1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አማራ ክልል የውይይትና ድርድር ጥሪ ቀረበ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 18 2016

አንድ ዓመት ግድም የተቃረበው የአማራ ክልል የፀጥታ መታወክ በውይይትና በድርድር እንዲቋጭ መንግስት በድጋሚ ጥሪ አቀረበ ። ከፍተኛ የፌደራል፣ የክልልና የዞን የመንግስት አመራር በተገኙበት ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ትናንት የሰላም ጉባኤ መጀመሩም ተገልጧል ።

Äthiopien | Amhara Regionalrat
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የሰላም ጉባኤ በባሕር ዳር ከተማ ተጀመረ

This browser does not support the audio element.

አንድ ዓመት ግድም የተቃረበው የአማራ ክልል የፀጥታ መታወክ በውይይትና በድርድር እንዲቋጭ መንግስት በድጋሚ ጥሪ አቀረበ ። ከፍተኛ የፌደራል፣ የክልልና የዞን የመንግስት አመራር በተገኙበት ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ትናንት የሰላም ጉባኤ  መጀመሩም ተገልጧል ።

በአማራ ክልል  የተፈጠረውን የሰላም እጦት በሰላማዊ መንገድ መፍታት ያስችላል የተባለ የሰላም ኮንፈረንስ በባህር ዳር ከተማ ትናንት ተጀምሯል፡፡ የመከላከያ ከፍተኛ የጦር አዘዦች፣ የክልልና የዞን ባለስልጣናት፣ የሐይማኖት አባቶችና የሐገር ሽማግሌዎች የሚሳተፉበት ይህ ኮንፈረንስ  ክልሉን ወደ ሰላም ሊያመጡ የሚችሉ ሀሳቦች ይቀርቡበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ "ሁሉም ነገሮች ከጠመንጃ በመለስ" እንዲፈቱ ተወያይዎቹ ትኩረት እንዲያደርጉ ነው በመክፈቻ ንግግራቸው ያሳሰቡት፡፡

"ሁሉም ነገሮች  ከብረት (ከጠብመንጃ) በመለስ በውይይት፣ በድርድር፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ ህዝብና አገርን በሚያሳድግ አቅጣጫ መነጋገር አለብን፣ መወያየት አለብን የሚል አቋም መያዝ አለበት፤ መንግስት ጭምር ህን አቅታጫ እንዲከተል፣ በተጨባጭ ውጊያ እያደረገ ያለውም ኃይል ላይ ከፍተኛ ተፅ㙀ኖ በማድረግ ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጣ የሚያደርግ አካሄድ ውይይት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ " ብለዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት በክልሉ ነዋሪዎች ነፃ እንቅስቃሴና ሌሎች ከፍተኛ ተፀዕኖ ያሏቸውን ሁኔታዎች ዘርዝረዋል፡፡

"ከጎንደር አዲስ አበባ መሄድ ቅንጦት ሆኗል፣ ከአዲስ አበባ ባሕር ዳር መምጣት ቅንጦት ሆኗል፣ ያላቸው በአውሮፕላን ነው የሚሄዱ፣ የእኔና የእናንተ ቤተሰቦች በአውሮፕላን መሄድ አይችሉም (ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል)፣ ተማሪዎች ትምህርታቸውን መማር አልቻሉም፣ በርካታ ተማሪዎች ለክልላዊና አገራዊ ፈተናዎች መቀመጥ አልቻሉም ባለው  የፀጥታ መታወክ ምክንያት እየተማሩ ያሉ ተማሪዎችም አጥጋቢ ውጤት ለማምጣት እየተቸገሩ ነው፣ በርካታ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እያቋረጡ ነው፣ መንግስት የልማት ስራዎችን መስራት አልቻልም፣ ህዝቡ ችግር ውስጥ ነው ያለው፡፡" ሲሉ ገልጠዋል፡፡

በኢኮኖሚው ዘርፍ ላይም ጦርነቱ ያስከተለውን ችግር አቶ አገኘሁ ሲያብራሩ፣ "የአማራ ክልል 35 ከመቶና ከዚያ በላይ የሚሆነውን የአገሪቱን የሰብል ምርት የሚሸፍን ሆኖ ሳለ፣ ዛሬ ማምረት አልቻለም፣ ማዳበሪያ ማሰራጨት አልቻለም፣ ምርጥ ዘር ማሰራጨት አልቻልም፣ አበዳሪ ተቋማት ብድር መሰብሰብ አልቻሉም፣ ባንኮች አገልግሎት መስጠት አልቻሉም፣ ነጋዴው ሰርቶ፣ ነግዶ ራሱን ማሻሻል አልቻለም፡፡ " ብለዋል፡፡

የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገርምስል Alemnew Mekonnen/DW

መገዳደሉና፣ በጠላትነት መፈላለጉ ከበቂ በላይ በመሆኑ ሁሉም ኃይሎች ለድርድር፣ ለውይይትና ለንግግር ራሳቸውን ያዘጋጁ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፣ የክልሉ መንግስትም ሆነ የፌደራሉ መንግስት ለድርድርና ለውይይት ዝግጁ መሆኑንም አቶ አገኘሁ አመልክተዋል፡፡

" ይህንን መገዳደል ካላስቆምን በስተቀር ክልላችን ወደፊት መራመድ አይችልም፣ እስኪበቃን ተገዳድለናል፣ ስለዚህ አሁን ይብቃን፣ መፍትሔው ንግግር ነው፣ መነጋገር ነው፣ መከባበር ነው፣ ሌለው አካል ብቻ  ችግር አለበት እልኩ አይደለም፣ እኔ ችግር የለብኝም እያልሁም አይደለም፣ እኔም ሁላችንም የችግሩ አካል ነን፣ ስለዚህ ይብቃን፣ ህዝባችን ከችግር እናውጣው፣ አሁንም መንግስታችንና ፓርቲያችን የሰላም ጥሪ ያቀርባል፣ ለመነጋገር፣ ለመወያየት ለመደራደር፣ ለመመካከር የክልሉም ሆነ የፌደራሉ መንግስት ዝግጁ ነው፡፡"

በአማራ ክልል የነበረውን የልዩ ኃይል አደረጃጀት መፍረስ ተከትሎ በክልሉ የተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ እስካሁን ይህ ነው የሚባል መፍትሔ ሳያገኝ  ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳቶችን እያስከተለ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

በአማራ ክልል ከተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ በክልሉ ሐምሌ 2015 ዓ ም ለ6 ወራት የታወጀውና ጥር 2016 ዓ ም ላይ እንደገና ለ4 ወራት የተራዘመው የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ ጊዜው የተጠናቀቀ ቢሆንም መንግስት ጉዳዩን በተመለከተ እስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW