1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችኢትዮጵያ

ተፈናቃዮችን ለመመለስ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች

ዓርብ፣ ጥር 24 2016

በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመመለስ የኦሮሚያና የአማራ ክልል መንግሥታት በጋራ እየሠሩ መሆናቸውን የአማራ ክልል መንግሥት አስታወቀ። ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጣ ኮሚቴ በምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ጉብኝት ያደረገ ሲሆን አንዳንድ ተፈናቃዮች አስተማማኝ ሰላም ካለ ወደ አደጉባቸው አካባቢዎች ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአማራ ተወላጅ ተፈናቃዮች
በአማራ ክልል በተለያዩ መጠለያ ስፍራዎች የሚገኙት ከኦሮምያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ምስል Alemenw Mekonnen/DW

ተፈናቃዮችን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለመመለስ

This browser does not support the audio element.

 

ከተፈናቃዮች፣ ከኦሮሚያና ከአማራ ክልል፣ ከሰላም ሚኒስቴርና ከኦሮሚያና ከአማራ ክልላዊ መንግሥታት ጽሕፈት ቤቶች የተዋቀሩ ኮሚቴዎች ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች በነበሩ ግጭቶች የወደሙ የተፈናቃይ መኖሪያ ቤቶችንና አካባቢዎችን እንደጎበኙ ከኮሚቴው አባላት መካከል የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ለገሠ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል። አሁን ሰላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች  ቤቶች ተጠግነው ተመላሽ ተፈናቃዮችን እየጠበቁ አንደሆነ፣ በምዕራብ ወለጋ አንድ ወረዳ፣ በምሥራቅ ወለጋ ደግሞ ስድስት ወረዳዎች ተፈናቃዮች ቅድሚያ የሚመለሱባቸው አካባቢዎች እንደሆኑ አቶ ወንድወሰን አመልክተዋል።

አቶ ወንድ ወሰን አክለውም፣ «ሄደን በጎበኘናቸው ወረዳዎች አስተማማኝ የፀጥታ ሁኔታ አለ፣ አስተማማኝ ሰላም አለ፣ ህዝቡም «ወገኖቻችን ይመለሱልን» የሚል ጥያቄ አቅርቧል፣ ከኦሮሞ ወገኖቻቸው ጋር ሚሊሺያ ሆነው ታጥቀው የሚሠሩ የአማራ ተወላጆችንም አይተናል፣ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቋል ባይባልም ቤቶች እየተጠገኑ አንደሆነ ተመልክተናል፣ አንዳንድ ቦታ ላይ ያልተቃጠሉ ተቆልፈው ያሉ የተፈናቃይ ቤቶችን አግኝተናል፣ የቡና ማሳቸው ሳይነካ እየተጠበቀላቸው ያሉ የተፈናቃይ ማሳዎችንም ሁሉ ተመልክተናል» ብለዋል።

እንዲያም ሆኖ አሁንም አንዳንድ ተፈናቃዮች የሰላም ስጋት አለባቸው፣ በዚህ ምክንያት ላለመመለስ የሚፈልጉ ተፈናቃየች አሉ ይህ እንዴት ይታያል? ተብለው የተጠየቁት ምክትል ኃላፊው፣ ዜጎች ችግር ባለበት ቦታ ሄደው ሌላ ጥቃት እንዲደርስባቸው እንደማይደረግ አመልክተዋል፣ ተፈናቃዮች የሚመለሱት አስተማማኝ ሰላም በተመለሰባቸው አካባቢዎች ብቻ እንደሚሆን አብራርተዋል።  የፀጥታው ሁኔታም እንዲቀጥል በሁለቱም ክልሎች መካከል ጠንካራ ሥራ ይከናወናል ነው ያሉት።ተፈናቃዮችን ለመመለስ በሚደረገው ሂደት የአማራ ክልል ትክክለኛ ተፈናቃይ የሆኑትን እንዲለይ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ደግሞ ተፈናቃዮች ይኖሩባቸው የነበሩ አካባቢዎችን የውኃ፣ የመንገድ የትምህርት የጤና መሠረተ ልማቶች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ እንዲያጠና ተደርጓል ብለዋል።

በአማራ ክልል በርካታ ተፈናቃዮች ከሚገኙባቸው መጠለያ ጣቢያዎች አንዱ የሆነው ጃራ የመጠለያ ስፍራ። ምስል Alamata City Youth League

ከተፈናቃዮች አንዱና ወደ ቦታው ሄደው ያለውን ሁኔታ ተከታትለው የተመለሱት አቶ ኑሩ ሁሴን እንደገለፁልን እርሳቸው ይኖሩርበት በነበረ ቶሌ ቀበሌ ጨቆርሶ ጎጥ 60 ቤቶች ተጠግነው ማየታቸውን አስረድተዋል። የአካባቢው ነዋሪዎችና አስተዳደሩም ተፈናቃዮችን መልሶ ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን «አይቻለሁ» ነው ያሉት።

በኦሮሚያ ክልል  የምዕራብ ወለጋ ቡሳ  ጎኖፋ (አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስና ጽሕፈት ቤት) መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ነፃነት ዓለማየሁ በበኩላቸው በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በዞኑ አምስት ወረዳዎች የሚገኙ በርካታ የአማራ ተዋላጆች መፈናቃላቸውን ጠቁመው፣ ሁኔታውን የሚያጠና ኮሚቴ ተቋቁሞ የደረሰበትን መደምደሚያ ካሳወቀ በኋላ በመጀመሪያ ዙር  601 አባወራ ተፈናቃዮችን በጊምቢ፣ በባቦጋምቤልና በጉሊሶ ወረዳዎች በሚገኙ ሦስት ቀበሌዎች መልሰን ለመቀበል ተዘጋጅተናል ብለዋል። እስካሁንም ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ በተለይም ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ 90 ቤቶች ተመልሰው ተገንብተዋል፣ ማቆያ ማዕከል ተዘጋጅቷል፣ 1,500 የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበሮች ተዘጋጅተዋል፣ ፕላስቲክ ሸራ፣ ምግብ ማብሰያ፣ የብርድ ልብስና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችም መቅረባቸውን ኃላፊዋ ተናግረዋል።

ከምሥራቅ ወለጋ ተፈናቅለው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙት መካከል አቶ አህመድ ኑር የተባሉ ተፋናቃይ አካባቢው ሰላም ከሆነና ቤታቸውና የእርሻ ማሳቸውን በሰላም ካገኙ ወደ ተወለዱበት ቀየ ለመመለስ በእጅጉ ይፈልጋሉ።

ከአማራ ተፈናቃዮች በከፊል ምስል Alemenw Mekonnen/DW

በአማራ ክልል ጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙና ስማቸው እንዳጠቀስ የፈለጉ ተፈናቃይም አብዛኛው ተፈናቃይ ወደ ቀየው ለመመለስ ፍላጎት ቢኖረውም የሰላሙ ሁኔታ ስጋት እንደሆነባቸው አስረድተዋል። ደብረብርሃን መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃይም የኦሮሚያና የአማራ ክልል መንግሥታት ለአካባቢው የሰላም ሁኔታ ዋስትና ከሰጡ፣ ለመመለስ ዝግጁ እንደሆኑ ገልጠዋል። ባለፉት አራት ዓመታት በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በነበሩ ግጭቶች አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ የአማራ ክልል ተወላጆች ወደ አማራ ክልል መፈናቀላቸውን በተለያዩ ጊዜዎች የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን መግለፁ የሚታወስ ነው።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW