1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አማራና ትግራይ የሚወዛገቡባቸው የራያ አካባቢዎች ሰሞናዊ ሁኔታ

ሰኞ፣ ሰኔ 3 2016

አማራና ትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱባቸው የራያ አላማጣ አካባቢዎች “የትግራይ ታጣቂዎች” “ግድያና እንግልት እየፈፀሙብን ነው” ሲሉ ነዋሪዎች ተናገሩ፣ ባለፈው ቅዳሜ አንድ ከተማዋ ነዋሪ ወጣት በታጣቂዎች መገደሉን ተከትሎ በአላማጣ ከተማ ግድውን የሚያወግዝና የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲከበር የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂድዋል፡፡

ራያ አላማጣ
ራያ አላማጣምስል Fikru Eshsiebel

አማራና ትግራይ የሚወዛገቡባቸው የራያ አካባቢዎች ሰሞናዊ ሁኔታ

This browser does not support the audio element.

አማራና ትግራይ የሚወዛገቡባቸው የራያ አካባቢዎች ሰሞናዊ ሁኔታ


አማራና ትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱባቸው የራያ አላማጣ አካባቢዎች “የትግራይ ታጣቂዎች” “ግድያና እንግልት እየፈፀሙብን ነው” ሲሉ ነዋሪዎች ተናገሩ፣ ባለፈው ቅዳሜ አንድ ከተማዋ ነዋሪ ወጣት በታጣቂዎች መገደሉን ተከትሎ ትናንት በአላማጣ ከተማ ግድውን የሚያወግዝና የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲከበር የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ መካሄዱን ነዋሪዎቹ  አመልክተዋል፡፡ የቀረበውን ስሞታ በተመለከተ ከትግራይ ክልል ባለስልጣናት ማረጋገጫም ሆነ ማስተባባያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
የአማራና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ ከሚያነሱባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ራያ አላማጣና አካባቢው ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ እንደገና አለመረጋጋቶች ተፈጥረዋል፣ የወሎ አማራ የወሰንና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላት “ከትግራይ ተሻግረው የመጡ” ያሏቸው ታጣቂዎች ወደ ራያ አላማጣና አካባቢው በኃይል በመግባት አካባቢውን እንደተቆጣጠሩና ግፍና በደል እየፈፀሙ ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ገልፀዋል፣ የትግራይ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ረዳኢ ኃለፎም ከዚህ በፊት ለዶይቼ ቬሌ በሰጡት መግለጫ ደግሞ አካባቢዎቹ የትግራይ ክልል አካል ስለሆኑ የትግራይ ታጣቂዎች ወደ አማራ ክልል ዘልቀው አልገቡም የሚል መከራከሪያ አላቸው፡፡
ያም ሆነ ይህ ግንበራያ አላማጣ፣ በራያ ባላና ወፍላበተባሉ ወረዳዎች ነዋሪው በትግራይ ታጣቂዎች በደል እየተፈፀመበት ነው ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልፃሉ፣
አንድ የአላማጣ ከተማ ነዋሪ እንዳሉት ባለፈው ቅዳሜ አንድ የከተማዋ ሰላመዊ ወጣት መገደሉንና ግድያውን ተከትሎ ትናንትና በከተማዋ የተቃውሞ ሰልፍ መካሄዱን አስረድተዋል፡፡
“...ሰሞኑን አንዲት እናት ጥቃት ደርሶባት ወደ ከፍተኛ የህክምና ጣቢያ ተልካለች፣ ትናንት ደግሞ የመብራት ኃይል ሰራተኛ ወጣት የተበላሸ መብራት ጥገና ሄዶ ባለበት ነው በዱላ ደብድበው ካደከሙት በኋላ መጨረሻ ላይ ተኩሰው ገድለውታል፡፡ ትናንትና ግድያውን በመቃወም በአላማጣ ከተማ ሰልፍ ተካሂዷል፣ የታጠቁ ኃሎችን አስወጡልን፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት ይከበር፣ ማንነታችን ይከበር የሚሉ መልዕክቶች ተላልፈዋል፡፡” ብለዋል፡፡
ሌላ የአላማጣ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው ነገ የሚሰጠውን የ8ኛ ክፍል ፈተና ለማደናቀፍና በከተማዋ ያሉ ጽህፈት ቤቶችን በኃይል ለመፈት ሙከራ ሲያደርጉ ዛሬ ጠዋት ታጣቂዎቹ ከወጣቶች ጋር በመጋጨታቸው ታጣቂዎቹ ተኩስ መክፈታቸውንና አንድ ሰው ማቁሰላቸውን አብራርተዋል፣ ሆኖም የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ሁኔታው እንዲረጋጋ አድርገዋል ብለዋል፡፡
“የ6ኛና የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ተፈታኝ ፈተናዎች ነገ ፈተና እንደሚጀምሩ ተነግሯል፣ ያንን ምክንያት በማድረግ ታጣቂዎቹ ኃላቸውን አጠናክረው ዛሬ የከተማውን ትምህርት ቤቶች በሙሉ ይዘው አድረዋል፣ ዛሬ ጠዋት ደግሞ ወደ ቀበሌ 3 በመሄድ ለመክፈት ሲሞክሩ ወጣቱ አትከፍቱም በሚል በተነሳ አለመግብብት አንድ ወጣት በጥይት ተመትቶ ቆስሏል፣ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ችግሩ ቶሎ እንዲበርድ አድርገዋል፣ ትምህርት ቤቶችን ግን እስከአሁን አለቀቋቸውም፡፡ ” ነው ያሉት፡፡
የራያ አላማጣ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉጌታ አስማማው ስለጉዳዩ ተጠይቀው እንዳሉት የትግራይ ታጣቂዎች 6 ወረዳዎችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው የዘረፋ ሥራ እየሰሩ ነው ሲሉ ይከስሳሉ፡፡
“በኮረምም ሶስት ወረዳዎች፣ በራያም ሶስት ወረዳዎች ተቆጣጥረውታል፣ የበረሀ ሰብልም ሳቀር ዘረፋም ተያይዘውታል፣  ሰዎችንም እፈኑ ይወስዳሉ፣ ይደበድባሉ ያስራሉ፣   የአማራ ክልል መንግስት ከፌደራል መንግስት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ እየተነጋገረ ነው፣ እኛም በቅርቡ ከፌደራልና ከክልል ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረንበታል፣ ግን ጠብቁ እየተባልን ነው፡፡”
የወፍላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍሰሐ ሞላ በስልክ እንደተናገሩት ደግሞ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ በተፈጠረው የሰላም እጦት በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ መምህራንና ሌሎችም የማንነት ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች ደግሞ እየተያዙ ወደማይታወቅ ቦታ እተወሰዱ እየታሰሩ ነው ብለዋል፡፡
አክለውም፣ “በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ ግማሹ ወደ ሰቆጣ፣ ግማሹ ወደ ቆቦ ወጥቷል፣ ኮረም ከተማን ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ናቸው እየተቆጣጠሩ ያሉት፣ የገጠር ቀበሌዎችን ግን ሰብረው ገብተዋል፣ የሚቃወም ሰው ሲኖር ደግሞ እፈኑ እያሰሩ ማይጨው ድረስ እየወሰዱ እያሰሯቸው ነው፡፡የታፈኑ ሰዎች አሉ ስንል በስም ዝርዝር ማስቀመጥ እንችላለን፡፡” ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡
ከራያ አላማጣ ነዋሪዎች ስለቀረበው ስሞታ ማስተባቤም ሆነ ማረጋገጫ ለማግኘት ለትግራይ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ረዳኢ ኃለፎምና ለደቡባዊ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀፍቱ ኪሮስ የእጅ ስልክ ብደውልም እንደሁል ጊዜው ሁለቱም ስልካቸው አይመልስም፡፡


ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ 

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW