጠር የብሔር ወይም የኃይማኖት ክፍፍል በአጭሩ ሲበተኑ ይስተዋላል።   ይህ እንዳይሆን እና ዘላቂነት እንዲኖረው የአባል ቁጥርን መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በአንድ ጊዜ ከመጨመር ይልቅ እንደየ ፕሮጀክቱ አስፈላጊነት እና ያለው ስራ ፀባይ የአባላቱን ቁጥር ለመጨመር መወሰናቸውን ስምኦን ገልፆልናል።  በማህበሩ ዝግጅቶች ላይ ተሳታፊ የነበረው ሰለሞን እንደገለፀልን በታዳሚው ዘንድ ምንም አይነት ክፍፍል ያልነበረበት ይልቁንስ በስራ እና ትምህርት ላይ ያተኮሩ ውይይቶች እንደነበሩ ነው። «ውይይቱ ፕሮፌሽናል በሆነ መንገድ ነው። የቋንቋ ትምህርት ፣ የትምህርት እድልን በሚመለከት ወይም በተማሩበት ሙያ ስራ ፈልጎ ማግኘት ላይ ይሆናል። እነዚህ የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ነው እንጂ የሚወሩት ሌሎች ጉዳዮች ተነስተው አያውቅም። ማንም ሰው ምንም አይነት ሐይማኖትም ይኑረው ብሔር መረጃ ማግኘት ወይም መረጃ ማካፈል ይችላል »

ማህበሩን ማግኘት የሚፈልጉ ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?

የማህበሩ የፕሮጀክት አስተባባሪ ነፃነት የተለያዩ አማራጮች አሉ ትላለች። « የራሳችን ድረ ገፅ አለን Grünes Herz für Äthiopien የሚል። ከዚህ በተጨማሪ  የቴሌግራም ቻናል አለን። እኛ ብቻ ሳንሆን ሰዎች ጠቃሚ ነው ብለው የሚሉትን መረጃ የሚያጋሩበት። እሱም Grünes Herz für Äthiopien ይሰኛል።»

 

ልደት አበበ

ታምራት ዲንሳ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW