1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራው ክልል ግጭት የመስፋፋት ስጋት

ረቡዕ፣ መስከረም 9 2016

በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት በተገቢው መንገድ እልባት ሳያገኝ ቀርቶ፤ ግጭቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ከተዛመተ መውጫው ከባድ ሊሆን እንደሚችል ተመላከተ።

ፎቶ ከማኅደር፤ በላሊበላ የአማራ ፋኖ ተዋጊ
አማራ ክልል የሚካሄደው ግጭት ወደሌሎች ክልሎች ሊስፋፋ ይችላል በሚል ስጋት አስከትሏል። ፎቶ ከማኅደር፤ በላሊበላ የአማራ ፋኖ ተዋጊ ምስል Solan Kolli/AFP/Getty Images

የአማራው ክልል ግጭት የመስፋፋት ስጋት

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት በተገቢው መንገድ እልባት ሳያገኝ ቀርቶ፤ ግጭቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ከተዛመተ መውጫው ከባድ ሊሆን እንደሚችል ተመላከተ። አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የፖለቲካ ተንታኞች ግጭቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ሳይዛመት ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል ነው ያሉት።

በአማራ ክልል ከፍተኛ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን እያስከተለ ያለው ጦርነት ከክልሉ መንግሥት ቁጥጥር ውጪ ነው በሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ በወታደራዊ እዝ መመራት ከጀመረ ቢያንስ አንድ ወር አልፎታል። በግጭቱም ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውሶች እየተከሰተ መሆኑም ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያስረዳሉ። ግጭቱአሁን አሁን ደግሞ ከክልሉም ባሻገር ወደ አጎራባች አካባቢዎች በመስፋፋት በተለይም በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭቶች እየተዘገቡ ነው። «ኢኒሼቲቭ ፎር ቼንጅ» የሚል ተቋም መስርተው በሰላም ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩት ገረሱ ቱፋ እንደሚሉት ይኽ ጅምር ቶሎ እልባት ካልተበጀለት የብሔር ግጭትን የመቀስቀስ ዕድሉ ሰፊ ነው።

«ችግሩ ሌላም ቦታ በሰላም የሚኖረውን ኅብረተሰብ ይጎዳል። በአማራ ክልል በፌዴራል መንግሥት እና በክልሉ ውስጥ በታጠቁ ኃይሎች መካካል የሚደረገው ግጭት እራሱ በዚህ  መልኩ መቀጠል የለበትም። ከዚህ በፊት በትግራይ ክልልም እንዳየነው እንዲህ ግጭቶች የአስተዳደር ወሰኖችን ሲያቋርጡ መልካቸውን ወደ ብሔር ግጭት ነው የሚቀይሩት። ትልቁ ነገር ግን የትም ቦታ ግጭት እንዳይኖር ነው መሠራት ያለበት።»

በአማራ ክልል የሚካሄደው ግጭት ተገቢው ዘላቂ እልባት የሚያገኝበት መንገድ እንዲፈለግለት ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኞች ያሳስባሉ። ፎቶ ከማኅደር፤ በአማራ ክልል የአባይ ድልድይምስል Seyoum Getu/DW

ከአማራክልል ግጭት ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ክልል በኩል በተለይም በሰሜን እና ምሥራቅ ሸዋ የሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አከባቢዎች ላይ በተደጋጋሚ ግጭቶች ተከስተው ታይቷል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላም እና ደህንነት የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ መብራቱ ገርጂሶ ደግሞ መሰል የወሰን አካባቢዎች ግጭት ባሁኑ ወቅት በተለይም ለአዋሳኝ አካባቢው ኅብረተሰብ አደገኛ መሆኑን ይናገራሉ። «ይሄ ለሁለቱም ማኅበረሰብ አይጠቅምም፡ ይልቅ ለከፋ ጉዳት ነው የሚዳርጋቸውም» ብለዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ ዘላቂ ነው ያሉትን እልባት ሲገልጹም፤ «ከታጣቂዎች በተጨማሪ መንግሥትም በሆደ ሰፊነት የአማራ ክልሉን ጨምሮ በየትኛውም የአገሪቱ አቅጣጫ ካሉ ጥያቄ አለን ከሚሉ ወገኖች ጋር መነጋገር ነው» የሚበጀው ነው ያሉት። «ለመንግሥት ሊሰጥ የሚገባው ኃላፊነት ተሰጥቶ ሁሉም ይመለከተኛል የሚል አካል ለውይይት እራሱን ካላዘጋጀ መሳሪያ ታጥቆ በዚህ አገር ዴሞክራሲ ማስፈን የሚቻለው ኃይል የለም»ም ሲሉም ለሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሰላማዊ እልባት የሚኖረውን አስፈላጊነት አብራርተዋል።

ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW